Jesus is born

ወደ ዓለም የገባው በኩር

የእግዚአብሔር ፍቅር

በኩርን ወደ ዓለም ሲያገባ”  እብ 1:6

በመምህር ጸጋ

ወደ ዓለም የገባው በኩር

በሁሉ ፊተኛ የፍጥረት ሁሉ መሠረት የኋለኛው አዳም ዛሬ ተወለደ፡፡ 

“ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤ ከመላእክት ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ስምን በወረሰ መጠን እንዲሁ ከእነርሱ አብዝቶ ይበልጣል። ከመላእክትስ፦ አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፥ ደግሞም፦ እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል ያለው ከቶ ለማን ነው? ደግሞም በኵርን ወደ ዓለም ሲያገባ፦ የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ ይላል።” እብ 1:1-6

ወደ ዓለም የገባው ከቅድስት ድንግል ማርያም በበረት የተወለደው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሁሉ በኩር እና ፊተኛ ነው፡፡ 

“እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው ሁሉም በእርሱ ተጋጥሞአል።  እርሱም የአካሉ ማለት የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ፥ መጀመሪያ ከሙታንም በኵር ነው።” ቆላ 1:15-18

እግዚአብሔር በኩርን ነው ወደ ዓለም ያስገባው፡፡

ወደ ዓለም የገባው ሊያድነን ሊያከብረን የመጣው የሁሉ በኩር እና ፊተኛ የሆነው በመጀመሪያ የነበረው የዘላለም ቃል ነው፡፡

የነበረው ተወለደ ያለው መጣ በኩሩ ተገለጠ፡፡ ከርሱ በፊት በመገለጣቸው በኩር የመሰሉን ሁሉ በኩር እንዳልሆኑ ተጋለጡ፡፡ እውነተኛው በኩር ወደ ዓለም ገባ፡፡ ለካ አዳም በኩር አልነበረም ለካ አዳም ቀዳሚ አልነበረም፡፡ ለካ ሞት ጅማሬም ፍጻሜም አይደለም፡፡ ይህንን ዘላለማዊና ድንቅ ሚስጢር ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየንን ታሪክ እንመልከት፡፡

“እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው ሁሉም በእርሱ ተጋጥሞአል።  እርሱም የአካሉ ማለት የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ፥ መጀመሪያ ከሙታንም በኵር ነው።” ቆላ 1:15-18

የያእቆብና ኤሳው የማህጸን ግብግብ

ተረከዝ ይዞ መወለድ

ይስሐቅ ለአባቱ ፈቃድ የተሰዋ የእግዚአብሔር ልጅ ምሳሌ ነው፡፡ ከይስሐቅ እስራኤል እንጂ ኤሳው ሊወጣ አይገባውም፡፡ መንፈስ እንጂ ሥጋ ሊገለጥ አይገባም፡፡ እረኛ እንጂ አዳኝ ቀስተኛ ሊወለድ አይገባም፡፡ የእግዚአብሔር ሐሳብና ቃል ኪዳን በይስሐቅ ዘር ይጠራ ዘንድ ነው፡፡ አስቀሞ ለአብርሃም ቃል ኪዳን ገብቶአል፡፡ በአንተና በዘርህ አህዛብ ይባረካሉ ዘርህ እንደ ሰማይ ከዋክብት ይበዛሉ ተብሎአል፡፡ ይህ ሁሉ የይስሐቅ በረከት የሚፈጸመው በያእቆብ እንጂ በኤሳው አይደለም፡፡ ስለዚህ ያእቆብ ቀድሞ መወለድ አለበት፡፡ በእግዚአብሔር እይታ ቀዳሚው በኩሩ ይህ የበረከት ዘር የሆነው ያእቆብ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ እንዳይሆን በርብቃ ማህጸን ጦርነት እየተካሄደ ነበር፡፡ ሁለት በማህጸን ያሉ ህጻናት እኔ እቀድም እኔ እቀድም እየታገሉ ነው፡፡ ያእቆብ በኩር ወራሽ እንዲሆን ቀድሞ ቢወሰንም ተቀናቃኝ ገጥሞታል፡፡ በእናት ማህጸን በማይታየው ዓለም ከፍተኛ ግብግብ እየተካሄደ ነው፡፡ ሆድዋ የጦርነት ማእከል የሆነባት ርብቃ አቤቱታዋን አሰማች፡፡

