የሥላሴ ማኅበር

ወደ ሥላሴ ማኅበር እንኳን በደህና መጡ፡፡ የሥላሴ ማኅበር በእግዚአብሔር አስገራሚ ፍቅር ተማርከንና ተሸንፈን ወደሰማያዊው ቤተሰብ ውስጥ የገባን ሰዎች ማኅበር ሲሆን እርስዎም በዚህ ፍቅር ተማርከው ከኛ ጋር ኅብረት ይኖሮዎት ዘንድ በታላቅ ፍቅር እንጋብዝዎታለን፡፡ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው። 1. ዮሐ. 1:3

የሥላሴ ማኅበር መሠረቱ በሰማይ ነው፡፡ የሥላሴ ማኅበር ሰማያዊ ነው፡፡ በአካል ሶስት በመለኮት አንድ የሆነው ሥሉስ እግዚአብሔር በመጀመሪያ ሰውን ሲፈጥረው በራሱ መልክ ነው፡፡ ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ አንድን ስናነብ እግዚአብሔር ሁሉን እንደወገኑ ፈጠረ እንዲህ እንዲህ እናነባለን፡፡ “እግዚአብሔርም አለ፦ ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን እንደ ወገኑ፥ እንስሳትንና ተንቀሳቃሾችን የምድር አራዊትንም እንደ ወገኑ፥ ታውጣ፤ እንዲሁም ሆነ። እግዚአብሔር የምድር አራዊትን እንደ ወገኑ አደረገ፥ እንስሳውንም እንደ ወገኑ፥ የመሬት ተንቀሳቃሾችንም እንደ ወገኑ አደረገ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።” ዘፍ።1፤24-25 እያለ ይተርክልንና ሰው ላይ ሲደርስ “እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።” ይላል፡፡ ዘፍ።1፤26-27 ሁሉን እንደወገኑ ከፈጠረ በኋላ ሰውን ደግሞ እንደ ወገኑ ማለትም በራሱ ወገን በእግዚአብሔር መልክና አምሳል ፈጠረው፡፡ ይህም ታላቅ ክብር ሲሆን ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት እንዲያደርግ የእግዚአብሔር ቤተሰብ እንደሆነ ያሳየናል፡፡ ሰው በውድቀት ምክን ያት ከዚህ ኅብረት ተለይቶ የነበረ ቢሆንም በኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ ወደዚህ ኅብረት መመለሱን ቅዱሳን ሐዋርያት እንዲህ በማለት ይመሰክሩልናል፡፡ “እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተ ደግሞ እናወራላችኋለን። ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው።”

ሰማያዊ ወደሆነው ወደዚህ ቤተሰብ ወደ ሥላሴ ማኅበር እንኳን በደህና መጡ፡፡

Play Video