December 6, 2020
የቃየን አቤቱታ
ወንድሙን በድንጋይ ቀጥቅጦ የገደለው ጀግናው {?} የአዳም ልጅ ቃየን ለተጠየቀበት ወንጀል ይግባኝ ጠየቀ፡ ለሰማዩ ፍርድ ቤት ባቀረበው አቤቱታ ወንድሞቹን ሰባት ቢልዮን የሚሆኑትን የአዳም ልጆች በስም ማጥፋት ወንጀልም ከሶአቸዋል፡፡ ክርክሩን በዝርዝር ሲያቀርብም እኔ ቃየን ስሜ የነፍሰ ገዳዮች ምሳሌ ሆኖ ሁልጊዜ በጥላቻ መነሳቱና በነፍሰ ገዳይነት መታወቁ ትክክል አለመሆኑን አመለክታለሁ በማለት አቤቱታውን እንዲህ በማለት አስረድቶአል፡፡ ክቡር ፍርድ ቤት በመጀመሪያ ወንድሜን ከመግደሌ በፊት ያለው መልካም ሥራየ እንዲታይልኝ አመለክታለሁ፡፡ ወንድሜን ከመግደሌ በፊት መስዋእት አቀርብ የነበርኩ ሰው መሆኔና ወንድሜንም የገደልኩት በጊዜአዊ ቁጣና ንዴት ተነሳስቼ ነው እንጂ ከልቤ ስለምጠላው አልነበረም፡፡ የገደልኩበትም መንገድ በዚህ ዘመን እንደሚደረገው በኒኩሌር በታንክ በመድፍና በከባድ መሳሪያ ሳይሆን በአንዲት እጄ ላይ በነበረች ድንጋይ ነበር፡፡ እንግዲህ እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ ዛሬ ህዝባቸውን በታንክ በመድፍና በሚሳይል የሚጨርሱት ወንድሞቼ በአንደኛ ደረጃ ሳይመዘገቡ እኔ የነፍሰ ገዳዮች ሁሉ ምሳሌ መደረጌና መጠቀሴ የስም ማጥፋት ዘመቻ መሆኑን ክቡር ፍርድ ቤቱ ይመልከትልኝ፡፡ ከሁሉ የሚያስገርመው ቃየን ነፍሰ ገዳይ ወንድሙን የገደለ እያሉ ስሜን የሚያጠፉት እነዚሁ በከባባድ መሳሪያዎች ህዝብን የሚያጠፉት መሆናቸው ነው፡፡ እነርሱ በየእለቱ በየሰዓቱና በየደቂቃው በመድፍ በታንክና በብዙ መሳሪያዎች ህዝብን እየጨረሱና ደም እንደ ጎርፍ እያፈሰሱ ቃየን ያልተባሉ እንዴት የኔ ስም በአንደኛ ደረጃ ይቀመጣል? እንዲሁ ስሜን እያነሱና እያጠፉ እንደሚጠሉኝ ቢናገሩም ሁሉም ከኔ የባሱ ነፍሰ ገዳዮች መሆናቸው ሥራቸው ይመሰክራል፡፡ አንደኛ እኔ አንድ ሰው ብቻ ነው የገደልኩት፡፡ ሁለተኛ ጭካኔ በተሞላበት በከባድ መሳሪያ ሳይሆን በተሻለ መንገድ በድንጋይ ነው መትቼ የገደልኩት፡፡ እነርሱ ግ ን ሰውን ሲገድሉ እንኳ አካላቱን ቆራርጠው ነው የሚገድሉት፡፡ እውነቱ ይህ ከሆነ ቃየን እነርሱ ናቸው እንጂ እኔ ልሆን አይገባም፡፡ በእውነቱ ስሜ ለብዙ ዘመናት በከንቱ ጠፍቶብኛል፡፡ ሌላው ቀርቶ የሃይማኖት መሪዎችና ሃይማኖተኞች ነን የሚሉት ጭምር እነርሱ ሄደው ሰው ባይገድሉም ገዳዮችን በመደገፍ አብረው ስለቆሙና በሰዎች መገደል ስለሚደሰቱ ሁሉም ከኔ የባሱ መሆናቸው የታወቀ ነገር ነው፡፡ በእውነቱ በዚህ ዘመን ባሉት ሰባት ቢልዮን በሚያህሉ ታናናሽ ወንድሞቼ ስመዘን እኔ ጻድቁ ቃየን እንጂ ነፍሰ ገዳይ ልባል አይገባም በማለት አቤቱታውን አቅርቦአል:: ስለዚህ ወንድሞቼ የአዳም ልጆች ምድርን በሰው ደም እያጠቧት እኔን አንድ ሰው ብቻ ያውም በድንጋይ የገደልኩትን ሰው ቃየን ነፍሰ ገዳይ እያሉ ስሜን ማጥፋታቸው እንዲታገድልኝ እና እኔ ነፍሰ ገዳይነቴ በእግዚአብሔር ፊት እንጂ በነርሱ ሥራ ስመዘን ግ ን የተሻልኩ ሰው መሆኔ ታይቶ ስሜ እንዲታደስልኝ በትህትና አመለክታለሁ በማለት አቤቱታውን አሰምቶአል፡፡ ክርክሩን በጥሞና ያዳመጠው ሰማያዊው ፍርድ ቤትም እነዚህ ከቃየን ይልቅ ብዙ ህዝብን በጭቃኔ እየገደሉ ያሉ የዓለም ህዝብ ከእንግዲህ በኋላ ቃየን እነርሱ መሆናቸውን አሳውቆ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ለነጩ ዙፋን ፍርድ ቀን ቀጠሮ ሰጥቶታል፡፡