Skip to content
Yeslase Mahber

December 6, 2020

ለኔ ህይወት ክርስቶስ ነው፡፡

ስም ክርስቲያን፡ የአባት ስም ክርስቶስ፡ አገር ሰማያዊ ስፍራ፡ ብሄር ክርስቲያን፡ ቋንቋ ክርስቶስኛ፡ ባህል ክርስቶስ፡ ህይወት ክርስቶስ፡ ኑሮ ክርስቶስ፡፡

“ይህ ናፍቆቴ ተስፋዬም ነውና፤ በአንድ ነገር እንኳ አላፍርም ነገር ግን በሕይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ በግልጥነት ሁሉ እንደ ወትሮው አሁን ደግሞ በስጋዬ ይከብራል።ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና።” ፊሊ 1፤20-21

እኔ ደግሞ ብዙዎቹ ይድኑ ዘንድ ለጥቅማቸው እንጂ የራሴን ጥቅም ሳልፈልግ በሁሉ ነገር ሰውን ሁሉ ደስ እንደማሰኝ፥ ለአይሁድም ለግሪክም ሰዎች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንም ማሰናከያ አትሁኑ። 1.ቆሮ።10፤32᎒33

“እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ፥ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁታልና፥ የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል፤
በዚያም የግሪክ ሰው አይሁዳዊም የተገረዘም ያልተገረዘም አረማዊም እስኩቴስም ባሪያም ጨዋ ሰውም መሆን አልተቻለም፥ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፥ በሁሉም ነው።” ቆላ።3፤9-11

ክርስቲያን ስትሆኑ ሁሉንም ነው የቀየራችሁት፡፡ ዘር ቀየራችሁ በዚህም ምክንያት ቤተሰብ ቀየራችሁ ባህል ቀየራችሁ ቋንቋ ቀየራችሁ ስሜት ቀየራችሁ፡፡ ጠቅለል ባለ አማርኛ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁታል ነው የሚለው፡፡ ከአሮጌው ሰው አንዳንድ ባህርያትን አይደለም የገፈፍነው፡፡ ሙሉ በሙሉ አሮጌው ሰው ሞቶ አሮጌው ሰው ተገፎልን ሙሉውን አዲሱን ሰው ነው የለበስነው፡፡
ዋናውን ዛፍ ዋናውን ስር ስትቆርጡ የማይቀየር ነገር የለም፡፡ አንድን ዛፍ ከስሩ ስንነቅለው ወይም ስንቆርጠው ሁለንተናውን ነው የቆረጥነውና የገደልነው፡፡ ግንዱ ቅርፊቱ ቅርንጫፉ ቅጠሎቹ ፍሬዎቹ ሁሉ ይሞታሉ፡፡ ዛፉን ሳንቆርጥ ቅርንጫፎቹን ቅጠሎቹን ፍሬዎቹን ብንቆርጥ ግን ዛፉን ሙሉ በሙሉ አላጠፋነውም፡፡ ዛፉ በህይወት አለና መልሶ ሌላ ቅርንጫፍ ያወጣል ሌላ ቅጠል ሌላም ፍሬ ያወጣል፡፡ ብዙ ክርስቲያኖች ክርስቲያን ሲሆኑ ሙሉ በሙሉ እንደተነቀለው ወይም እንደተቆረጠው ዛፍ ሙሉ በሙሉ የማንነት ለውጥ እንዳደረጉ አላወቁም፡፡ የሰዎች ሁሉ ግንድና አባት ከሆነው ከምድራዊው አዳም ወጥተው ወደ ኋለኛው አዳም ወደ ክርስቶስ እንደተሻገሩ አልሰሙም አላመኑም አላወቁም፡፡ ለነርሱ ክርስቲያን መሆን ማለት በዚያው በድሮው በአዳም ሆኖ የተወሰኑ ባህሪያትን ማሻሻል ይመስላቸዋል፡፡ ከስሩ ሳይነቀል ቅርንጫፎቹና ቅጠሉ እንደተቆረጡበት ዛፍ አንዳንድ ክፉና ኃጢአት ያሏቸውን ባህርያት ብቻ ቆረጥ አድርገው በመጣል ብቻ ተለወጥን ክርስቲያን ሆንን ብለው ያስባሉ፡፡ የሃይማኖት መምህራኖቻቸውም እንደነርሱው ቅጠልና ቅርንጫፍ መልምለው የተቀመጡ አዳሞች ስለሆኑ እውነተኛውን ወንጌል ለህዝቡ የነገረው የለም፡፡ እውነተኛው ክርስትና ግን እንደ ጓሮ አትክልት አዳምን በየወሩ እየከረከሙ ማሳመር ሳይሆን እርሱ ተነቅሎና ሞቶ በርሱ ምትክ ክርስቶስ ተተክቶ የዘር ግንዳችን መሆኑ ነው፡፡ ከሰማያዊው ሰው ከክርስቶስ ዳግመኛ ስለመወለድ በመጀመሪያ የሰማው የአይሁድ አለቃው የህጉ መምህር ኒቆዲሞስ ከላይ የሚታይና የሚከረከም ኃጢአት አልነበረውም፡፡ ህጉን ጠንቅቆ የተማረና ሌሎችን የሚያስተምር ረቢ ነበር፡፡ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣባት ሌሊትም የመጣው እንደ ሌሎቹ ፈሪሳውያን ሊያሳድደው ሳይሆን እውነተኛ መልእክተኛ መሆኑን ለመመስከር ነበር፡፡ መጥቶም እንዲህ አለው “መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው።” የዮሐንስ ወንጌል 3፤2
ይህ መልካም ምስክርነት ነው፡፡ እንደ ሰው ስናየው ኒቆዲሞስ ትልቅ ምስጋናና ሙገሳ ከኢየሱስ ክርስቶስ መቀበል የነበረበት ይመስላል፡፡ ከኢየሱስ ክርስቶስ የሰማው መልስ ግን እጅግ የሚያስገርምና ረቢው ኒቆዲሞስ ሰምቶት የማያውቅ ነገር ነበር

“ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው።” ቁ።3
ይህም ማለት ኒቆዲሞስ በዚያው ማንነቱ ኒቆዲሞስነቱን አይሁዳዊነቱንና የአይሁድ ህግ መምህርነቱን እንደያዘ የቱንም ያህል መልካም ስብእና ቢኖረውና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም ቢናገር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባትና የእግዚአብሔር ወገን መሆን አይችልም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ከላይ እንዳየነው ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ የወረደው የሞተውን አሮጌውን አዳም ጠጋግኖና አሰማምሮ ለማዳን ሳይሆን በመስቀሉ ገድሎትና አስወግዶት እኛን ከራሱ ዳግመኛ በመውለድ የርሱ ዘሮች ያደርገን ዘንድ ነው፡፡ ስለዚህ ከኋለኛው አዳም ከክርስቶስ የተወለዱ ሁሉ ልደታቸው ዘራቸው ማንነታቸው ከሰማይ ነው፡፡ ዳግመኛ መወለድ አዲስ ጅማሬ ነው፡፡ ሰው ከመወለዱ በፊት ምንም ማንነት እንደሌለውና ህይወትን የሚጀምረው ሲወለድ እንደሆነ ሁሉ የክርስቲያኖችም ማንነት ዳግመኛ ተወልደው ክርስቲያን ሲሆኑ የጀመረ አዲስ ማንነት ነው፡፡
ስለዚህ ክርስቲያን ማለት ሁለንተናው ከላይ የሆነ ማህበረሰብና ህይወት ነው፡፡ ብዙዎቹ እንደለመዱት ክርስትና ማለት ባላቸው አሮጌ ማንነት ዘርና ብሄር ባህልና ኑሮ ላይ የተደረበ ካባ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ራሱን የቻለ ሰማያዊ ህይወት ነው፡፡ ይህ ያልገባቸው ሰዎች ግን ሃይማኖትህ ምንድን ነው? ተብለው ሲጠየቁ ክርስቲያን ይሉና ዘርህ ወይም ነገድህ ወይም አገርህ ሲባሉ ደግሞ ነጭ ጥቁር አሜሪካዊ ኢትዮጵያዊ አማራ ኦሮሞ ትግሬ ወዘተ ይላሉ፡፡ ይህ መቸም በብዙኃኑ የተለመደና ተቀባይነት ያገኘ ነገር ስለሆነ እግዚአብሔር ልቡናውን ከከፈተለት ሰው በቀር የሚረዳው የለም፡፡ እዚህ ጋ አሜሪካዊ መሆን ኢትዮጵያዊ ወይም ሱዳናዊ መሆን አማራ ትግሬ ኦሮሞ መሆን ክፉ ነው እያልኩ አይደለም፡፡ አሜሪካዊነት ለአማኤሪካውያን እንግሊዛዊነት ለእንግሊዛዊያን ቻይናዊነት ለቻይናውያን ትክክል ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ማንነት የለውምና፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ኢትዮጵያዊ መሆኑ ወይም በብሄር አማራ ትግሬ ኦሮሞ ባንቱ ወዘተ መሆኑ ለርሱ ችግር የለበትም፡፡ እያልኩ ያለሁት ክርስቲያኖች ግን ሌላ ማንነት አላቸው ነው፡፡ አሜሪካዊ ከኢትዮጵያዊ የተለያየ እንደሆነ ሁሉ ክርስቲያኖችም ከነዚህ የምድር የክፍፍል መደቦች የተለዩ ናቸው፡፡ ኦሮሞው ትግሬ እንዳልሆነ ሁሉ ትግሬው ነጭ አሜሪካዊ እንዳልሆነ ሁሉ ነጩ አሜሪካዊ ጥቁር አፍሪካዊ እንዳልሆነ ሁሉ ክርስቲያንም ነጭ ጥቁር ወይም ሌላ ዘር አይደለም፡፡ ክርስቲያን ነገዱ ክርስቲያን ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን የተናገረውን ተመልከቱ፡፡ “ለአይሁድም ለግሪክም ሰዎች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንም ማሰናከያ አትሁኑ።” 1.ቆሮ።10፤32᎒33፡፡
