ለወንጌሉ ሥራ ገንዝብ የምንሰጥበት ትክክለኛ መንገድና ምክንያት

“ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፥ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ።” ኤፌ 5፡32

በመምህር ጸጋ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

በእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ፍቅር ለተወደዳችሁ ወንድሞችና እህቶቻችን የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከእናንተ ጋር ይሁን፡፡ 

ባለፈው ጉባኤያችን የስላሴን ሕብረት አገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋትና ብዙዎችን በወንጌሉ ብርሃን ለማገልገል፤ በዓመት አራት ጊዜ ልናደርገውም ላሰብነው ማኅበርና እንደዚሁም በማኅበራዊ መገናኛዎች ልናስተላልፈው ስላሰብነው አገልግሎት ሁላችንም እግዚአብሔር በባረከን መጠን በገንዘባችን እንድንረዳ ተነጋግረን ነበር፡፡ በዚሁ መሠረት በሥራ ያላችሁ ወገኖች የምትችሉት ወርኃዊ ስጦታ እንድትሰጡ ፤ ተማሪዎች የሆናችሁና የማትችሉ ደግሞ በቻላችሁ ጊዜ በሙሉ ደስታ የበረከቱ ተካፋዮች እንድትሆኑ እናበረታታችኋለን፡፡ በዚህ የስጦታ አገልግሎት ለመካፈል ልባችሁ የፈቀደ ሁሉ የስጦታውን ፎርም በመሙላት በወር ምን ያህል መስጠት እንደምትችሉ እንድታሳውቁን በፍቅር እንጠይቃለን፡፡ 

ከሁሉ በፊት ግን ሁላችሁም ትክክለኛውን የመስጠት መርህና አካሄድ በማወቅ ታደርጉት ዘንድ የእግዚአብሔር ቃል ስለ መስጠት የሚናገረውን በጥቂቱ ላስታውሳችሁ፡፡

 

ምንም እንኳ ይህ አገልግሎት እንዲሰፋና ብዙዎች እንዲጠቀሙ ገንዘብ የሚያስፈልገን ቢሆንም ሳይገባችሁ በመስጠት ከበረከት እንድትጎድሉ  ግን አልሻም፡፡ ዘመኑ “የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጪው” የሚባልበት ዘመን ስለሆነ ስለ ህይወታችሁ ምንም ሳይገዳቸው ገንዘባችሁን ብቻ የሚፈልጉበት ዘመን ቢሆንም እኔ ግን እግዚአብሔር በረዳኝ መጠን ለቃሉ የታመንኩ እሆን ዘንድ መርጫለሁ፡፡ በመሆኑም የምታደርጉትን ሁሉ እንደ ቃሉ ታደርጉ ዘንድ ልመክራችሁ ይገባኛል፡፡

  1. ሁሉ የርሱ ነው፡፡

 ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል። ቆላ 1፤16

ሁሉን የፈጠረ እኛን በመልኩ የፈጠረ የምንተነፍሳትን እስትንፋስ የሰጠንና በእጁ የያዘ እርሱ ነው፡፡ የተማርነው፤ ሥራ ያገኘነው፤ ሰርተን የምንገባው፤ በየሰከንዱ የምንተነፍሰው እርሱ በሰጠን ህይወት ነው፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያው ሰጪ እርሱ እንጂ እኛ አይደለንም፡፡ በመሆኑም ምንም ነገር ለእግዚአብሔር ከመስጠታችን በፊት ሁሉንም ከርሱ መቀበላችንን ማወቅና ማመን ስለሰጠንም ማመስገን ይገባናል፡፡ ይህን ሳንረዳና ሳናምን ለእግዚአብሔር ከሰጠነው ከራሳችን የሰጠነው ነው የሚመስለን፡፡ ሁሉን ከርሱ እንደተቀበልን ስናምን  ግን እርሱ ከሰጠን መልሰን እየሰጠነው መሆኑን ስለምናውቅ በትእቢትና ለእግዚአብሔር እንዲህ አደረግሁለት በማለት አንመካም፡፡ ይልቅስ እንደ ንጉሱ ዳዊት እንዲህ እንላለን፡፡

 

1 ዜና 29

10፤ ዳዊትም በጉባኤው ሁሉ ፊት እግዚአብሔርን ባረከ፤ ዳዊትም አለ። አቤቱ፥ የአባታችን የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ተባረክ።

11፤ አቤቱ፥ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና ታላቅነትና ኃይል፥ ክብርም፥ ድልና ግርማ ለአንተ ነው፤ አቤቱ፥ መንግሥት የአንተ ነው፥ አንተም በሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያልህ ራስ ነህ።

12፤ ባለጠግነትና ክብር ከአንተ ዘንድ ነው፥ አንተም ሁሉን ትገዛለህ፤ ኃይልና ብርታት በእጅህ ነው፤ ታላቅ ለማድረግ፥ ለሁሉም ኃይልን ለመስጠት በእጅህ ነው።

13፤ አሁንም እንግዲህ፥ አምላካችን ሆይ፥ እንገዛልሃለን፥ ለክቡር ስምህም ምስጋና እናቀርባለን።

14፤ ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነውና፥ ከእጅህም የተቀበልነውን ሰጥተንሃልና ይህን ያህል ችለን ልናቀርብልህ እኔ ማን ነኝ? ሕዝቤስ ማን ነው?

