Come out of her, my people.

የእግዚአብሔር ፍቅር

“ከሰማይም ሌላ ድምፅ ሰማሁ እንዲህ ሲል፦ ሕዝቤ ሆይ፥ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ ኃጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና፥ እግዚአብሔርም ዓመፃዋን አሰበ።” የዮሐንስ  ራእይ 18:4-5

በመምህር ጸጋ

“ሕዝቤ ሆይ፥ …..ከእርስዋ ዘንድ ውጡ፤”
የሰማይ መልአክ፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ ራእይ 18፤5 

የክርስትና ጅማሬው ተጠርቶ መውጣት ነው፡፡ አባታችን አብርሃም በእግዚአብሔር ተጠርቶ ከባቢሎን ወጣ ወደ ከነዓንም መጣ፡፡ የርሱ ዘር የሆኑት እስራኤላውያን ተጠርተው ከግብጽ ወጡ ወደ ከነዓንም መጡ፡፡ ግብጽና ባቢሎን የዚህች በዚህ ዓለም ገዢ ስር ያለችው የጨለማ ዓለም ምሳሌ ሲሆኑ ከነዓን ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህች ዓለም ገዢ ከዲያብሎስ ስልጣንና ከጨለማው ዓለም ከጠማማው ትውልድ ሊያድነን ራሱን በመስቀል ላይ አሳልፎ ሰጠ፡፡ በስሙ ያመኑትንም ከዚህች ከረከሰች ዓለም አወጣቸው፡፡ እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደላችሁም አላቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ በዚህ ዓለም ሳለ በዓለም ነበረ ከዓለም ግን አልነበረም፡፡ በዚህች በጨለማ በተወረሰች ዓለም እየኖረ እርሱ ግን የዓለም ብርሃን ነበረ፡፡ ዲያብሎስ በርሱ ላይ ስልጣን አልነበረምው ይልቅስ እርሱ ዲያብሎስን ረገጠው አሸነፈው መንግሥቱንም ገለበጠ፡፡ በዚህች ሰይጣን ዙፋኑን በዘረጋባትና የሰዎችን አእምሮ ሁሉ በክፉ ሐሳብ ሞልቶ ፈቃዱን በሚፈጽባት ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በርሱ ያመኑትን ክርስቲያኖች አድኖ የሰማይ መንግሥቱን መሠረተ፡፡ የዳዊት መንግሥት የእግዚአብሔር መንግሥት ነጸብራቅ እንደነበረችው ሁሉ ቤተ ክርስቲያንም የእግዚአብሔር መንግሥት ነጸብራቅ ናት፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ወይም ምእመናን ሁሉ የእግዚአብሔር መንግሥት ዜጎች ናቸው፡፡ በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ የተመሠረተችው ቤተ ክርስቲያን እንደ አባቶቻችን እንደ ሐዋርያት ከዚህ ዓለም ያይደለች ነገር ግን ብርሃን ለመሆን በዓለም ያለች ናት፡፡ አባቶቻችን ሐዋርያት እንደዚህ ዘመን መምህራን ፖለቲከኞችና ምድራዊያን አልነበሩም፡፡ ይልቅስ ሰማያዊትዋን ቤተ ክርስቲያን እያገለገሉ ለዚህች ምድር ብርሃን የሚሰጡ ነበሩ፡፡ አሁንም የነርሱን ፈለግ የምትከተለዋ እውነተኛዋ የክርስቶስ አካል ቤተ ክርስቲያን በዓለም ናት እንጂ ከዓለም አይደለችም፡፡ እውነተኛዎቹ ምእመንና ትክክለኛዎቹ ክርስቲያኖች በዓለም ናቸው እንጂ ከዓለም አይደሉም፡፡ በዓለም ያለው የሰይጣን ሲስተም በሰይጣን ስልጣን ስር የሚንቀሳቀሰው የፖለቲከኞች ምህዋር በነርሱ ላይ አይሰራም፡፡ ክርስቲያን የሚመላለሰው በተወለደበት መንፈስ ነው፡፡ “ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው።” የዮሐንስ ወንጌል 3፤8 ከዓለም መውጣት ማለት ከከተማ መውጣት ከሥልጣኔ መራቅ ማለት አይደለም፡፡ ዓለምን ከሚገዛው ከዓለም መንፈስ ዓለም ከትምሽከረከርበት የጨለማው ስር ዓት የእሽክርክሪት ዛቢያ መውጣት ማለት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ማለት ክርስቲያኖች የሚመላለሱት በተወለዱበት በእግዚአብሔር መንፈስ ነው፡፡ እናት ጸንሳ መውለድ ብቻ ሳይሆን የወለደችውን አጥብታ የምታሳድግበት መለኮታዊ መግቦት ተሰጥቶአታል፡፡ መንፈስ ቅዱስም አንድን ክርስቲያን ከወለደ በኋላ ትቶት አይሄድም፡፡ ይመግበዋል ያሳድገዋል ይመራዋል፡፡ ፍጥረታዊው አካላችን ከተቆነጠርንበት አፈር ምግቡን እንደሚያገኝ ውስጣዊ ማንነታችንም ከተወለደበት መንፈስ ምግቡን እና የአካሄድ ስርዓቱን ያገኛል፡፡ ጌታችንንና መድኃኒታችን ለኒቆዲሞስ ስለዳግም ልደት ሚስጢር ከገለጸለት በኋላ ወዲያኑ ስለምልልስ ነው የነገረው፡፡ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው   ከመንፈስ የተወለድነው ከዚህች ዓለም የጨለማ ሥርኣት ወጥተን ወደ ብርሃን መንግሥት ለመግባት ነው፡፡ የተወለድንበት መንፈስ የራሱ መንገድ አለው፡፡ ስለዚህ የአንድ ክርስቲያን የመጀመሪያ እርምጃ ከዓለም ሲስተም መውጣት ነው፡፡ ከዓለም ምህዋር ሳንወጣ ክርስቲያን ልንሆንና እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መመላለስ መንፈሱ ወደምሄድበት መሄድ አንችልም፡፡ ለአንዳንዶቻችሁ ይህ አዲስ ነገር ሊመስላችሁ ይችል ይሆናል፡፡ ይህ ግን በብዙ ልብ ወለድ አስተምህሮዎች አቧራ ተዳፍኖብን ያላየነው እውነተኛው የአባቶቻችን የሐዋርያት ወንጌል ነው፡፡ ስለዚህ ከሁሉ አስቀድማችሁ ከባቢሎን ውጡ፡፡ ከግብጽ ውጡ፡፡ አሁን ባቢሎንና ግብጽ የምትኖሩበት በዓመጻ በኃጢአት በግፍ የተሞላው ጠማማ ማህበረሰብ ነው፡፡ የምትወጡትም በአካሄድ በአስተሳስብ በማንነት ለውጥ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንገድ አሁን የዚህች ዓለም መንግሥታትና የምንኖርበት ማኅበረሰብ ከሚመላለስበት መንገድ የተየለየ ሰማያዊ መንገድ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅ ናት ሰላም ናት ፍቅር ናት፡፡ በእውነተኛይቱ የክርስቶስ አካል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታየው ይህ ነው፡፡ የመውጣታችንን አስፈላጊነት የሚያሳየንን አንድ ምሳሌ እንመልከት፡፡

“ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ {One way}   እየነዳችሁ መሆኑን ብታውቁና መኪናውን ሳታዞሩ ራሳችሁን ብቻ ወንበሩ ላይ ፊታችሁን ወደ ኋላ አዙራችሁ ብትቀመጡ መንገድ አልቀየራችሁም ከሚመጣው አደጋም አትድኑም፡፡ 

ወደ ምእራብ እየበረረ ያለ አውርፕላን ውስጥ ወደ ምስራቅ ዞራችሁ ብትራመዱ እየሄዳችሁ አይደለም፡፡ ወደሁላ የተራመዳችሁ ቢመስላችሁም አውሮፕላኑ ወደሚሄድበት ነው እየሄዳችሁ ያላችሁት፡፡ በትክክል ወደፈለጋችሁት ወደ ምስራቅ አቅጣጫ መሄድ ከፈለጋችሁ በመጀመሪያ አውሮፕላኑ አርፎ ከአውሮፕላኑ ወጥታችሁ በራሳችሁ መራመድ አለባችሁ፡፡ ከአውሮፕላኑ ሳትወጡ እዚያው እየበረረ ባለው አውሮፕላን ውስጥ ወደ ፊትም ወደሁላም ብትሄዱ ግን የፍጥነቱም ሆነ የአቅጣጫው ህግ የሚወሰነው በአውሮፕላኑ እንጂ በእናንተ አይደለም፡፡ ውስጥ ሆናችሁ የምትራመዱት የእናንተ እርምጃ አይደለም፡፡  ትራመዳላችሁ ግን እየሄዳችሁ አይደለም፡፡ እንደዚሁም ወደ ጥፋት እየፈጠነች ባለች ዓለም ውስጥ ተሳፍራችሁ ወደ ኋላም ወደፊትም ብትሄዱ መልካም ነገር ለማድረግም ብትሞኩሩ መጨረሻችሁ ግን እርስዋ የገባችበት ጉድጓድ ነው፡፡

“ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ {One way}   እየነዳችሁ መሆኑን ብታውቁና መኪናውን ሳታዞሩ ራሳችሁን ብቻ ወንበሩ ላይ ፊታችሁን ወደ ኋላ አዙራችሁ ብትቀመጡ መንገድ አልቀየራችሁም ከሚመጣው አደጋም አትድኑም፡፡ 

ወደ ምእራብ እየበረረ ያለ አውርፕላን ውስጥ ወደ ምስራቅ ዞራችሁ ብትራመዱ እየሄዳችሁ አይደለም፡፡ ወደሁላ የተራመዳችሁ ቢመስላችሁም አውሮፕላኑ ወደሚሄድበት ነው እየሄዳችሁ ያላችሁት፡፡ በትክክል ወደፈለጋችሁት ወደ ምስራቅ አቅጣጫ መሄድ ከፈለጋችሁ በመጀመሪያ አውሮፕላኑ አርፎ ከአውሮፕላኑ ወጥታችሁ በራሳችሁ መራመድ አለባችሁ፡፡ ከአውሮፕላኑ ሳትወጡ እዚያው እየበረረ ባለው አውሮፕላን ውስጥ ወደ ፊትም ወደሁላም ብትሄዱ ግን የፍጥነቱም ሆነ የአቅጣጫው ህግ የሚወሰነው በአውሮፕላኑ እንጂ በእናንተ አይደለም፡፡ ውስጥ ሆናችሁ የምትራመዱት የእናንተ እርምጃ አይደለም፡፡  ትራመዳላችሁ ግን እየሄዳችሁ አይደለም፡፡ እንደዚሁም ወደ ጥፋት እየፈጠነች ባለች ዓለም ውስጥ ተሳፍራችሁ ወደ ኋላም ወደፊትም ብትሄዱ መልካም ነገር ለማድረግም ብትሞኩሩ መጨረሻችሁ ግን እርስዋ የገባችበት ጉድጓድ ነው፡፡  ከሁሉ አስቀድሞ ከባቢሎን ውጡ ፡፡ በዓለም ውስጥ ሆነን ምንም ብናደርግ ትክክል አንሆንም፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ጥሪ ሰው  ሁሉ ከዚህች ከምትጠፋው ባቢሎን ከሆነችው የጨለማ ዓለም ወጥቶ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ራስና ንጉሥ ወደሆነላት ወደ ቤተ ክርስቲያን ለርስቱ ወደተለየው ከጨለማ ወደ ሚደነቅ ብርሃን ወደገባው ማኅበረሰብ እንዲገባ ነው፡፡”  በእግዚአብሔር ዓይን ነገሮች ሁሉ በሁለት የተከፈሉ ናቸው፡፡ ብርሃንና ጨለማ ክርስቶስና ቤልሆር የሚያምኑና የማያምኑ የክርስቶስ የብርሃን መንግሥትና የሰይጣን የጨለማ መንግሥትና ቤተ ክርስቲያንና ዓለም በጎችና ፍየሎች  ናቸው፡፡ 