በቆሮንቶስ ያሉት ክርስቲያኖች ድሮ ግሪካውያንና አይሁዳዊያን የነበሩ ናቸው፡፡ ቁጥራቸውም ከነዚሁ የማህበረሰብ መደብ የሚመደብ ነው፡፡ ክርስቲያን ሲሆኑ ግን ከዚያ የዘር መደብ ወጥተዋል፡፡ ለዚህም ነው ለአይሁድም ለግሪክም ሰዎች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንም ማሰናከያ አትሁኑ። የሚላቸው፡፡ በዚህ ስፍራ እነርሱ የተካተቱባት በቆርንቶስ ያለችው ማህበር የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ እነርሱ ከግሪክና ከአይሁዳዊነት ስለወጡ ከነርሱ ጋር አልመደባቸውም፡፡ እነርሱ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡ ግሪክም አይሁድም አይደሉም፡፡ በዚህ ዘመን ይህ የገባቸው አብያተ ክርስቲያናትና መንግሥታት ቢኖሩ አዋጅ ሲያወጡ እንደዚህ ለይተው ነበር የሚያወጡት፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካ መንግሥት አንድ አገር አቀፍ አዋጅ ሲያውጅ ለአሜሪካውያን ሁሉ ነው የሚያውጀው እንጂ ለአሜሪካውያንና ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን አይልም፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን በአሜሪካኖች ውስጥ እንደማትካተት አያውቅምና፡፡ ለነገሩ ምሳሌውን አነሳን እንጂ ቤተ ክርስቲያን ነኝ የምትለው ራስዋ ካላወቀች እንዴት መንግሥት ያውቃል? ክርስቲያን ግን ከዚህ ዓለም ሰዎች ጋር አይቆጠርም ነገዱ ክርስቶስ ነው፡፡ አንድ አሜሪካዊ ኢትዮጵያዊ ለምን አልሆንክም ብለን እንደማንጠላው ሁሉ አንድ ክርስቲያንም ነገዴ ህይወቴ ብሄሬ ቋንቋይ ክርስትና ነው ሲል ልንጠላው አይገባም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ከላይ ባየነው ለቆላስይስ ም እመናን በላከው መል እክቱ “የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል፤ በዚያም የግሪክ ሰው አይሁዳዊም የተገረዘም ያልተገረዘም አረማዊም እስኩቴስም ባሪያም ጨዋ ሰውም መሆን አልተቻለም፥ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፥ በሁሉም ነው።” ብሎ ሲናገር ግሪኮችን አይሁዳዊያንን እየጠላቸው ሳይሆን ክርስቲያኖች በለበሱት አዲሱ ሰው ውስጥ ግን አይሁዳዊነትና ግሪካዊነት የለም እያለ ነው ያለው፡፡ በእርግጥ ዳግም ተወልደው ክርስቲያን ላልሆኑ አይሁዶች አይሁነት አለ ለግሪኮችም ግሪክነት አለ፡፡ በክርስቲያኖች ውስጥ ግን ክርስቶስ ብቻ ነው