ቅዱስ ዳዊት ይህን ሁሉ ወርቅና ብር ለመቅደሱ መሥሪያ ከሰጠ በኋላ ነበር ይህን የተናገረው፡፡ ወርቁንና ብሩን የሰጠው ከእግዚአብሔር እንደተቀበለው ካወጀ በኋላ ነው፡፡

 

  1. መሰጠትና መስጠት

ሁለተኛ ከመስጠታችን በፊት እኛ ራሳችን ለእግዚአብሔር መሰጠት አለብን፡፡ ክርስቶስ በደሙ የገዛው እኛን እንጂ ገንዘባችንን አይደለምና፡፡

ስለዚህ እግዚአብሔር መጀመሪያ የሚፈልገው እኛን እንጂ ያለንን አይደለም፡፡ 

እግዚአብሔር አባታችንን አብርሃምን ልጁን እንዲሰጠው ከመጠየቁ በፊት እርሱን ራሱን እንዲህ አለው

“እግዚአብሔርም አብራምን አለው። ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ። ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፥ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም አከብረዋለሁ፤ ለበረከትም ሁን፤” ዘፍ.12 እና 1  እና 2

 

አባታችን አብርሃምም ይህንን ቃል አምኖ ታዘዘና ከባቢሎን ከዑር ወጣ፡፡ አገሩን ህዝቡን ቤተሰቡን ትቶ ለእግዚአብሔር ተለየ ወጣ ራሱንም ለአምላኩ ሰጠ፡፡ ከዚያም በኋላ በስተ እርጅናው እግዚኣብሔር ይስሐቅን ሰጠው፡፡ በመጨረሻም አንዱን ልጁን ይስሐቅን እንዲሰዋለት ጠየቀው {ዘፍ22} ልብ በሉ እግዚአብሔር ከመጠየቁ በፊት ራሱ ነው የሰጠው፡ ልጅህን ሰዋልኝ ሲለው የሰጠውን ነው የጠየቀው፡ እግዚአብሔር ያልሰጠውን አይጠይቅም ካልዘራበትም ሊያጭድ አይመጣም፡፡ 

ጻድቁ ኢዮብ ያለውን ሁሉ ሲያጣ እንኳ እግዚአብሔርን ሊያመሰግን የበቃው ሁሉን የተቀበለው ከእግዚአብሔር መሆኑን ስላወቀ ነው፡፡

ስለዚህ ሁሉን ሲያጣ እግዚአብሔርን አልከሰሰም ይልቅስ እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔርም ነሣ፤ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን። በማለት አመሰገነ {ኢዮ1፤21} ማስተዋሉን ተመልከቱ ያጣው ሁሉ የራሱ እንደሆነ ቢያስብ ኖሮ እግዚአብሔር  ነሳ ብሎ ነበር የሚጀምረው እርሱ ግን ሁሉን የተቀበለው ከእግዚአብሔር እንደሆነ ያውቃልና እግዚአብሔር ሰጠ .. ብሎ ጀመረ፡፡ በዚህ ሁሉ የምንረዳው እግዚአብሔር በሁላችንም ህይወት በመስጠት ነው የጀመረው፡፡ ሁሉን ከርሱ መቀበላችንን ስናውቅ መስጠት ቀላል ይሆንልናል፡፡ አንድ ሰው ከራሳችሁ ብዙ ገንዘብ እንድሰጡት ቢጠይቃችሁ ሊከብዳችሁ ይችላል አስቀምጥልኝ ብሎ የሰጣችሁን ገንዘብ ለመውሰድ ሲጠይቃችሁ ግን እንዴት ይከብዳችኋል?? እግዚአብሔርም ለወንጌሉ ሥራ እንድንሰጥ እየጠየቀን ያለው እርሱ ራሱ ከሰጠን በረከት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የቆሮንቶስን ምእመናን በቅዱሱ ስጦታ እንዲሳተፉ ሲጠይቃቸው “ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤ “ በማለት የሚዘሩትን ወይም የሚሰጡትን የሰጣቸው እግዚአብሔር እንደሆነ ያስረዳቸዋል {2.ቆሮ.9፤10} 

ሌላው አዲስ ኪዳናዊው የመስጠት አምልኮ ምን እንደሚመስል ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር ሁለት ዋና መርሆዎችን ያስቀምጣል፡፡

 

  1. የመዝራትና የማጨድ ህግ

 

“እኔ ነጻ አይደለሁምን? ሐዋርያስ አይደለሁምን? ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስንስ አላየሁትምን? እናንተስ በጌታ ሥራዬ አይደላችሁምን?

