Skip to content
Yeslase Mahber

December 16, 2020

ሁለት ታላላቅ ብርሃናት

ሁለት ታላላቅ ብርሃናት

ብርሃናችሁ በሰው ሁሉ ፊት ይብራ።

“እግዚአብሔርም ሁለት ታላላቆች ብርሃናትን አደረገ ትልቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፥ ትንሹም ብርሃን በሌሊት እንዲሰለጥን ከዋክብትንም ደግሞ አደረገ። እግዚአብሔርም በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር አኖራቸው” ዘፍ.1:16-17

“ደግሞም ኢየሱስ፦ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ብሎ ተናገራቸው።” የዮሐንስ ወንጌል 8፥12 

“እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል። መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።” ማቴ.5:14-16

“እንዲሁ ጌታ፦ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለማዳን ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ ብሎ አዞናልና አሉ።” ሐዋ.13:47

“በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ፦ በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና።” 2.ቆሮ.4፤6

ዘላለማዊው የሥላሴ ሕይወት ሚስጢር

“ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም፤ አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፥ አንተ፥ አባት ሆይ፥ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ።
እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል።” ዮሐ.17፤20-23
ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎቱን ፈጽሞ ወደ አባቱ ሊያርግ በተቃረበበት ጊዜ ይህን ጸሎት ወደ አባቱ አቀረበ። ከርሱ ጋር የነበሩት ደቀመዛሙርቱና እንደዚሁም ከነርሱ በኋላ ለሚመጡት ሁሉ ህያው ሰሌዳ ሆነው የሥላሴን መልክ እንዲያንጸባርቁ ጸለየላቸው ጸለየልን። በሥላሴ ያለው ይህ ሕይወትና አንድነት ደግሞ ሊተረክ የሚችለው ያንን ሕይወት በተካፈሉና በሚያንጸባርቁ ሰዎች ብቻ ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ከአብ ዘንድ የነበረና ለእኛም የተገለጠ ሕይወት ነው። ማንም አይቶት የማያውቀውን እግዚአብሔርን እርሱ ገለጠው ተረከው። በርሱ መገለጥም የሥላሴን ሕይወት በቀጥታ ስርጭት {Live} አየን። በታቦር ተራራና በዮርዳኖስ ወንዝ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ እርሱን ስሙት የሚል የፍቅር ድምጽ ከአባቱ ሲነገር ሰማን። መንፈስ ቅዱስም በእርግብ አምሳል በርሱ ላይ በማረፍ የዋህነቱን መሰከረለት። ኢየሱስ ክርስቶስም ደጋግሞ አባቱ እንደሚወደው ይመሰክር ነበር። ይህ በሥላሴ መካከል ያለው ዘላለማዊና አስደናቂ ኅብረት ፍቅርና አንድነት ለወደቁትና በጨለማ ላሉት እርስ በርስ ሲገፋፉና ሲጠላሉ ለሚኖሩ ለሰው ልጆች እንግዳ ሕይወት ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ ያየነው የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ ሕይወት ዘላለማዊውና እውነተኛው ሕይወት ነው። እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ ሲፈጠረው ይህንን ሰማያዊ ሕይወት እንዲካፈልና እንዲኖር ነበር የፈጠረው። ሰው ግን የሞትን የጨለማን መንገድ መርጦ ከእግዚአብሔር ጋር ሳይሆን በሐሰት ካታለለው ከሰይጣን ጋር የሚመሳሰል ኑሮ መኖር ጀመረ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ የጨለማና የሞት ኑሮ ሲናገር

“እንግዲህ አሕዛብ ደግሞ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ በጌታም ሆኜ እመሰክራለሁ።
እነርሱ ባለማወቃቸው ጠንቅ በልባቸውም ደንዳንነት ጠንቅ ልቡናቸው ጨለመ፥ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ፤ ደንዝዘውም በመመኘት ርኵሰትን ሁሉ ለማድረግ ራሳቸውን ወደ ሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ።” ይላል። ኤፌ.4፤17-19። 

