አማኑኤል፡ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር

የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ብሥራት በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በጣም አስገራሚው ብሥራት  ነው።  ቅዱስ ማቴዎስ ስለሁኔታው እንዲህ ይተርክልናል፡፡

“የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበረ። እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች።እጮኛዋ ዮሴፍም ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ።

እርሱ ግን ይህን ሲያስብ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፥ እንዲህም አለ፦ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። በነቢይ ከጌታ ዘንድ፦እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም፦ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው።” ማቴ.  1፡18-23

ሆኖም በዚህ መለኮታዊ አዋጅ ዙሪያ ያሉት ሁኔታዎች አስገራሚ ሆነው ይታያሉ።

አማኑኤል “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” ነው የሚለውን ብሥራት ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ የተከሰቱት ነገሮች ነገሩ ነገሩ ግር እንዲለን ሊያደርጉ የሚችሉ ናቸው፡፡ ከተፀነሰበት ጊዜ ጀምሮ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ እና የእናቱ የቅድስት ድንግል ማርያም  ህይወት በፈተናዎች  የታጀበ ነበር። ድንግል የሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳለች፤ ይህ ሁኔታ በቀላሉ ለሕዝብ ውርደት አልፎ ተርፎም በኅብረተሰቡ ሥርዓት መሠረት ከባድ ቅጣት ሊያደርስባት የሚችል ነበር። እጮኛዋ የሆነው ዮሴፍ የመልአኩ መልእክት እስኪያረጋግጥ ድረስ በጥበብ ሁኔታውን ለመያዝ እየታገለ ነው፡፡  

የልደቱ ጊዜ ሲቃረብ፣ በአውግስጦስ ቄሳር አስቸኳይ የህዝብ ቆጠራ በመታወጁ ዮሴፍና ቅድስት ድንግል ማርያም አስቸጋሪ የእግር ጉዞ አድርገው ቤተ ልሄም ቢደርሱም  በእንግዶች ማደሪያ ቦታ ስላልተገኘ የዓለም መድኃኒት የሆነው ጌታ በግርግም እንዲወለድ ግድ ሆነበት። ብዙም ሳይቆይ ሄሮድስ ንጉሥ ተወለደ የሚል  አስደንጋጭ ዜና በመስማቱ ተቀናቃኝ መጣብኝ ብሎ ዙፋኑን ለማዳን በቤተልሔም የተወለዱ ሕጻናት እንዲገደሉ አዘዘ፡፡ ቅዱሱ ቤተሰብም በእግዚአብሔር ምሪት ወደ ግብፅ እንዲሰደዱ ግድ ሆነ። እንግዲህ ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው አማኑኤል ማለትም እግዚአብሔር ከነርሱ ጋር እግዚአብሔ ከኛ ጋር ሆነ በተባለበት እና በሆነበት ጊዜ ነው፡፡

እነዚህን ሁኔታዎች ስናይ በአንድ ጌዴዎን በአንድ ወቅት እንዳደረገው፣ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ፣ ይህ ሁሉ ለምን ደረሰብን?” አማኑኤል ከሆነ ይህ ሁሉ ችግር እንዴት ይመጣል?  ብሎ መጠየቁ ተፈጥሯዊ ይሆናል። ( መሳፍንት 6:13 ) እንደሰው ካሰብነው በእርግጥም አማኑኤል መባሉ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” መሆኑ ከችግርና ከሥቃይ ጋር መገናኘቱ ግራ የሚያጋባ ሊመስል ይችላል። እግዚአብሔር ከኛ ጋር ሲሆን ነገሮች ይመቻቻሉ እንጂ በመከራ ላይ መከራ ያመጣብናል እንዴ ብለንም ልንጠይቅ እንችላለን፡፡ 

“እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” የሚለው ትክክለኛ ትርጉም

አማኑኤል – እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚለው ሚስጢር ወይም የእግዚአብሔርን ከኛ ጋር መሆን ምኞታችንን ከማኘትና ለኛ የሚመች ከመሆን ያለፈ ነገር ነው፡፡ እግዚአብሔር ከኛ ጋር መሆኑ የፈተናዎች አለመኖርን ወይም የሁሉም ፍላጎቶች መሟላት አያመለክትም። ይልቁንም፣ በሁሉም ሁኔታ የእግዚአብሔርን መገኘት ያመለክታል፣  እርሱ ከኛ ጋር የሚሆነው በህይወታችን ውስጥ መለኮታዊ ዓላማውን ለመፈጸም ነው።