የሐዋርያነቴ ማኅተም በጌታ እናንተ ናችሁና ለሌሎች ሐዋርያ ባልሆን ለእናንተስ ምንም ቢሆን ሐዋርያ ነኝ።

ለሚመረምሩኝ መልሴ ይህ ነው። ልንበላና ልንጠጣ መብት የለንምን?

እንደ ሌሎቹ ሐዋርያትና እንደ ጌታ ወንድሞች እንደ ኬፋም፥ እኅት ሚስታችንን ይዘን ልንዞር መብት የለንምን? ወይስ ሥራን ለመተው መብት የሌለን እኔና በርናባስ ብቻ ነን?

ከቶ በገዛ ገንዘቡ በወታደርነት የሚያገለግል ማን ነው? ወይስ ወይን ተክሎ ፍሬውን የማይበላ ማን ነው? ወይስ መንጋ እየጠበቀ ከመንጋው ወተት የማይጠጣ ማን ነው?

ይህን በሰው ሥልጣን ብቻ እላለሁን? ሕግስ ደግሞ ያን አይልምን? የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር ተብሎ በሙሴ ሕግ ተጽፎአልና። እግዚአብሔርስ ስለ በሬዎች ይገደዋልን?

ይህን የሚለው ፈጽሞ ስለ እኛ አይደለምን? የሚያርስ በተስፋ ሊያርስ የሚያበራይም እንዲካፈል በተስፋ ሊያበራይ ስለሚገባው በእውነት ስለ እኛ ተጽፎአል።

እኛ መንፈሳዊን ነገር የዘራንላችሁ ከሆንን የእናንተን የሥጋዊን ነገር እኛ ብናጭድ ትልቅ ነገር ነውን?”      1 ቆሮ 9፡1-11

በዚህ ክፍል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሚመረምሩትና ስለርሱም ስለሌሎቹ ሐዋርያት ጥያቄ ላላቸው ሰዎች መልስ ሲሰጥ ልንበላና ልንጠጣ መብት የለንምን? በማለት ይጀምርና በገዛ ገንዘቡ በወታደርነት የሚያገለግል ማነው ? ወይን ተክሎስ ፍሬውን የማይበላ ወይስ መንጋን እየጠበቀ ከመንጋው ወተትን የማይጠጣ ማነው? በማለት ያስተምራቸዋል፡፡ በመቀጠልም እርሱ  በሐዋርያነቱ ከሌሎች ጋር ሆኖ እያገለገላቸው እንደሆነና መንፈሳዊ ነገርን የዘሩላቸው ከሆነ ፍጥረታዊ ነገርን ከእነርሱ ቢያጭዱ ትልቅ ነገር እንዳልሆነ ማለትም ቆሮንቶሶች ከሚሰጡት ገንዘብ ይልቅ በክርስቶስ አገልጋዮች የተዘረላቸው ወንጌል ትልቅ እንደሆነ ያሳያቸዋል፡፡

ከዚህ ቃል እንደምንማረው ትክክለኛው አዲስ ኪዳናዊ ስጦታ በመዝራትና በማጨድ ህግ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ከላይ እንዳየነው እግዚአብሔር ካለዘራበት አያጭድም፡፡ ስለዚህ ወንጌሉን ከዘራብን በኋላ ህይወታችን ከተጠቀመና ከተለወጠ በኋላ ነው በገንዘባችን አገልግሎቱን እንድንደግፍ የሚፈልገው፡፡ ራሱን ጌታችንንና መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በገንዘባቸው ያገለግሉት ስለነበሩት ሰዎች ሲናገር 

“ከዚህም በኋላ እየሰበከና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች እየተናገረ በየከተማይቱ በየመንደሩም ያልፍ ነበር፤

አሥራ ሁለቱም ከእርሱ ጋር ነበሩ፥ ከክፉዎች መናፍስትና ከደዌም ተፈውሰው የነበሩ አንዳንድ ሴቶች፤ እነርሱም ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የምትባል ማርያም፥

የሄሮድስ አዛዥ የኩዛ ሚስት ዮሐናም ሶስናም ብዙዎች ሌሎችም ሆነው በገንዘባቸው ያገለግሉት ነበር።” ሉቃስ 8፤1-3

 