“ልጆችም በሆድዋ ውስጥ ይገፋፉ ነበር፤ እርስዋም፦ እንዲህ ከሆነ ይህ ለእኔ ምኔ ነው? አለች። ከእግዚአብሔርም ትጠይቅ ዘንድ ሄደች። እግዚአብሔርም አላት፦ ሁለት ወገኖች በማኅፀንሽ ናቸው፥ ሁለቱም ሕዝብ ከሆድሽ ይከፈላሉ፤ ሕዝብም ከሕዝብ ይበረታል፤ ታላቁም ለታናሹ ይገዛል። ትወልድ ዘንድ ዘመንዋ በተፈጸመ ጊዜም፥ እነሆ፥ በማኅፀንዋ መንታ ነበሩ። በፊትም የወጣው ቀይ ነበረ፥ ሁለንተናውም ጠጕር ለብሶ ነበር፤ ስሙም ዔሳው ተባለ። ከዚያም በኋላ ወንድሙ ወጣ፥ በእጁም የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ነበር፤ ስሙም ያዕቆብ ተባለ። እርስዋ ልጆችን በወለደቻቸው ጊዜ ይስሐቅ ስድሳ ዓመት ሆኖት ነበር። ብላቴኖቹም አደጉ፤ ዔሳውም አደን የሚያውቅ የበረሃ ሰው ሆነ፤ ያዕቆብ ግን ጭምት ሰው ነበረ፥ በድንኳንም ይቀመጥ ነበር።” ዘፍ 25፡22-27

በእግዚአብሔር ታላቁ ቀድሞ ቢገለጥም ለታናሹ እንዲገዛ ተወስኖአል፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅነት በመገለጥ ቀዳሚነት ሳይሆን በመኖር ቀዳሚነት ነው፡፡ ስለዚህ ያእቆብ በእግዚአብሔር ዘንድ ገዢ እንዲሆን ተወስኖአል፡፡ ኤሳው ቀድሞ ቢወለድ በኩር አይሆንም፡፡ ስለዚህ ቀድሞ ቢወለድም እንደማያመልጠው ለማሳየት ያእቆብ ተረከዙን ይዞት ተወለደ፡፡ ኤሳው ቀድሞ ቢወለድም ሁለንተናው ጸጉር ተከናንቦ ነበር፡፡ ጸጉርን መከናነብ የመገዛት ምልክት ነው፡፡ ስለዚህ ቀድሞ መታየቱ ቀድሞ መገለጡ ቀዳሚ ገዢ አላደረገውም፡፡ በኩርነት ህይወት ነው፡ በኑሮ በእርምጃ የሚገለጥ በኤሳው ደግሞ ይህ ህይወት አይታይም ነበር፡፡ የኤሳውና የያእቆብ ኑሮ ምን እንደሚመስል እንመልከት፡፡