በሰይጣን ምክንያት ልቡናው የጨለመው የሰው ልጅ በልቡ ደንዳናነት ደንዝዞ ከእግዚአብሔር ሕይወት ርቆ ጠፋ። እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ። ፍቅር የሆነው እግዚአብሔር ግን የሰውን ልጅ ከዚህ ጨለማና ሞት አድኖ የሥላሴ ወደሚመስለው ሕይወት ለመመለስ አንድ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ላከ። ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶም በጨለማ ላሉት ብርሃን ሆነላቸው። እግዚአብሔር ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነም በመካከላቸው በመኖር የሥላሴን ሕይወት ተረከላቸው። ሆኖም ሁሉም አልተቀበሉትም። ከነርሱ ያልተለየ እንደሆነ ተራ ሰው ያውም አሳች እንደሆነ የጸራቢው የዮሴፍ ልጅ እንደሆነ ይናገሩ ነበር። እርሱ ግን ከሶስቱ አካላት አንዱ አካል ህያው የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ ለደቀመዛሙርቱ ተገለጠላቸው። ከርሱ ጋር በመኖርም የሥላሴን ሕይወት ፍቅርና አንድነት በቅርበት ተመለከቱ። በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ የሚያዩት ፍቅር እና ህብረት በዚህ ዓለም የሌለና ከላይ እንደሆነ በትንሹ አስተዋሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ ከሰማይ ነኝ ከእግዚአብሔር ነኝ ቢልም ህጉንና ነቢያትን የሚያነቡ የአይሁድ ካህናትና ፈሪሳውያን ሳይቀሩ ከኛ የተሻልክ አይደለህም እንዲያውም ከኛ የባስክ ኃጢአተኛ ትእቢተኛና ሐሰተኛ ነህ አሉት። እርሱ የህያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ በርሱ በአባቱና በመንፈስ ቅዱስ ያለው ፍቅርና አንድነት የተለየ እንደሆነ ያዩት ደቀመዛሙርቱ ብቻ ነበሩ። እንዲያውም ደጋግሞ ሰለአባቱ ከመናገሩ የተነሳ አብን እጅግ ናፈቁትና  አብንና አሳየንና ይበቃናል እስከማለት ደረሱ። አብን ወልድንና መንፈስ ቅዱስን እጅግ ወደዱ። ጌታም እርሱን ከወደዱት ትእዛዙን እንደሚጠብቁ አብም እንደሚወዳቸው ደግሞም መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክላቸው ከዚህ በኋላ ከአብ ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ ተለይተው እንደማይኖሩ በመናገር አጽናናቸው። ደቀ መዛሙርቱ ከዚህች በጨለማ ከተሞላች ዓለም በአታላዮች በገዳዮች በከዳተኞች ከተሞላች ዓለምና ከጠማማ ማህበረሰባቸው እየወጡ ወደ ሰማያዊው የሥላሴ ቤተሰብ ኅብረት እየገቡ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ ከነርሱም በኋላ በነርሱ ምስክርነት ሰዎች ወደሰማያዊው ህብረት እንዲገቡ ፈልጎአል። ይህ እንዲህን ደግሞ ጌታችንና መድኃኒታች ከአብ እንደተላከ ከሰው ልጆች የተለየ ኃጢአት የሌለበት ሰውም ሆኖ ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ህብረቱ ያልተቋረጠ እንደሆነ፤ ሰው የሆነ አምላክነቱን እና የሥላሴ አካልነቱን ሳይተው እንደሆነ በዓለም ያሉ ሰዎች እንዲያውቁ ይፈልጋል።  በርሱ ሰው መሆንም ሰዎች ከጨለማና ከኃጢአት በመውጣት ወደዚህ የብርሃን ህብረት እንዲመጡ ሐዋርያቱን እየላከ ነው። ስለዚህ ጸሎቱ እርሱን አብ እንደላከው፤ ከሰው ልጆች የተለየ እንደሆነ፤ እየኖረ ያለው ሕይወት የገለጠው ባህርይና ማንነት  ከሰማይ እንደሆነ ዓለም ያምን ዘንድ ያ በርሱ በአባቱና በመንፈስ ቅዱስ መካከል ያለውና ደቀመዛሙርቱ ያዩት ሕይወት በደቀመዛሙርቱ እንዲገለጥ ነው። ደቀ መዛሙርቱ ወደዚህ ህብረት ገብተው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ አንድነትና ፍቅር ህብረት ውስጥ ሲኖሩና ያ በኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠውና የታየው የሥላሴ ሕይወት በነርሱም ሲገለጥ ያን ጊዜ ዓለም ይህንን በዓለም የማይገኝን ህብረት ፍቅርና አንድነት በክርስቲያኖች ሲያይ ኢየሱስ እውነትም ከአብ የተላከ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እንዲያምን ነው። በዚህ ሁሉ የምንመለከተው የኛ የክርስቲያኖች ኑሮ ህያው ወንጌል እንደሆነ ነው። ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እንዲያምኑ ምስክርና ማስረጃ የሚሆነው ያ በኛ በክርስቲያኖች ውስጥ የሚተረከው የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ አንድነት ኅብረትና ፍቅር ነው። ይህም ማለት የሰዎች ክርስቶስን የማወቅና የማመን ሁኔታ የተመሠረተው በኛ በክርስቲያኖች በሚገለጠው ሰማያዊ ሕይወት ነው ማለት ነው። የኛ አንድነትና የሰዎች መዳን ምን ያህል በቀጥታ እንደተያያዘ ተመልከቱ። ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር እንደመጣ እንዲያምኑ እርሱ ያመጣው እና የገለጠው ለኛም የሰጠው አንድነት ፍቅርና ሕይወት በኛ መተረክና መታየት አለበት። ኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር እንደሆነና የገለጠው የሥላሴ ሕይወት የተለየ እንደሆነ ማረጋገጫው ያ በዓለም የሌለ የተለየ የፍቅርና የአንድነት ሕይወት በኛ ሲተረክ ነው።