ከዚህም ከዚያም ያልሆነ ከሰይጣን ወይም ከእግዚአብሔር ያልሆነ ከብርሃን ወይም ከጨለማ ያልሆነ ሌላ ሶስተኛ አካል የለም፡፡ ስለዚህ ሁላችንም እያንዳንዳችን ከነዚህ ሁለት ክፍሎች በአንዱ ውስጥ ነው የምንገኘው፡፡

Come out of her, my people

ከዚህ በታች ያለውን የወንጌል ድምጽ እንዲሰሙ በታላቅ ፍቅር እንጋብዝዎታለን፡፡

ጨለማው የዲያብሎስ መንግሥት በክርስቶስ የማያምኑ  በአጠቃላይ ይህች ዓለም በቅርቡ የምትጠፋ ሲሆን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ቤተ ክርስቲያን የሆኑና በፍቅሩ ልጅ መንግሥት ውስጥ ያሉት ደግሞ በእግዚአብሔር መንግሥት ለዘለዓለም ይኖራሉ፡፡  ስለዚህ ከዓለም የሆነ ሁሉ ወይም ከዓለም ጋር የወገነ ሁሉ የክርስቶስ ጠላት ነው፡፡ ምክንያቱም ዓለምና በውስጥዋ ያለው የሰይጣን ጨለማ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ናቸውና፡፡  ዓለም ሲባል ግን ብዙዎቻችን እንደምናስበው ጭፈራ ቤቱ መጠጥ ቤቱ ወይም ኃጢአት ይደረግባቸዋል የሚባሉ ቦታዎች ማለት አይደለም፡፡ ዓለም በሚለው ቃል ውስጥ የዚህ ዓለም የትምህርት የፍስልስፍና የፖለቲካ የመንግሥት ታላላቅ የሃይማኖት ድርጅቶችንም ያጠቃልላል፡፡ ዓለም ጉደኛ ናት፡፡ ሌላው ቀርቶ ብዙ የተከበሩና የታወቁ የእምነት ድርጅቶችም አሉአት፡፡ አንዳንድ የዋሆች የእምነት ድርጅት ሲባል ከዓለም ውጭ የሆነ መንፈሳዊ ቦታ ወይም ተቋም ይመስላቸዋል ነገር ግን በእግዚአብሔር ዓይን ክርስቶስ ራስ ያልሆነለት መንፈሳዊ አካል የለም፡፡ ብቸኛዋና ክርስቶስ ራስ የሆነላት ደግሞ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ትባላለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል ስርወ ቃል ኤክሌሺያ ἐκκλησία ek-kla-se’-ä } የሚለው  የግሪክ ቃል ሲሆን ለአንድ ለተለየ ዓላማ ከህዝቡ ተለይተው ተጠርተው የወጡ ማለት ነው፡፡ ከክርስቶስ ልደት ከአምስት መቶ ዘጠና አራት ዓመት ጀምሮ ግሪካውያን ራሳቸውን ለማስተዳደር ይጠቀሙበት የነበረ ከህዝብ የተመረጡ ሰዎች ስብስብ ስም ሲሆን እነዚህ ሰዎች ከህዝቡ ተመርጠውና ተለይተው ህዝብን ለመምራት የሚሰበሰቡ ነበሩ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ጴጥሮስ በሰጠው ስልጣን በዚህች ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ የገሃነም ደጆችም አይችሏትም” ብሎ ሲናገር ህዝቡ የሚያውቀውን የኤክሌሺያ ስያሜ በመጠቀም የኔ የሆነች ከሰማይ የሆነ ስልጣንና ውክልና ያላት ቤተ ክርስቲያኔን እመሰርታለሁ ማለቱ ነበር፡፡ በግሪክ ከህዝቡ ተመርጠው የሚሰበሰቡት ህዝቡን ለመምራትና ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ ስልጣን እንደነበራቸው ሁሉ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በዚህ ዓለም ገዢ በሰይጣን ላይ ስልጣን የተሰጣትና የዚህን ዓለም ገዢ የዲያብሎስ ስልጣን በክርስቶስ ወንጌል ብርሃን ኃይል ለማሸነፍ የተሰበሰበች የአማንያን ጉባኤ ናት፡፡ {ሐዋ 26፤17-18 1.ጴጥ 2፤9 } ለዚህም ነው በዚህች ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ ካለ በኋላ ስልጣን ያላትና የርሱን ስልጣን የምትገልጥ መሆንዋን ለማሳየት “የገሃነም ደጆችም አይችሏትም” በማለት የተናገረው፡፡  ወደዚህች የክርስቶስ አካል የሚገቡት ደግሞ በክርስቶስ አምነው ከዚህ ከጨለማው ዓለም ወጥተው በክርስቶስ ደም  ነጽተው ለድሮው አሮጌ ማንነታቸው ዘራቸውና ቋንቋቸው ሞተው በዳግም ልደት አዲሱን ሰው የለበሱ ብቻ ናቸው፡፡ በመሆኑም ከሚመጣው ጥፋት እና ቁጣ ለመዳን የወንጌሉን ጥሪ ሰምተን የሰው ልጆች ብርሃን ወደሆነው ወደ ክርስቶስ እንድንገባና የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ብልቶች እንድንሆን እግዚአብሔር ሁላችንን እየጠራን ነው፡፡  

እግዚአብሔር ከምትጠፋው ባቢሎናዊት ዓለም እንድንወጣ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም እንድንገባ በወንጌሉ እየጠራን ያለበት ምክንያት በበደላችንና በኃጢአታችን ምክንያት ከርሱ ወጥተንና ርቀን ስለነበረ ነው፡፡ ስለዚህ የየእያንዳንዳችን የመጀመሪያ እርምጃ የወንጌሉን ጥሪ ሰምተን ከጠፋንበት መመለስ ነው፡፡ የሚያዝነው ግን ሰዎች ከጠፉበት ስፍራ ሳይመለሱ ከወደቀው ማንነታቸው ሳይድን ከዓለም ሳይወጡ በዚያው ባላችሁበት መዳንና ክርስቲያን መሆን ትችላላችሁ በማለት ህዝቡን በሚያስቱ የሐይማኖት አስተማሪዎች ብዙዎች መታለላቸውና እንደ ቃየን በአንድ እጃቸው መስዋእት በሌላው እጃቸው ወንድማቸውን የሚገድሉበትን ድንጋይ ወይም መሳሪያ የያዙ ክርስቲያን በሚል ስም የሚጠሩ ብዙዎች መኖራቸው ነው፡፡ እውነታው ግን ከዓለም ሳንወጣ ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባት አለመቻላቻን ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱና እግዚአብሔር በየዘመናቱ ሰዎችን ውጡ እያለ ካሉበት እያስወጣ ወደራሱ ያመጣበት የታሪክ ሂደት ቀጥለን እንመልከት፡፡ 