የቤት ልጅና የበረሃ ልጅ

በርብቃ ማህጸን ውስጥ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት በማይታየው የእግዚአብሔር ዓለም ይካሄድ የነበረው ሚስጢር ግልጦት ነው፡፡ ይስሐቅ አብርሃም የአብ ይስሐቅ የዘላለማዊው ቃል የክርስቶስ ያእቆብ ደግሞ ሰው የሆነው ክርስቶስ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ይስሐቅ የተስፋ ቃል ልጅ ነው፡፡ ለአብርሃም በተሰጠው የተስፋ ቃል ልጅ የተወለደ፡፡ ይህ የተስፋ ቃል እግዚአብሔር አብ ለሰው ልጆች ሁሉ የሰጠው የእውነተኛው ተስፋ ቃል የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ኤሳው ደግሞ የፊተኛው አዳም ምሳሌ ነው፡፡ ኑሮአቸውና ፍላጎታቸው በእጅጉ የተለያየ ነው፡፡ ኤሳው የበረሃ ሰው ሲሆን ያእቆብ የቤት የድንኳን ሰው ነው፡፡ ያእቆብ በድንኳን የሚቀመጠው ጭምት ስለሆነ ሲሆን ኤሳው በረሃን የሚወደው ደግሞ አዳኝ ቀስተኛ ለፍቶ አዳሪ ስለሆነ ነው፡፡ እነዚህ ልጆች የሁለቱ አዳሞች ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በእግዚአብሔር ዓለም ሁለት አዳሞች አሉ አንዱ ፍጥረታዊ ሌላኛው መንፈሳዊ አንዱ ምድራዊ ሌላኛው ሰማያዊ አንዱ ህያው ነፍስ ያለው ሌላኛው ህይወትን የሚሰጥ መንፈስ አንዱ ሞትን ኃጢአትን ያስገባ ሌላኛው ደግሞ ህይወትን ጽድቅን ያስገባ ናቸው፡፡ በኩሩ መጀመሪያው የበረከት ተስፋ ያለው ኋለኛ የተባለው አዳም ክርስቶስ ሲሆን ፊተኛ የተባለው አዳም ግን ፊተኛ የተባለው እንደ ኤሳው ቀድሞ ስለተገለጠ እንጂ ብኩርናና በረከትስ የርሱ አይደለም፡፡ ፊተኛ የተባለው አዳም ፊተኛነቱ በመገለጥ እንጂ በህልውና አይደለም፡፡ በህልውናማ በመጀመሪያ ቃል ነበረ የተባለለት ዘመን የማይቆጠርለት የፍጥረት ሁሉ ፊተኛ እና በኩር የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ስለነዚህ ሁለት አዳሞች የሚተርክልን ቅዱስ ጳውሎስ የክርስቶስን ቀዳሚነትና በኩርነት ካወጀልን በኋላ ስላገላለጣቸው ሲናገር “እንዲሁ ደግሞ፦ ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም።” {1 ቆሮ 15:45-46::} አዎ ኋለኛው አዳም የተባለው ክርስቶስ በህልውና ቀዳሚ እና ዘመን የማይቆጠርለት ዘላለማዊ ቢሆንም በመገለጥ በመምጣት ደረጃ ፍጥረታዊው አዳም ቀድሞአል፡፡ ቀድሞ የመጣው አዳም ኃጢአትንና ሞትን ይዞብን መጣ በአንድ ሰው ምክንያት ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፡፡ ይህ በኃጢአት በሞት በዓመጻና በክፋት የተሞላ አሁን የምናየው የዓለም ህዝብ ከዚህ ከሞተ ማንነት የተወለደ ነው፡፡በመገለጥ ደረጃ ይህ ሞትን ያመጣብን አዳም ቀዳሚ ቢመስልም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ቀዳሚና በኩር የሆነው ኋለኛው የተባለውና እንደ ያእቆብ ከኋላ ተረከዝ ይዞ የተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሚስጢር ስለተረዳ ኃጢአትንና ሞትን ስላስገባብን ስለፊተኛው አዳም ከተናገረ በሁላ “አዳም ይመጣ ዘንድ ላለው ለእርሱ አምሳሉ ነውና።” ይለናል፡፡ ሮሜ 5፤14፡፡ እንደ ኤሳው በረሃ በረሃ አደን አደን ጥሮ ግሮ ራስን መቻል በወዝ በድካም መብላት እንጂ በድንኳን በገነት ማረፍና መቀመጥ የማይወደው የበረሃ ሰው አዳም ይዞን በረሃ ቢገባም በቤት በድንኳን መቀመጥ የሚወደው በአባቱ እቅፍ ያለው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከጠፋንበት ከተቅበዘበዝንበት በረሃ መልሶ ወደቤት ሊያስገባን መጣ፡፡

አዳም ከእግዚአብሔር ድንኳን ወጥቶ ከእግዚአብሔር ተለይቶ በምድረ በዳ ሲያቅበዘብዘን ክርስቶስ ግን ከባህርይ አባቱ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በአብ ዘንድ ይኖር ነበር፡፡ ዘመኑ ሲደርስም በድንኳን ያለው ለሰው ልጆች የተሰጠውን ተስፋ ሁሉ የያዘው ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ ዘንድ ወጥቶ መጣልን፡፡

“ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤” 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 1፡1-2::
በአብ ዘንድ የነበረው ለእኛም የተገለጠው ጌታ በቤት የሚኖር ልጅ ነው፡፡

“ኢየሱስ መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው። ባርያም ለዘላለም በቤት አይኖርም፤ ልጁ ለዘላለም ይኖራል። እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ።” ብሎናልና፡፡ {ዮሐ 8፤34 36} እኛ ግ ን በአዳም ምክን ያት የኃጢአት ባሪያዎች ስለነበርን በቤት አንኖርም ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የበረሃ ወይራ በማለት ይገልጸናል፡፡

“ነገር ግን ከቅርንጫፎች አንዳንዱ ቢሰበሩ አንተም የበረሀ ወይራ የሆንህ በመካከላቸው ገብተህ ከእነርሱ ጋር የወይራ ዘይት ከሚወጣው ሥር ተካፋይ ከሆንህ፥ በቅርንጫፎች ላይ አትመካ፤ ብትመካባቸው ግን ሥሩ አንተን ይሸከምሃል እንጂ ሥሩን የምትሸከም አንተ አይደለህም።” { ሮሜ 11፡17-18} እኛን እንደ ኤሳው የበረሀ ሰዎች የነበርነውን የኃጢአትና የሞት ባሪያዎች የነበርነውን ልጆች አድርጎ ወደ አባቱ ቤት ሊያስገባን መጣ፡፡ {ዮሐ 14}

መልካም እረኛ

ያእቆብ በቤት የሚቀመጥ ብቻ ሳይሆን የበጎች እረኛም ነው፡፡ ኤሳው ግን አዳኝ ነው፡፡ ባህርያቸው በእጅጉ ይለያያል፡፡ ያእቆብ ከኮበለለበት ምድር ሲመለስ ኤሳው ሊቀበለው መጣ፡፡ ከዚያም አብረው እንዲሄዱ ጠየቀው፡፡ “እርሱም፦ ተነሣና እንሂድ፥ እኔም በፊትህ እሄዳለሁ አለ።”
እረኛው ያእቆብ ግ ን እንዲህ ብሎ መለሰ፡፡ “እርሱም አለው፦ ጌታዬ ሆይ፥ ልጆቹ ደካሞች እንደ ሆኑ ታውቃለህ፤ በጎችና ላሞችም ግልገሎቻቸውን ያጠባሉ፤ ሰዎችም አንድ ቀን በችኮላ የነዱአቸው እንደ ሆነ ከብቶቹ ሁሉ ይሞታሉ።ጌታዬ ከባሪያው ፊት ቀድሞ ይለፍ፤ እኔም ወደ ሴይር ከጌታዬ ዘንድ እስክደርስ ድረስ ከፊቴ ባሉት በእንስሳቱ እርምጃና በሕፃናቱ እርምጃ መጠን በዝግታ እከተላለሁ።” {ዘፍ 33 -12 14}
የያእቆብ እርምጃ በበጎቹ የተለካ ነው፡፡ ስለራሱ ሳይሆን ስለበጎቹ ይራመዳል፡፡ ያእቆብ የዘላለሙ እረኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ስለዚህ ስለዘላለሙ እረኛ ሲናገር እንዲህ ይላል፡፡

“እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ኃያል ይመጣል ክንዱም ስለ እርሱ ይገዛል፤ እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር ደመወዙም በፊቱ ነው። መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፥ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፥ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል።” ኢሳ 40 10 11 ይህ መንፈስ ነበር በያእቆብ እየሰራ የነበረው ስለዚህ ስለበጎቼ ቀስ ብየ ዝግ ብየ እራመዳለሁ አለ፡፡ ወንድሞቼ እህቶቼ እግዚአብሔር ኃያል አምላክ ነው፡፡ የመብረቅ ፍጥነት የመላእክት መብረር አይደስበትም፡፡ አረማመዱ የፍጥነት መለኪያ የለውም፡፡ ነገር ግ ን መልካም እረኛ ነው፡፡ ከኛ ጋር ሲራመድ እንደኛ ይራመዳል፡፡ አባት የህጻን ልጁን እጅ ይዞ በልጁ እርምጃ ልክ እንደሚራመድ መልካሙ እረኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድንቅ መካር ኃያል አምላክ ሆኖ ሳለ በእያንዳንዳችን የድካም ልክ ይራመዳል፡፡ የዘላለሙ አምላክ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ እኛን አህሎ መጣ፡፡ በኛ ላይ ያለው ዓላማው ፍቅር ነውና የፍቅር ገመድ ከኛ ጋር አስሮት ኃያልነቱን ሰውሮበታል፡፡ እርሱ ታናናሽ ጠቦቶች የሆነውን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ተሸክሞናል፡፡ ክንዱ በኛ ላይ ሳይሆን ለኛ ነው፡፡ መራመድ እንደማንችል ደካሞች እንደሆንን ተረድቶ ብድግ አድርጎ አቅፎናል፡፡ የሚያጠቡትን ደግሞ በቀስታ ይመራል፡፡ የያእቆብ በጎች ፊተኛ ሆኖ የተወለደው ኤሳው ቢመራቸው ኖሮ አልቀው ነበር፡፡ ነገር ግን ኋለኛ ሆኖ የተወለደው ነገር ግ ን የብኩርና ቃል ኪዳን ያለው ያእቆብ እረኛ ሆነላቸው፡፡ እኛም የፊተኛው አዳም ወደ በረሃ ነዳን ገደለን ነገር ግን ኋለኛው አዳም ክርስቶስ መጥቶ በክንዱ ሰብስቦ ተሸከመን፡፡

ኤሳው ፈጣን ተራማጅ ነው፡፡ ውጤቱ የሚለካው በፍጥነቱ በአለሞ ተኳሽነቱ በላቡ በማደሩ ነው፡፡ ኤሳው በረከትን የሚያገኝ የሚመስለው በሥራው ነው፡፡ በኩር ሆኖ መወለዱን ረስቶ በረከትን ለማግኘት ለአባቱ ምግብ አድኖ ለማምጣት ሄደ፡፡ ሰርቶ በሚያገኘው በረከት እንጂ ከእግዚአብሔር በጸጋ በተገኘ ብኩርና አያምንም፡፡ በኩር የሚለው ስም ቢኖረውም በኩርነት በውስጡ ዋጋ የለውም፡፡ ብክርናየ ለምኔ ናት ማለቱን አስታውሱ፡፡ ስለዚህ ኤሳው ሁሉን በጥረቱ በሥራው ለማግኘት የሚፈልግ ለፍቶ አዳሪ ጥሩ የአዳም ልጅ ሲሆን ያእቆብ ደግሞ በድንኳን የሚቀመጥ ያረፈ ማንነት ያለው ሰው ነው፡፡ ለያእቆብ እረፍት ከሁሉ በፊት ነው፡፡
ይህ የበጎች እረኛ ነው በበረት የተወለደው፡፡ የበጎቹ እረኛ በበረት ተወለደ፡፡