ያለው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያውያንም አሜሪካውያንም በአጠቃላይ በምድር ያሉ የሰው ልጆች ሁሉ እግዚአብሔር የሚወዳቸውና አንድ ልጁን አሳልፎ የሰጣቸው ናቸው፡፡ ክርስቲያን ለመሆን ግን ዳግመኛ መወለድና አዲሱን ሰው መልበስ ይጠይቃል፡ ይህም ወንጌሉን ሰምቶና አምኖ በፈቃደኝነት የሚደረግ ለውጥ ነው፡፡ በምድር ላይ ብዙ አገሮች ሁለተኛ ዜግነት ደርቦ መያዝን አይፈቅዱም፡፡ ያውም ያ ዜግነቱን የቀየረው ሰው በወረቀት ላይ እንጂ ማንነቱን ባህሉን ቋንቋውን ተፈጥሮውን አልቀየረም፡፡ ወረቀት ላይ ዜግነቱን ስለቀየረ ብቻ የድሮ ዜግነቱን እንዲያጣ ይገደዳል፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥትም ድራቢ ብሄርን ዜግነትን አይፈቅድም፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ዜግነት ምድራዊ ዜግነትን ከመቀየር በእጅጉ የላቀ እና የማይወዳደር ነው፡፡ አንድ ሰው ክርስቲያን ሆኖ ዜግነቱን ወደ እግዚአብሔር ወደ ሰማያዊው መንግሥት ሲቀይር በወረቀት ላይ ሳይሆን በዳግም ልደት ማንነቱ ሙሉ በሙሉ በመንፈስ ቅዱስ ከማይጠፋው ዘር ተወልዶ ነው የሚቀየረው፡፡ በዚህም አሰራር ከጨለማው መንግሥት ወጥቶ ወደ ብርሃን መንግሥት ገብቶአል፡ ከአሮጌው ሰው አዳም ዘር ወጥቶ ወደ ኋለኛው አዳም ወደ ክርስቶስ ዘር ገብቶአል፡፡ ሲቀየር ሙሉ በሙሉ ነው የተለወጠው፡፡ ቀድሞ የእግዚአብሔር ወገን አልነበረም አሁን ግን ወገን ሆነ ቀድሞ በጨለማ ነበረ አሁን ግን በብርሃን ነው፡፡ ቀድሞ አሮጌው ሰው ነበረ አሁን ግን አዲሱ ሰው ነው፡፡ ስለዚህ አሁን የእግዚአብሔር ወገን ከሆነ በኋላ ድሮ ወገን ወዳልነበረበት ማንነት አይመለስም፡፡ አሁን በብርሃን ከሆነ በኋላ ድሮ ወደነበረበት ጨለማ አይመለስም፡፡ አሁን አዲሱን ሰው ከለበሰ በሁላ ድሮ ይኖርበት ወደነበረው አሮጌው ሰው አይመለስም፡፡ በመሆኑም እውነተኛው ክርስትና ውስጥ ያለ ሰው ሃይማኖት ሲባል ክርስትና ብሄር ሲባል አማራ ወይም ትግሬ አይልም፡፡ ባህል ቋንቋ ሲባል ምድራዊ ቋንቋና ባህልን አይጠቅስም፡፡ ሃይማኖት ክርስትና ብሄር ክርስትና ቋንቋ ክርስትና ባህል ክርስትና ብሎ ነው የሚመልሰው፡፡ ክርስትና ለርሱ ሁሉንም ነው፡፡ ክርስትና የሚባለው ህይወት እንዲሁ እንደ ኮፍያ ከላይ የሚደረብ ነገር ሳይሆን ሁለንተናችንን የሚገዛና የምንኖርበት የክርስቶስ ህይወት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው በትውልድ አሜሪካዊ መሆኑን ካወቃችሁ አሜሪካዊ ነኝ በሚለው ስብእና ውስጥ ብዙ ነገሮች የተካተቱ መሆናቸውን ታውቃላችሁ፡፡ አሜሪካዊ በሚለው ስብእና ውስጥ ባህል ቋንቋ ስሜት አስተሳስብ ሁሉ አብረው ተገምደዋል ተዋህደዋል፡፡ የክርስትና ህይወት ክርስቶስ ሁሉ በሁሉ የሆነበት ማንነት ነው፡፡ ክርስቲያን ሐሳቡም ባህሉም ቋንቋውም ልቡም ህይወቱም የክርስቶስ ነው፡፡ ክርስቶስ ሞልቶበታልና፡፡

← Teachings