ሰዎች መጽሐፍ አንብበንላቸው ስለ እግዚአብሔር ሊያውቁ ይችላሉ። የስሉስ ቅዱስን መልክ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ያለውን አስደናቂ ሕይወት ሊያዩ የሚችሉት ግን በእኛ ላይ ሲንጸባረቅ ብቻ ነው።
እኛ ክርስቲያኖች የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ የሚተረክብን ህያው ሰሌዳዎች ነን። የሥላሴ ሕይወት ዘላለማዊ ሚስጢር ነው። ሥላሴ ከዘላለም እስከ ዘለዓለም በአንደነትና በሶስትነት የሚኖሩ እንደ ወንዝ በማያቋርጥ የፍቅር የአንድነትና የኅብረት ዑደት የሚኖሩ በአካል ሶስት በመለኮት አንድ የሆኑ ናቸው። ይህ ዘላለማዊ ህብረት ፍቅርና አንድነት በሥላሴ መካከል እንደወንዝ እየፈሰሰ ይኖራል። ነገር ግን ሰው ከክብሩ ስለወደቀና ስለሞተ ይህንን የሥላሴን ሕይወትና ባህርይ እንዳያይ ልቡ ስለታወረና በጨለማ ስለሚመላለስ ማየት አይችልም ነበር። ጌታችንንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ ግን ይህንን ለዘላለም ተሰውሮ የነበረውን ሚስጢር ለኛ ለሰው ልጆች ገለጠው። ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የነበረው ህብረት አንድነትና ፍቅር በርሱ ሲተረክ አየን። እርሱ የክብሩ መንጸባርቅ ነው። እርሱ የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን የሥላሴን ባህርይ ገልጦ ሲያሳየን ግን ሊያስቀናን ወይም ለሰላሳ ሶስት ዓመት ብቻ አሳይቶት ለመሄድ ሳይሆን እንደ ዘር በኛ ውስጥ ዘርቶት እንዲበቅልና በዳግም ልደት የዚህ ባህርይ ተካፋዮች እንድንሆን ነው። ቅዱስ ዮሐንስ ስለዚህ አስደናቂ ሕይወት መገለጥና እነማን እንደሚቀበሉት እንደዚህ ይተርክልናል

“በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።
ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ዮሐ.1፤1-4

ይህች በርሱ የነበረችው ሕይወት የሰው ብርሃን ነበረች ካለ በኋላ ይህች የሰው ልጆች ብርሃን የሆነችው ብርሃን እንዴት እንደተገለጠች ማለትም ስለ ክርስቶስ መገለጥ ይተርክልናል።

“ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር። በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም።  የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም። ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን። ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ እንዲህም ብሎ ጮኸ፦ ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ። እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ። መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው።” ዮሐ.1፤9-18

በመጀመሪያ የነበረው ሁሉ በእርሱ የሆነው የሰው ሕይወት በእርሱ ያለችው ዘላለማዊው ቃል ክርስቶስ ሥጋ ሆነ ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ በእኛ አደረ፡ ነገር ግን ሁሉም አልተቀበሉትም። የተስፋ ቃል የተሰጣቸው ክርስቶስ በነርሱ በኩል እንደሚመጣ የተነገረላቸው የአብርሃም ዘሮች የሆኑት ወገኖቹ አልተቀበሉትም። ጥቂቶች ግን እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ በእርሱ ሕይወት እንዳለች ሕይወትም ብርሃን እንደሆነችላቸው አይተው አመኑት ተቀበሉት። ይህችን ብርሃን የሆነች ሕይወት በመካፈላቸውም የእግዚአብሔር ልጆች ሆኑ። ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ በመካከላቸው ከተገኘው ከክርስቶስ ሙላትን ተቀብለው ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ብለው መሰከሩ። ማንም አይቶት የማያውቀውን ፍቅር የሆነውን እግዚአብሔር በአንድ ልጁ አዩት አመኑት። ከዘላለም እስከ ዘለዓለም በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ የነበረው ህብረት ፍቅርና አንድነት በዚህ በተካፈሉት ሕይወት ምክንያት በደቀመዛሙርቱ ተዘርቶ በቀለ። ሕይወት ተገልጦ ወደ አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ህብረት ጨመራቸው። ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ የዚህን ዘላለማዊ ሕይወት መገለጥና ሕይወት በመገለጡ ምክንያት ያገኘነውን አዲስ ማንነት እንዲህ ይተርክልናል

“ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤ እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተ ደግሞ እናወራላችኋለን። ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው። ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን እንጽፍላችኋለን።”1.ዮሐ.1፤1-4

ከአብ ዘንድ የነበረውንና ለእኛም የገለጠውን የዘላለምን ሕይወት ስላገኘን ህብረታችን ከአብ  ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሆነ። ይህ ህብረት ከሰማይ ነው። ይህንን ህብረት አናውቀውም ነበር። በአዳም ምክንያት ስለሞትንና ስለወደቅን ህይወታችን የጨለማ ኑሮ ነበር። በዚህች ክፋትና ዓመጽ በሞላባት ዓለም በተለያየ መከፋፈልና መደብ በተከፋፈለው ክፉ ማህበረሰብ መካከል የአንደኛው ክፍል ሆነን እንኖር ነበር። ሁላችንም የዚህ ናችሁ የተባልንበት ወይም የዚህ ነን የምንለው ወገንተኝነት የነበረን ራሳችንን ከአንዱ አመጸኛ ስብስብ ጋር የምንቆጥር ሰዎች ነበርን። ደቀመዛሙርቱ አይሁዳውያን ነበሩ። ከነርሱ በኋላ ወንጌሉን አምነው ከመጡት ደግሞ ግሪካውያን አረማውያን ነበሩ። ነገር ግን የክርስቶስን አዲሱን ሰማያዊ ሕይወት ሲያገኙና የእግዚአብሔር ልጆች ሲሆኑ ከድሮው የኃጢአተኞች ማህበረተኝነት ወጥተው ወደ ሰማያዊው የብርሃን ህብረት ገቡ። 
እንደዚህ በመሆናቸው በኢየሱስ ክርስቶስ የተጀመረውን የሥላሴን ባህርይ ክርስቶስ ካረገም በኋላ ይተርኩትና ይገልጹት ጀመር። ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱ እንደርሱና እንደ አባቱ አንድ ይሆኑ ዘንድ ሲጸልይ ያንን እርሱ የገለጠላቸውንና በህይወቱ በነርሱ ውስጥ የዘራውን ሕይወት ይኖሩት ይገልጡት ዘንድ መፈለጉን ነው። ከዘላለም ተሰውሮ የነበረው ሚስጢር የሆነው የሥላሴ ሕይወት በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ እንደታየና እንደተተረከ አሁን እርሱ ወደ አባቱ ካረገም በኋላ ይህ ሕይወት በቤተ ክርስቲያን እንዲተረክ ነው እኔና እናንተ በዓለም ያለነው። በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ የህያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ አንድም ሶስትም እንደሆኑ በነርሱ ውስጥ ያለው ፍቅር አንድነትና ህብረት ለኛ እንደተሰጠና እግዚአብሔር በክርስቶስ ወንጌል ሰዎችን ወደዚህ ህብረት እየጠራ እንደሆነ መታየትና መተረክ የሚችለው በኛ ሕይወት ከተገለጠ ብቻ ነው። በሥላሴ ውስጥ ያለውን የዘላለም ሕይወት ሰዎች እንዲያገኙና ከዚህች የጨለማ ዓለም ወጥተው ከክፉውና ከጠማማው ትውልድ ተለይተው ወደዚህ ህብረት መግባት የሚችሉት ይህ የሚያስቀና የሥላሴ መልክ በቤተ ክርስቲያን በኛ በምእመናን ሲገለጥ ነው።