በብሉይ ኪዳን የምናገኘው  የዮሴፍ ታሪክ ይህንን እውነት ያሳያል። ዮሴፍ በወንድሞቹ ተላልፎ፣ ለባርነት ተሽጦ፣ በሐሰት ተከሶና ታስሯል፤ ዮሴፍ ብዙ መከራዎችን ተቋቁሟል። ሆኖም፣ ቅዱሳት መጻሕፍት በዚህ ሁሉ ሁኔታና ሂደት “እግዚአብሔርም  ከዮሴፍ ጋር ነበረ” በማለት ደጋግሞ ያረጋግጣል። ( ዘፍጥረት 39:2, 21 ) የእግዚአብሔር መገኘት የተረጋገጠው በፈተናዎች አለመኖር ሳይሆን በምሪቱና እና ከእርሱ ጋር ሆኖ ሞገስ እየሆነው በመጨረሻም ዮሴፍን ወደ ከፍታ ቦታ በማምጣት ትልቁን እቅዱን በመፈጸም ነው

በመከራ ላይ የበሰለ አመለካከት ይኑረን፡፡

ሐዋርያው ​​ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል? (ሮሜ 8፡31) ብሎ ይጠይቃል፡፡  ይህ ጥያቄ መጀመሪያ ላይ እግዚአብሔር ከኛ ጋር ሲሆን ምቾት እንደሚኖር ምንም እንደማይጎድለን  የሚጠቁም ቢመስልም  ጳውሎስ ወዲያውኑ ማብራራቱን ቀጠለ፡- 

“ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።” በማለት የእግዚአብሔር ከኛ ጋር መሆን እነዚህ ሁሉ እንዳይደርሱብን የሚያደርግ ሳይሆን በነዚህ ሁሉ በድል የሚያሳልፈን መሆኑን ያውጅልናል፡፡ መከራ፣ ጭንቀት፣ ስደት፣ ረሃብ እና አደጋ የክርስቲያናዊ ጉዞ አካል ናቸው።

ሆኖም ጳውሎስ እነዚህን መከራዎች አምላክ አለመኖሩን የሚያሳዩ ምልክቶች አድርጎ አይመለከታቸውም። ይልቁንም፣ “በዚህ ሁሉ በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን ይለናል፡፡  ( ሮሜ 8:37 )

በሕይወታችን ውስጥ የእግዚአብሔር መገኘት

አማኑኤልን  ወይም የእግዚአብሔርን ከኛ ጋር መሆን መረዳታችን ከእግዚአብሔር መገኘት የምንጠብቀውን ነገር እንደገና እንድናጤነው ይሞግተናል። የምድር ምቾት ወይም ያልተቋረጠ ፍጥረታዊ ደስታ ተስፋ አይደለም። ይልቁንም፣ እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ አብሮን እንደሚሆን በፈተናዎች እንደሚደግፈን እና ልምዶቻችንን ከዘላለማዊ ዓላማዎቹ ጋር እንደሚያስማማ ማረጋገጫው ነው።

ሁኔታዎች እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ቢመስሉም እንደ ጎለመሱ አማኞች፣ ስንመለከታቸው የምናልፍባቸው ሁሉ በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት እንድንታመን የበለጠ ያሳድጉናል። ልክ እንደ ሐዋርያው ​​ጳውሎስ፣ “ስለ እርሱ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን” እያልን በማወጅ ጥንካሬ እና ዓላማ ማግኘት እንችላለን። እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን። በእነዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ( ሮሜ 8፡36–37 )

የደስታ ጥሪ

የአማኑኤልነቱ አዋጅ – እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆኑ – በጥልቅ ደስታ እና ተስፋ ሊሞላን ይገባል። እግዚአብሔር በድል ጊዜ ብቻ ሳይሆን በፈተናም ጊዜ እንደሚገኝ ያረጋግጥልናል። የእርሱ መገኘት የጥንካሬያችን ምንጭ፣ የእምነታችን መልህቅ እና የመጨረሻው የድላችን ዋስትና ነው።

ይህ እውነት ጊዜያዊ ስሜቶችን ወይም ውጫዊ ሁኔታዎችን አልፎ ብቻችንን አይደለንም በሚለው እውነታ ላይ እንድንቆም ያደርገናል። የክርስቶስን መወለድና የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ፍጻሜ ላይ ስናሰላስል፣ “አማኑኤል—እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው” ብለን በድፍረት እናውጅ።

በረከትና ሰላም ላንተ ይሁን።

መምህር ጸጋ

Leave a Comment