የአባት ፍቅር

ከዚህ በታች ያለውን የወንጌል ድምጽ እንዲሰሙ በታላቅ ፍቅር እንጋብዝዎታለን፡፡

የዳዊት ልጅ ህጻኑ ንጉሥ፡፡

ሳይታጀብ ሳይታጠቅ ብቻውን መጣ በበረት ተወለደ መላእኩትም የምስራቹን ሊያወሩ እንጂ ሊዋጉለት ወይም ሊያግዙት አልመጡም፡፡  በኩሩ ወደዚህች ዓለም ሲገባ ከርሱ በፊት የመጡትን ሌቦችና ወንበዴዎች አስወግዶ በመንግሥቱ ሁሉን ለመጠቅለል ነው፡፡ የእግዚአብሔር የዘላለም ሐሳብ ሁሉን በክርስቶስ ለመጠቅለል ነውና፡፡ {ኤፌ.1:10} የሁሉ በኩር የሆነው ህጻኑ ልጅ ሲወለድ ሄሮድስ በኢየሩሳሌም ላይ ንጉሥ ነበር፡፡ ቀያፋና ሃና ሊቃነ ካህናት ናቸው፡፡ የዳዊት ምድር ያልተገረዘ ሮማዊ ነግሶባታል፡፡ ቅዱሱ መቅደስ ሥጋዊያኑ ካህናትና ነጋዴዎች የወንበዴዎች ዋሻ አድርገውታል፡፡ በአጠቃላይ የዚህች ዓለም ህዝብ በጨለማው መንግሥት በዲያብሎስ ባርነት ሥር ነው፡፡ ይህንን ሁሉ ጨለማ ገፎ ሁሉን በብርሃን መንግሥቱ ሊጠቀልል ከአብ ዘንድ የመጣው ክርስቶስ በቤተልሄም በበረት ተወለደ፡፡ ጠላቶቹን ሁሉ ከግሩ በታች ለማስገዛትና የብርሃን መንግሥቱን ለመግለጠ የመጣው የእግዚአብሔር ተዋጊ በእጁ ላይ ግ ን ምንም ዓይነት የሚታይ የጦር መሳሪያ የለም፡፡ የጦር እቃው ማንነቱ ራሱ ነው፡፡ እርሱ በመጀመሪያ የነበረው ሁሉ በርሱ የሆነው ከሆነውስ እንኳ አንዳች ያለ እርሱ ያልሆነው የዘላለም ፈጣሪ ነው፡፡ እርሱ እንደሰው ልጆች ከውጭ የሆነ የጦር እቃ የለውም፡፡ ማንነቱ እርሱነቱ ኃያልነት ነው፡፡ ነቢዩ ስለዚህ ህፃን ግን ንጉሥ ሲናገር 

“ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፥ ለሰላሙም ፍፃሜ የለውም። የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል። እያለ ይቀኛል፡፡” ኢሳ.9:6-7 ህጻን ነው ግን አለቅነት በጫንቃው በራሱ በውስጡ በማንነቱ አለ፡፡ ስሙም ድንቅ መካር ኃያል አምላክ ነው፡፡ ኃያልነቱ በስሙ ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ የጦር እቃው አምላክነቱ ማንነቱ ነው፡፡ ይህንን በጥቂቱ የሚረዳው በሄሮድስ ውስጥ የነበረው የዚህ ዓለም ገዢ ሰይጣን ንጉሥ ተወለደ ሲባል በድንጋጤ ተመታ፡፡ ሰራዊት የሌለው ምድራዊ ቤተ መንግሥት ይቅርና የሚወለድበትን ቤት አጥቶ በእንስሳት በረት የተወለደው ህጻኑ ንጉሥ የሄሮድስን  ዙፋን አናጋ፡፡ ገና ከመወለዱ የዚህ የጨለማ ዓለም ገዢ ዙፋኖች ተናወጡ፡፡ ህጻን ሆኖ ቢወለድም ንጉሥነት አምላክነት ኃያልነት ባህርዩ  ነውና በመወለዱ ኢየሩሳሌም ታወከች፡፡ ለርሱ ንጉሥነት ከጊዜ በሁላ የሚገኝ ከላይ የሚደረብ ስልጣንና ዙፋን ሳይሆን ባህርዩ ነው፡፡ ንጉሥ ሊሆን ሳይሆን ንጉሥ የሆነው ነው የተወለደው፡፡ አሁን የእግዚአብሔር ክንድ ተገለጠ፡፡ አለቅነት በጫንቃው ላይ የሆነው የዘላለም ንጉሥ ተወለደ፡፡ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፥ ለሰላሙም ፍፃሜ የለውም። የተባለለት የዳዊት መንግሥት ወራሽ እንሆ ተወለደ፡፡ ዳዊት እረኛና ንጉሥ ነው፡፡ ዳዊት በገዛ ወገኖቹ ሳይቀር የተናቀ በእግዚአብሔር ግን የተመረጠ ንጉሥ ነበረ፡፡  የዳዊት መንግሥት የእግዚአብሔር መንግሥት ናት፡፡ ዳዊት የሚመጣው የክርስቶስ ምሳሌ ነበር፡፡ ከወገቡ ፍሬ በዙፋኑ ላይ እንደሚያስቀምጥ እግዚአብሔር ተስፋን ሰጥቶት ነበር፡፡ ያም ተስፋ የዘላለም ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል የብስራቱን ዜና ለቅድስት ድንግል ማርያም ሲያበስራት “እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም። ብሎአት ነበር፡፡” ሉቃ 1፡32 33 

ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ የዳዊትን መንግሥት የወረሰ ነው፡፡ የዳዊት መንግሥት የእግዚአብሔር ክንድ መገለጫ ናት፡፡ በጦርና በሰረገላ ሳይሆን በእግዚአብሔር ስም የምታሸንፍና የምታድን መንግሥት ናት፡፡ ታናሽ ትመስላለች ግን ታላቅ ናት፡፡ እስራኤልና ፍልስጤኤም ሲዋጉ እስራኤል ያላሸነፉት ወታደር ስላነሰ ወይም የጦር መሳሪያ ስለሌለ ሳይሆን ከሁሉ  ያነሰ ወንጭፍና ድንጋይ የያዘ ብላቴና ስላልመጣ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት በዳዊት ተገለጠች፡፡ የዳዊት ልጅ የሆነው ኢየሱስ ሲወለድ ሲመጣ በሰውና በሰይጣን ሰራዊትና ጦር በተሞላች ዓለም ነው የመጣው እርሱ ግን የሚታይ የጦር እቃ ወይም አጃቢ አልነበረውም፡፡ ይህ ሁሉ ችግር ላለባት ምድር በበረት የተወለደ ህጻን ንጉሥ ተላከላት፡፡ ንጉሱ ከመወለዱ የሲኦል ደጆች ተናወጡ፡፡ የዘላለሙ ንጉሥ በመጀመሪያ የነበረው ቃል የፍጥረት ሁሉ በኩር መልካሙ እረኛ በድንኳን የሚቀመጠው የቤቱ ወራሽና ባለቤት ኋለኛው አዳም መልካሙ እረኛ እንሆ በበረት ተወለደልን፡፡ ይህን ታሪክ የሚያምኑም የማያኑም ያወሩታል ይዘክሩታል፡፡ ለኛ ግን ታሪክ ሳይሆን የኛ ነው፡፡ 

ተወለደ ማለት እና ተወለደልን ማለት ይለያያል፡፡ ተወለደ ማለት እንዲሁ የክስተቱን እውነታ መናገር ሲሆን ተወለደልን ማለት ግን ለኛ ተወለደልን አገኘነው በመወለዱ ተጠቃሚዎች ሆንን ማለት ነው፡፡ የሚከተሉትን ቃላት መልሰን እናንብባቸው፡፡

“ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤” ኢሳ 9፤6 

“በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው፦ እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ።”  ሉቃ 2፤8 12 

ነቢዩ ኢሳይያስ ህጻን ተወልዶልናልና ወንድ ልጅም  ተሰጥቶናልና አለ፡፡ መል አኩም ለእረኞቹ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና አላቸው፡፡ 

ተወልዶአል ሳይሆን ተወልዶልናል፡፡ ተሰጥቶአል ሳይሆን ተሰጥቶናል፡፡ የመጨረሻዎቹ ፊደሎች ከኛ ጋር የሚያያዙት ናቸው፡፡ ለኛ ተወልዶልናል፡፡ ለኛ ተሰጥቶናል፡፡ ስለዚህ እንደ ብዙዎች የክርስቶስን መወለድ ከኛ ተጠቃሚነት ነጥለን እንዲሁ ተወልዶአል በማለት አንዘክረውም፡፡ የመወለዱ ተጠቃሚ ሆነን በመወለዱ ያገኘነውን ክብር ይዘን፡፡ በበረት የተወለደውን በልባችን አስገብተን  ግንባችንን ሳይሆን ልባችንን በብርሃኑ አሸብርቀን በመወለዱ ተወልደን በተዋሕዶ ሚስጢር “ተወልዶልናል ተሰጥቶናል” እያልን እናመሰግነዋለን፡፡

Leave a Comment