 በመጀመሪያ ሰው ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብና ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመግባት ካለበት ዓለም መውጣት ያለበት አስቀድሞ ከእግዚአብሔር ወጥቶ ወደ ዓለም ገብቶ ስለነበረ ነው፡፡ 

ሰው  ከእግዚአብሔር ወጥቶ ሰይጣን ወደሚገዛው የዓለም ሥርአት የገባው ደግሞ አትብላ የተባለውን ዛፍ በልቶ በሞተው የሰው ልጆች ሁሉ አባት በሆነው በአዳም ምክንያት ነው፡፡ አዳም ያንን ዛፍ ከበላ በሁላ የሆነውን የእግዚአብሔር ቃል ሲናገር እንዲህ ይላል፡፡ 

 

“ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ ከዔድን ገነት አስወጣው፥ የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድ። አዳምንም አስወጣው፥ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔድን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ።” ኦሪት ዘፍጥረት 3፤23-24

አዳም እግዚአብሔር አትብላ ያለውን ዛፍ በልቶ በመሞቱና ከሰይጣን ጋር በማበሩ በምቾትና በክብር ከእግዚአብሔር ጋር ሲኖርባት ከነበረው ከኤደን ገነት ወጣ ፡፡ ወጥቶም ከገነት ብዙም በማይርቅ ስፍራ መኖር ጀመረ፡፡ ከዚያ በኋላ የበኩር ልጁ ቃየን እንደገና ወንድሙን በመግደል ኃጢአቱን አበዛ፡፡ በዚህን ጊዜ ከስፍራ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ህልውና ወጣ  

“ቃየንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፤ ከዔድንም ወደ ምሥራቅ በኖድ ምድር ተቀመጠ።” ዘፍ 4፡16 

እንግዲህ በዚህ ዓይነት ሁኔታ የቀጠለው የሰው ልጆች የውድቀት ታሪክ ቀጠለ፡፡ የሰው ልጆች የበለጠ ዓመጸኞች እየሆኑ በሄዱ ቁጥር እግዚአብሔር እርሱን በመፍራት ከኃጢአት ለመራቅ የሚወዱትን ጥቂት ሰዎች ወደራሱ ይጠራ ጀመር፡፡ ከነዚህም አንዱ ነቢዩ ሄኖክ ሲሆን በዘመኑ ከነበረው አመጸኛ ትውልድ ተለይቶ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ፡፡ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር ስለወሰደው አልተገኘም፡፡ ከዚያም የርሱ የልጅ ልጅ የሆነው ኖህ በዘመኑ ከነበረው ዓመጸኛ ትውልድ ተለይቶ ለእግዚአብሔር ታዘዘ፡፡ መርከብንም በመሥራት በዘመኑ ከመጣው የእግዚአብሔር ፍርድ ራሱንና ቤተሰቡን አዳነ፡፡ ከዚያም በሁላ እግዚአብሔር አብርሃንም ከዑር ጠራ፡፡ አብርሃም ዑር በምትባል ብዙ ጣኦታት በሚመለኩባት ከተማ የሚኖር የመሴጦምያ ሰው ነበር፡፡ አንድ ቀንም እግዚአብሔር ተገለጠለትና እንዲህ አለው፡፡ 

“እግዚአብሔርም አብራምን አለው፦ ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ። ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፥ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም አከብረዋለሁ፤ ለበረከትም ሁን፤ የሚባርኩህንም እባርካለሁ፥ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ።” ኦሪት ዘፍጥረት 12:1-3

አብርሃም በአካሄድ ብቻ ሳይሆን በአካልም ከተወለደባትና ካደገባት ምድር ወጥቶ ዘመዶቹን ሁሉ ትቶ እግዚአብሔር ወደሚያሳየው ምድር እንዲሄድ ነው የተጠራው፡፡ አብርሃምም በእምነት እግዚአብሔርን ታዘዘና ወደ ከነዓን መጣ፡፡ “ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ።” የሚለው ቃል ልብ ብላችሁ አንብቡት፡፡ አብርሃም ለእግዚአብሔር ለመሆን ወይም ወደ እግዚአብሔር ለመምጣት መውጣትና መተው የነበረበት ዓለምና ማኅበረሰብ ነበረ፡፡ ተወልዶ ያደገባትን ምድር ባህሉን ወጉን የቅርብ ዘመዶቹን ሁሉ ትቶ ነው የወጣው፡፡ አብርሃም እብራዊ ነው፡፡ እብራዊ ማለት ደግሞ ወንዝ ተሻጋሪ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ወንዝ ተሻግሮ ወደ እግዚአብሔር ርስት የመጣ ሲሆን ወንዙም በርሱና በድሮ ማንነቱ መካከል የተቀመጠ መስመር ነው፡፡ ከዚህም ከረጅም ጊዜ በኋላ የርሱ ዘር የሆኑት እስራኤላውያን እግዚአብሔር ለአባታቸው ለአብርሃም ርስት አድርጎ ከሰጠው ምድር ተለይተው ወደ ግብጽ ምድር ገቡ፡፡ ከአራት መቶ ሰላሳ የባርነት ዘመን በሁላ እግዚአብሔር መጣና እነርሱም እንዲወጡ በሙሴ በኩል እንዲህ ብሎ ጠራቸው፡፡ 

 

“እግዚአብሔርም አለ፦ በግብፅ ያለውን የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ፥ ከአስገባሪዎቻቸውም የተነሣ ጩኸታቸውን ሰማሁ፤ ሥቃያቸውንም አውቄአለሁ፤