ሁለት ታላላቅ ብርሃናት
ይህ ሕይወት የጸሐይንና የጨረቃን የብርሃን ነጸብራቅና የብርሃን ዑደት ይመስላል። እግዚአብሔር በአራተኛው ቀን የፈጠራቸው ጸሐይና ጨረቃ እንዴት እንደተፈጠሩ እንመልከት
ትልቁ ብርሃንና ትንሹ ብርሃን

“እግዚአብሔርም አለ፦ ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ ለምልክቶች ለዘመኖች ለዕለታት ለዓመታትም ይሁኑ፤በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር ብርሃናት ይሁኑ፤ እንዲሁም ሆነ። እግዚአብሔርም ሁለት ታላላቆች ብርሃናትን አደረገ ትልቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፥ ትንሹም ብርሃን በሌሊት እንዲሰለጥን ከዋክብትንም ደግሞ አደረገ። እግዚአብሔርም በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር አኖራቸው፤ በቀንም በሌሊትም እንዲሠለጥኑ፥ ብርሃንንና ጨለማንም እንዲለዩ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አራተኛ ቀን።” ዘፍ.1፤14-19
በዚህ ቃል ትልቁ ብርሃን የተባለው ጸሐይ ስትሆን ትንሹ ብርሃን የተባለችው ደግሞ ጨረቃ ናት። ከነዚህ ብርሃናት ሁለት ዋና ዋና ባህርያትን እናስተውል። አንደኛ ጸሐይ የብርሃን ምንጭ ስትሆን ጨረቃ ግን የራስዋ ወይም ከራስዋ የሚመነጭ ብርሃን የላትም። ሁለተኛ ትልቁ ብርሃን የተባለችው ጸሐይ እንድትሰለጥን የተደረገችው በቀን ሲሆን ጨረቃ ደግሞ በሌሊት ነው። ጸሐይ በሰለጠነችበት ወይም በገዛችበት ጨለማ ወይም ሌሊት የለም። ጨረቃ በምትገዛበት ግን ሌሊት አለ። ጨረቃ የራስዋ ብርሃን ስለሌላት በምትገዛበት ሌሊት የምታበራውን ብርሃን የምታገኘው ከጸሐይ ነጸብራቅ ነው። ይህ የእኛ የክርስቲያኖች የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ምሳሌ ነው። የዓለም ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር። ዮሐ.1፤9 
 አምላክ ዘእም አምላክ ብርሃን ዘእምብርሃን የሆነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ የሚያምንብኝ ከሞት ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም እያለ መጣ። እርሱ ሲመጣ በነቢዩ ኢሳይያስ የተተነበየው እንዲህ የሚለው ቃል ተፈጸመ።
“ኢየሱስም ዮሐንስ አልፎ እንደ ተሰጠ በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ፈቀቅ ብሎ ሄደ። ናዝሬትንም ትቶ በዛብሎንና በንፍታሌም አገር በባሕር አጠገብ ወደ አለችው ወደ ቅፍርናሆም መጥቶ ኖረ። በነቢዩም በኢሳይያስ፦ የዛብሎን ምድርና የንፍታሌም ምድር፥ የባሕር መንገድ፥ በዮርዳኖስ ማዶ፥ የአሕዛብ ገሊላ፤ በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፥ በሞት አገርና ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ። ከዚያ ዘመን ጀምሮ ኢየሱስ፦ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ይሰብክ ጀመር።” ማቴ.4፤12-17 