በገንዘባቸው እንዲያገለግሉት ከመፍቀዱ በፊት ከክፉዎች መናፍስትና ከደዌም ፈውሶአቸው ቃሉን አስተምሮአቸው እየተከተሉት ነበር፡፡ ይህም የሚያሳየን እግዚአብሔ በመጀመሪያ የሚፈልገው እኛን ካለብን ሸክምና መከራ ማሳረፍ በወንጌሉ ነጻ ማውጣት ነው፡፡ ለዚህም ነው በመጀመሪያ ሲጠራን 

“እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።” ማቴ. 11፤28 – 30 

እግዚአብሔር ሳያሳርፈን ከኛ ምንም አይፈልግም፡፡ በመሆኑም እናንተም ለዚህ አገልግሎት መስጠት ያለባሁ በአገልግሎቱ ከተጠቀማችሁ፤ እግዚአብሔር በወንጌሉ ኃይል ነጻ ካወጣችሁ፤ በዚህ አገልግሎት እግዚአብሔር የቃሉን በረከት በህይወታችሁ ከዘራና፤ ቃሉ በህይወታችሁ በቅሎ እየለወጣችሁ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ከእናንተ ገንዘብን ከተቀበልን ካልዘራንበት አጭደናልና ባለእዳዎች እንሆናለን፡፡ ይህንን ደግሞ እንዳናደርግ እግዚአብሔር በቃሉ አስተምሮናል፡፡

ይህ የሆነላችሁ ወንድሞቼና እህቶቼ እናንተ ያገኛችሁት በረከተ ወንጌል ለሌሎች ደግሞ ይደርስ ዘንድ በምትችሉት ሁሉ አገልግሎቱን እንድታግዙ አበረታታችኋለሁ፡

 

  1. በልብ እንዳሰቡ በደስታ መስጠት 

እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም። 2.ቆሮ. 9፤7

እግዚአብሔር የምንሰጠውን ብቻ ሳይሆን የምንሰጥበትን ልብም ያያል፡ ለርሱ የምንሰጠውን ሁሉ በኃዘን በግድ ሳይሆን በልባችን እንዳሰብን ፍቅሩ ግድ ብሎን በደስታ እንድናደርገው ይወዳል፡፡ ለሰው እንኳ ስጦታን ስንሰጥ ፍቅሩ ግድ ብሎን እንደምናደርገው ለእግዚአብሔርም ለምንሰጠው ሁሉ ምክንያቱ እውነተኛ ፍቅር ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡

እውነተኛው የወንጌል ሰባኪ ቅዱስ ጳውሎስ የቆሮንቶስን ሰዎች በዚህ ሁሉ ቃል ከመከራቸው በኋላ 

“እነሆ፥ ወደ እናንተ እመጣ ዘንድ ስዘጋጅ ይህ ሦስተኛዬ ነው፤ አልከብድባችሁምም፥ እናንተን እንጂ ያላችሁን አልፈልግምና..” ይላቸዋል {2.ቆሮ.12፤14}

እግዚአብሔርም እናንተን እንጂ ያላችሁን አልፈልግምና ያላችሁን ከመስጠታችሁ በፊት ራሳችሁን ገንዘብ ከመስጠታችሁ በፊት ህይወታችሁን ስጡት፡፡

 

እግዚአብሔር ሁላችሁንም ይባርክ፡፡

መምህር ጸጋ

https://yeslasemahber.com/ 

https://www.facebook.com/Yeslasemahber 

support@yeslasemahber.com/

life@yeslasemahber.com/

https://www.facebook.com/MemhirTsega/

Phone:- 2817454435

             832-466-2140

 

Back

የጸጋው ብዛት እንጂ የገንዘብ ብዛት ሰጪዎችና ለጋሶች አያደርገንም፡፡ ትክክለኛው ስጦታ ራሳችንን ለጌታ ከሰጠን በኋላ ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሳ የምናደርገው ነው፡፡

ወንድሞች ሆይ፥ ለመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ እናስታውቃችኋለን፤ በብዙ መከራ ተፈትነው ሳሉ የደስታቸው ብዛትና የድህነታቸው ጥልቅነት የልግስናቸውን ባለ ጠግነት አብዝቶአል፤ እንደ ዓቅማቸው መጠን ከዓቅማቸውም የሚያልፍ እንኳ ወደው እንደ ሰጡ እመሰክርላቸዋለሁናለቅዱሳን በሆነው አገልግሎት እንዲተባበሩ ይህን ቸርነት በብዙ ልመና ከእኛ ይለምኑ ነበር፥አስቀድመውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸውን ለጌታ ለእኛም ሰጡ እንጂ እንዳሰብን አይደለም።

2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 8፡1-5