ከግብፃውያንም እጅ አድናቸው ዘንድ፥ ከዚያችም አገር ወተትና ማር ወደምታፈስሰው አገር ወደ ሰፊይቱና ወደ መልካሚቱ አገር ወደ ከነዓናውያንም ወደ ኬጢያውያንም ወደ አሞራውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ኢያቡሳውያንም ስፍራ አወጣቸው ዘንድ ወረድሁ።” ኦሪት ዘጸአት 3፤7-8 

አሁንም “አወጣቸው ዘንድ ወረድሁ።” የሚለውን ቃል ልብ በሉ፡፡ ሙሴና አሮንም ወደ ፈርኦን በመግባት የእግዚአብሔርን መል እክት እንዲህ ሲሉ አደረሱ፡፡ 

“ከዚህም በኋላ ሙሴና አሮን መጥተው ፈርዖንን እንዲህ አሉት፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በምድረ በዳ በዓል ያደርግልኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።” ኦሪት ዘጸአት 5:1

 

የግብጽ ንጉስ ፈርኦን እስራኤልን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባይሆንም እግዚአብሔር ግን በብዙ ድንቅና ተአምራት ህዝቡን ከግብጽ ምድር አውጥቶ ከነዓን አስገባቸው፡፡ በከነዓንም መንግሥትና ካህናት አደረጋቸው፡፡ የክርስቶስ መንግሥት ምሳሌ የሆነችውን የዳዊትንና የሰሎሞንን መንግሥት ሰጣቸው፡፡ አዳም ከገነት እንደወጣው ሁሉ እስራኤላውያን በተለያየ ጊዜ እግዚአብሔርን እየበደሉ ከተስፋቱ ምድር እየወጡ ወደ አሶር እና ወደ ባቢሎን የተማረኩ ቢሆንም እግዚአብሔር መልሶ ነጻ እያወጣቸው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ድረስ በርስታቸው ቆዩ፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ እስራኤል በሮማውያን ቅኝ ግዛት ስር የነበረች እና ከድሮ ክብርዋ በወረደ ሁኔታ የነበረች ቢሆንም ያ ግን ለሰው ልጆች ሁሉ የተሰጠው ተስፋ ጌታችንና መድኃኒታችን እንዳይወለድ አላገደውም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣውም የሰውን ልጆች ሁሉ ከወደቁበት ኃጢአትና ሞት አድኖ ከጨለማው የዲያብሎስ መንግሥት አውጥቶ የራሱ ሊያደርጋቸው ነው፡፡ ከክርስቶስ መወለድ በፊት የነበረው የእግዚአብሔር ጥሪ እና ማስወጣት በተወሰኑ ሰዎች ላይ ያነጣጠረና መውጣቱም ከግብጽና ከባቢሎን ሲሆን በኢየሱስ ክርስቶስ የተደረገው ነጻ የማስወጣት ሥራ ግን ሁሉንም ሰው የሚመለከትና የአዳም ዘሮች ሁሉ ከሞት ወጥተው ከዲያብሎስ የጨለማ መንግሥት ድነው ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት እንዲገቡ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ እግዚአብሔር የዳዊትን መንግሥት እንደሚሰጠው ተነግሮአል፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛው ዳዊት ነው፡፡ ምሳሌ የሆነውና የድሮው ንጉሥ ዳዊት የነገሠው በእስራኤል ምድርና ህዝብ ላይ ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በዓለም ሁሉ ላይ ንጉሥና ጌታ ነው፡፡ ነገር ግን የንጉሥነቱና የጌትነቱ ተጠቃሚ የሚሆኑት በመስቀል ሥራው ቤዛነት ድነው በዳግም ልደት ከርሱ የተወለዱና ሰማያዊ ዜጎች የሆኑት ምእመናን ብቻ ናቸው፡፡ አዎ ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክነቱ የዓለም ሁሉ ገዢ ነው፡፡ ሆኖም በተለየ ሁኔታ ጌታ አዳኝ ንጉሥና ራስ የሆነለት ማሕበረሰብ አለ ይኸው ተጠርተው የወጡ የተባሉት ስብስብ ብዙ ብልቶች አንድ አካል የሆነችው ቅድስት ቤተክርስቲያን ስትሆን እርስዋ አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት፡፡  ጌታችንና መድኃኒታችን ለቅዱስ ጴጥሮስ ስለዚህች ቤተ ክርስቲያን መሰራትና ምንነት ሲናገር 

“ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ። እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም። የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።” ማቴ. 16:17-19 

 ስንጀምር እንደተመለከትነው ቤተ ክርስቲያን ወይም ኤክሌሺያ ማለት ተጠርተው የወጡ ማለት ነው፡፡ ከሆነ ከየት ነው ተጠርተው የወጡት? ይህስ መውጣት ምን ማለት ነው የሚለውን ጥያቄ እንመልስ፡፡  ለዚህም ራሱ ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተናገረው እንመልከት፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ጊዜ በተቃረበበት ወቅት ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፡፡ 

“እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ይህን አዛችኋለሁ። ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ። ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል። ባርያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ። እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው እንደ ሆኑ ቃላችሁን ደግሞ ይጠብቃሉ። ዳሩ ግን የላከኝን አያውቁምና ይህን ሁሉ ስለ ስሜ ያደርጉባችኋል።” ዮሐ 15፡17-21

 

“ከዚህም በኋላ በዓለም አይደለሁም፥ እነርሱም በዓለም ናቸው፥ እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ። ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው። ከእነርሱ ጋር በዓለም ሳለሁ የሰጠኸኝን በስምህ እኔ እጠብቃቸው ነበር፤ ጠበቅኋቸውም መጽሐፉም እንዲፈጸም ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ ማንም አልጠፋም። አሁንም ወደ አንተ እመጣለሁ፤ በእነርሱም ዘንድ ደስታዬ የተፈጸመ እንዲሆንላቸው ይህን በዓለም እናገራለሁ። እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔም ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው። ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም። እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም። በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው። ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ እንዲሁ እኔ ወደ ዓለም ላክኋቸው፤ እነርሱም ደግሞ በእውነት የተቀደሱ እንዲሆኑ እኔ ራሴን ስለ እነርሱ እቀድሳለሁ።” ዮሐ 17፡11-19

በነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በግልጽ እንደምናየው የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት ወይም ቤተ ክርስቲያን ከዓለም ጋር አትቆጠርም የዓለምም ክፍል አይደለችም፡፡ ክርስቶስም ራሱን አሳልፎ የሰጠው ቤተ ክርስቲያንን ከዓለም ለማስወጣትና ለመለየት መንግሥቱንም ለመሥረት ነው፡፡ ይህንን ያደረገው ደግሞ ራሱን ለሰው ልጆች በመግለጥ እና በመስቀልም ላይ ነፍሱን ቤዛ አድርጎ በመስጠት ነው፡፡ ሁኔታው ከርሱ ከራሱ ይጀምራል፡፡ እርሱ ከዚህ ዓለም አይደለም፡፡ ዓለም ጨልማ ናት እርሱ ግን ብርሃን ነው፡፡ ዓለም በጨለማው ስልጣን ስር ናት እርሱ ግን ከእውነተኛ ብርሃን የተገኘ እውነተኛ ብርሃን ነው፡፡ ብርሃን ሆኖ መጥቶ ጨለማዋንና የጨለማ ሥራዋን ሳልጋለጠባት ዓለም በእጅጉ ትጠለዋለች፡፡ ቤተ መንግሥቱ ቤተ ክህነቱም የርሱ ጠላቶች ነበሩ፡፡ ጲላጦስና ሄሮድስ ብቻ ሳይሆኑ የመቅደሱ ካህናት አሳደውታል፡፡ እንዲያውም ጲላጦስ ሊያድነው ሲከራከርለት ስቀለው ስቀለው እያሉ ያስገደዱት የካህናቱ አለቆች ነበሩ፡፡ ብዙ ሰዎች ዓለም ክርስቶስን እንደምትጠላና ክርስቶስን እንደሰቀለች ሲነገር ይህን ያደረገችው በቤተ ክህነትዋ በኩል እንደሆነ ይረሳሉ፡፡ ዓለም የቤተ ክህነት ቅርንጫፍ አላት፡፡ ዓለም ማለት አንድ ክንፍዋ ፖለቲካ ሌላ ክንፍዋ ሰው ሰራሽ ሐይማኖታዊ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ዓለም ይህንን የሰውን ልጆች ሁሉ ለማዳን የመጣውን ጌታ በመስቀል ላይ ሰቅላ ገድላዋለች፡፡ በርሱ የደረሰው ይህ  መጠላትና መከራ በደቀ መዛሙርቱም ደርሶአል፡፡ ይህም የሆነው ደቀመዛሙርቱ በስሙ በማመናቸው ምክንያት ከእግዚአብሔር ተወልደው የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆኑ ነው፡፡ ይህም ከዓለም የተለዩበት መለኮታዊ ሚስጢር ነው፡፡ ስለዚህ እኔን ጠልተውኝ አሳደውኝ እንደሆነ እናንተንም ያሳድዷችኋል ይገድሏችኋል አላቸው፡፡  በዚህ ሁሉ የምናየው እውነተኞቹን ምእመናን የያዘችው የክርስቶስ አካል ቤተ ክርስቲያን አሁን በዚህ ዘመን የፖለቲከኞች ቀኝ እጅ እንደሆኑት አብያተ ክርስቲያናት ከዓለም ጋር የተደባለቀች አይደለችም፡፡ እውነተኛዋን ቤተ ክርስቲያን ከፖለቲከኞች ጋር ቆማ መግለጫ ስትሰጥም ሆነ በምንም ዓይነት መንገድ ከነርሱ ጋር ስትቆጠር አታገኟትም፡፡ እውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያን የሰማዩን መንግሥት በምድር ላይ የምታንጸባርቅ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ናት፡፡ ማንኛውም ሰው ከዓለም ሳይወጣ በዓለም በቅሎ የነበረው ስሩ ሳይነቀል ወደ አካሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ሊተከል አይችልም፡፡ በቤተ ክርስቲያን ለመተከል ከዓለም መነቀል ይጠይቃል፡፡  ነገር ግን አንዳንድ ህጻናት ክርስቲያኖች ይህ ሳይገባቸው ከዚህች ከረከሰች ዓለም ጋር ለመደባለቅ ሲሞክሩ ይታያል፡፡ እንዲህ ዓይነቶችን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲመክራቸው እንዲህ ይላል

“ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው? እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና እንዲሁም እግዚአብሔር ተናገረ እንዲህ ሲል፦ በእነርሱ እኖራለሁ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፥ አምላካቸውም እሆናለሁ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ። ስለዚህም ጌታ፦ ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኵስንም አትንኩ ይላል፤ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ፦ እኔም እቀበላችኋለሁ፥ ለእናንተም አባት እሆናለሁ እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ ይላል።”  2 ቆሮ 6:14-18 

ይገርማል  እውነተኛ ክርስቲያን ከማያምኑ ሰዎች ጋር ያለውን ልዩነትና ርቀት ብርሃን ከጨለማ ጋር ቤልሆር ከክርስቶስ ጋር ያለውን ያህል ነው እያላቸው ነው፡፡ ወገኖቼ ይህን ያህል ከዓለም ርቋችሁል? ወይስ እንደ ኬፋ በሊቀ ካህናቱ ግቢ እሳት እየሞቃችሁ ነው? የምትሞቁት እሳት ሳይፈጃችሁ ቶሎ ብላችሁ ከገዳዮች ማህበር ከዚህች ዓለም ጉባኤ ውጡ፡፡ እናንተ ተጠርታችሁ የወጣችሁ ለክርስቶስም የተለያችሁ ናችሁ፡፡ 

ቅዱስ ጴጥሮስም የሚለንን ተመልከቱ፡፡  

“እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤ እናንተ ቀድሞ ወገን አልነበራችሁም አሁን ግን የእግዚአብሔር ወገን ናችሁ፤ እናንተ ምሕረት ያገኛችሁ አልነበራችሁም አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል።” ይላል፡፡ 1 ጴጥ 2:9-10 

ይገርማል እጅግም ይደንቃል፡፡ የተመረጠ ትውልድ የንጉሥ ካህናት ቅዱስ ሕዝብ ለርሱ የተለየ ወገን፡፡ ከማን የተለየ? በጨለማ ከሚርመሰው ትውልድ የተለየ ወገን ድሮ በጨለማ የነበረ አሁን ግ ን በብርሃንና ብርሃን የሆነ ትውልድ፡፡ 

ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ማለት ወይም ክርስትና ማለት ከዚህች ዓለም ጨለማ ስርዓት ጨርሶ የወጣ ማለት ነው፡፡ በዚያው በዓለማዊው ስርአተ ዑደት ሆነን ክርስቲያን መሆን አንችልም፡፡ ብዙዎች በዚያው በዓለም የስርዐት ዛቢያ እየተሽከረከሩና እየተጓዙ፤ በዓለም መርከብ ተሳፍረው አንዳንድ መልካም ነገሮች በማድረግ የሚድኑ ወይም ክርስትናቸውን የሚገልጹ ይመስላቸዋል፡፡ ማስተዋል ያለባችሁ ነገር  ከባዱ ስህተት በየዕለቱ የምትሰሩት ኃጢአት ወይም ጉድለት ሳይሆን የምትኖሩባት ማህበርተኛ የሆናችሁባት ዓለም ራስዋ ስህተት ናት፡፡ ስህተት ከሆነችው ዓለም ሳንወጣ ትክክል  መሆን አንችልም፡፡ ዓለም ውስጥ ባቢሎን ውስጥም ብትሆኑ በቻላችሁት መጠን መልካም ነገር አድርጉ ጹሙ ጸልዩ ሳይሆን የተባልነው ከርስዋ ዘንድ ውጡ ነው የተባልነው፡፡ ከተሳሳተው ኣለም ሳንወጣ ትክክለኛ መሆን አትችይም፡፡ 

በዓለም ሲስተም ውስጥ ሆኖ በዓለም የሞተር እሽክርክሪት ውስጥ እየኖሩ አንዳንድ መልካም ስነ ምግባሮችን ለማድረግ በመሞከር መዳን የለም፡፡ ይህ ዜሮን በዜሮ ማባዛት ነው፡፡ መጀመሪያውኑ የሚባዛ ቁጥር ከሌለን ብዙ ዜሮዎችን በማባዛት አንድ ቁጥርን አናመጣም፡፡ ዜሮን ስናባዛ ብንውል ብዙ ዜሮዎችን ነው የምናመርተው፡፡ ከዓለም ሳይወጡ ክርስቲያን ለመሆን መሞክር ማለት ያ ነው፡፡ ችግሩ የሰው ልጅ በተሳሳተ ማንነትና ዓለም ውስጥ መሆኑ ነው፡፡ በጨለማው ዓለም ውስጥ ሆኖ ምንም ቢያደርግ ውጤት የለውም፡፡ የሞተ ሰው ምንም ቢያደርግ የሞተ ሥራ ነው የሚያመርተው፡፡ ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ {One way}   እየነዳችሁ መሆኑን ብታውቁና መኪናውን ሳታዞሩ ራሳችሁን ብቻ ወንበሩ ላይ ፊታችሁን ወደ ኋላ አዙራችሁ ብትቀመጡ መንገድ አልቀየራችሁም ከሚመጣው አደጋም አትድኑም፡፡ 

ወደ ምእራብ እየበረረ ያለ አውርፕላን ውስጥ ወደ ምስራቅ ዞራችሁ ብትራመዱ እየሄዳችሁ አይደለም፡፡ ወደሁላ የተራመዳችሁ ቢመስላችሁም አውሮፕላኑ ወደሚሄድበት ነው እየሄዳችሁ ያላችሁት፡፡ በትክክል ወደፈለጋችሁት ወደ ምስራቅ አቅጣጫ መሄድ ከፈለጋችሁ በመጀመሪያ አውሮፕላኑ አርፎ ከአውሮፕላኑ ወጥታችሁ በራሳችሁ መራመድ አለባችሁ፡፡ ከአውሮፕላኑ ሳትወጡ እዚያው እየበረረ ባለው አውሮፕላን ውስጥ ወደ ፊትም ወደሁላም ብትሄዱ ግን የፍጥነቱም ሆነ የአቅጣጫው ህግ የሚወሰነው በአውሮፕላኑ እንጂ በእናንተ አይደለም፡፡ ውስጥ ሆናችሁ የምትራመዱት የእናንተ እርምጃ አይደለም፡፡  ትራመዳላችሁ ግን እየሄዳችሁ አይደለም፡፡ እንደዚሁም ወደ ጥፋት እየፈጠነች ባለች ዓለም ውስጥ ተሳፍራችሁ ወደ ኋላም ወደፊትም ብትሄዱ መልካም ነገር ለማድረግም ብትሞኩሩ መጨረሻችሁ ግን እርስዋ የገባችበት ጉድጓድ ነው፡፡  ከሁሉ አስቀድሞ ከባቢሎን ውጡ ፡፡ በዓለም ውስጥ ሆነን ምንም ብናደርግ ትክክል አንሆንም፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ጥሪ ሰው  ሁሉ ከዚህች ከምትጠፋው ባቢሎን ከሆነችው የጨለማ ዓለም ወጥቶ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ራስና ንጉሥ ወደሆነላት ወደ ቤተ ክርስቲያን ለርስቱ ወደተለየው ከጨለማ ወደ ሚደነቅ ብርሃን ወደገባው ማኅበረሰብ እንዲገባ ነው፡፡ 

 

እጅግ የሚያሳዝነው ነገር በክርስቶስ ወንጌል አምኖ ክርስቲያን የሚለውን ስም የያዘ ብዙ ህዝብ ወደኋላ በሚጎትቱት ሐሰተኛ አስተማሪዎች ምክንያት በዓለም ወጥመድ ተይዞ  ክርስቲያን የሚለውን ስም ብቻ ይዞ በዚህች ልትጠፋ ባለችው ዓለም ውስጥ መኖሩ ነው፡፡  ይህንን የሚያውቀው እግዚአብሔር መል አኩን ልኮ እንዲህ ይጣራል፡፡ 

“ከዚህ በኋላ ታላቅ ስልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፥ ከክብሩም የተነሣ ምድር በራች። በብርቱም ድምፅ፦ ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፥ ወደቀች፥ የአጋንንትም ማደሪያ ሆነች፥ የርኵሳንም መናፍስት ሁሉ መጠጊያ የርኵሳንና የተጠሉም ወፎች ሁሉ መጠጊያ ሆነች፤ አሕዛብ ሁሉ ከዝሙትዋ ቍጣ ወይን ጠጅ የተነሳ ወድቀዋልና፥ የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ የምድርም ነጋዴዎች ከቅምጥልነትዋ ኃይል የተነሳ ባለ ጠጋዎች ሆኑ ብሎ ጮኸ። ከሰማይም ሌላ ድምፅ ሰማሁ እንዲህ ሲል፦ ሕዝቤ ሆይ፥ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ፤ ኃጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና፥ እግዚአብሔርም ዓመፃዋን አሰበ።” የዮሐንስ ራእይ 18:1-5

ተመልከቱ እግዚአብሔር ህዝቤ ሆይ እያለ እየጠራው ያለው ህዝብ ያለው በባቢሎን ውስጥ ነው፡፡ በክርስቶስ በማመኑ ምክንያት ህዝቤ ተብሎ ተጠርቶአል ግን ልትጠፋ ካለችው ባቢሎን ከዚህች ዓለም ሥርኣት አልወጣም፡፡ ባቢሎን ደግሞ በቅርቡ ትጠፋለች፡፡ ዓለም በጨለማ እየተርመሰመሰች ነው፡፡ እርስዋ በምትመላለስበት ጨለማ እየተመላለስን እርስዋ የምታስበውን እያሰብን የተለየን ነን ማለት አንችልም፡፡ የወንጌሉን ጥሪ ሰምተን ካልወጣን መጥፋትዋ ጥፋታችን ይሆናል፡፡ ወንጌላችንን ካልተካፈለች ቁጣዋን ታካፍለናለች፡፡ ለዚህም ነው ቅዱሱ መልአክ  በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከርስዋ ዘንድ ውጡ የሚለን፡፡ በርስዋ ውስጥ ሆነው የሚቀጥሉ ሁሉ በኃጢአትዋ እየተባበሩ ነው፡፡ ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች ተብለው የሚጠሩ ሰዎች በዘረኝነቱ በመከፋፈሉ በጥላቻው ዓለማውያን ከሚባሉት በበለጠ ሁኔታ ሲዋኙ ይታያል፡፡ ከነዚህ ውስጥ የሆናችሁ ይህንን የሰማይ ድምጽ ለመስማት እድሉን ያገኛችሁ ወገኖቼ ሆይ ከመቅሰፍትዋ እንዳትካፍሉ ከባቢሎን ውጡ፡፡ በሐይማኖታዊ ቃላት ሸፍነው የሚያቀርቡላችሁን ጠማማ ወንጌል አትስሙት፡፡ 

  ቤተ ክርስቲያን ቢቻል ለማኅበረሰብ ብርሃን ልትሆን ይገባታል፡፡ ካልተቻለና ከደከመች ግን ቢያንስ ከጨለማው ጋር መደመርና ለዚህች የዓመጻና የኃጢአት ሸክም በዝቶባት እየተናወጠች ላለችው ዓለም ሌላ ሸክም ልትሆን አይገባም፡፡ አሁን የሚታየው ግን  አብያተ ክርስቲያናትና መሪዎቻቸው የመፍትሄው ሳይሆን የችግሩ አካል ሲሆኑና የዚህችን ዓለም ዓመጽ አብረው ሲያቀጣጥሉ ነው፡፡ ይህን ሲያደርጉ  የሚታዩ ራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን ብለው የሚጠሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ የእውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን ሥራ የእግዚአብሔርን ዓላማ ለማኅበረሰብ ማምጣት መግለጥና ማሳየት ነው፡፡ 

ከወንጌሉ ወጥታችሁ ህዝቡን እያሳሳታችሁ ያላችሁ የክርስትና ሐይማኖት መሪዎች የፍርድ ቀን ሳይደርስ ንስሐ ግቡ፡፡ በነዚህ በውጭ ታላላቅ በሆኑ የሃይማኖት መሪዎች የተታለላችሁ ወንድሞቼና እህቶቼ ም እመናን ሆይ ክርስትና የከበረ ህይወት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የተለየች የከበረች የክርስቶስ አካል ናት፡፡ በክርስቶስ አካል ውስጥ የምድር ብሄርና ቋንቋ አይታወቅም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ቋንቋ ብሄርዋ ክርስቶስ ነው፡፡ ስለዚህ የሚያስቷችሁን ትታችሁ እውነተኛው አስተማሪ መልካሙን እረኛ ኢየሱስ ክርስቶስን ተከተሉ፡፡ እርሱ መልካም እረኛ ነው፡፡ እርሱ ፍቅር ነው እርሱ ሰላም ነው እርሱ ህይወት ነው፡፡  እውነተኛይቱ  ቤተ ክርስቲያን የርሱን ወንጌል የምትሰብክ ናት፡፡ በምድር ላይ የምትደግፈውም የምትቃወመውን መንግሥት ሊኖራት አይገባም፡፡ ወንጌሉ ይሰበክ ዘንድ ጸጥታና ሰላም እንዲሆን ላሉት መንግሥታት መጸለይና ወንጌልን በመስበክ የሰማዩን መንግሥት ማስፋት ብቻ ነው፡፡ መልአኩ አንሁንም በብርቱም ድምፅ፦ እንዲህ ይላል፡፡  “ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፥ ወደቀች፥ የአጋንንትም ማደሪያ ሆነች፥ የርኵሳንም መናፍስት ሁሉ መጠጊያ የርኵሳንና የተጠሉም ወፎች ሁሉ መጠጊያ ሆነች፤ አሕዛብ ሁሉ ከዝሙትዋ ቍጣ ወይን ጠጅ የተነሳ ወድቀዋልና፥ የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ የምድርም ነጋዴዎች ከቅምጥልነትዋ ኃይል የተነሳ ባለ ጠጋዎች ሆኑ ብሎ ጮኸ። ከሰማይም ሌላ ድምፅ ሰማሁ እንዲህ ሲል፦ ሕዝቤ ሆይ፥ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ፤ ኃጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና፥ እግዚአብሔርም ዓመፃዋን አሰበ።” የዮሐንስ ራእይ 18:1-5

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡

Leave a Comment