የዓለም ብርሃን የሆነውና ለሰው ሁሉ ሊያብራ የመጣው የብርሃን ምንጭ የሆነው ታላቁ ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ይህን ብርሃን በርሱ ብቻ እንዲቀር አላደረገም። ለሰው ሁሉ ሊያበራና ብርሃኑን ሊያንጸባርቅ እያበራ መጣ። ይህንን ብርሃኑን በትህትና በደስታ በጉጉት የተቀበሉት ሁሉ ይህንን ሕይወት የሆነ ብርሃን በነርሱ ላይ ሲያንጸባርቅ ነጸብራቁን ተቀበሉ። ይህንን ብርሃን እንደ ጨረቃ የተቀበሉትን ደቀመዛሙርቱን እንዲህ አላቸው።
“እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል። መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።” ማቴ.5:14-16
ጸሐይ በምትገዛበት ቀን ጨለማና ሌሊት እንደሌለ ሁሉ በእግዚአብሔርም ዘንድ ሌሊት ወይም ጨለማ የለም። ንጉሡ ዳዊት ሲናገር “ጨለማ በአንተ ዘንድ አይጨልምምና፥ ሌሊትም እንደ ቀን ታበራለችና፤ እንደ ጨለማዋ እንዲሁ ብርሃንዋ ነው።” ይላል። መዝ.139፡12
ከጸሐይ  የምትቀበለውን ብርሃን የምታንጸባርቀው ጨረቃ ግን ግዛትዋ በሌሊት ነው። ይህም ቤተ ክርስቲያንን የሚያመለክት ነው። ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን ብርሃን ተሞልታ የምታንጸባርቅ ብትሆንም ብርሃንዋን እንድትሰጥ ስለምትፈለግ ለዚህች በሌሊት ላለችው ዓለም የቀረበች ናት። በጨለማው ላይ በዚህ ዓለም ባለው ከባድ ሌሊት ላይ ለመሰልጠንና ከጸሐይ ያገኘችውን ብርሃን እያንጸባረቀች የትልቁን ብርሃንነት የምትመሰክር አካሉ ናት። ትልቁ ብርሃን ክርስቶስ ሲመለስ የዚህችን ዓለም ሌሊት ለዘለዓለም እስኪገፈው ድረስ የክርስቶስን የብርሃን መንግሥት እየተረከችና እየገለጠች በብርሃንዋ የብርሃንዋን ምንጭ እንዲያዩ ጨለማውን እየገፈፈች የብዙዎችን ዓይን ለመክፈት ምስክር ሆና በሰማያዊ ስፍራ  ተቀምጣለች። እግዚአብሔር ትልቁን ብርሃን ጸሐይንም ትንሹን ብርሃን ጨረቃንም ያስቀመጣቸው በጠፈር ላይ ነው። ሁለቱም በጠፈር ቢቀመጡም ለምድር ያላቸው ርቀት ግን የተለያየ ነው። ጸሐይ ከምድር ያላት ርቀት 92.96 ሚልዮን ማይል ሲሆን ጨረቃ ከምድር ያላት ርቀት ግን 238.900 ማይል ነው። ስለዚህ ለምድር የምትቀርበው ብርሃን ትንሽዋ ብርሃን ጨረቃ መሆንዋን እናያለን። ይህም ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ በሰማያዊ ስፍራ የተቀመጠች ብርሃን ብትሆንም ራስ ከሆነላት ጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ የምትቀበለውን ብርሃን  በጨለማ ለተወረሰው ለዚህ ዓለም ለማብራት ግን ለምድር ቀረብ ብላ ግን በሰማያዊ ስፍራ የተቀመጠች ናት። ምድር ግማሽ ፊትዋን ከጸሐይ ስትሰውርና ከጸሐይ ግዛት ስትርቅ የምድር ግማሽ በሌሊት ይወረሳል። በዚህን ጊዜ ከጸሐይ ብርሃን በመራቅዋ ጨለማ የወረሰውን የምድር ፊት ቀረብ ብላ ያለችው ጨረቃ የጸሐይን ብርሃን ተቀብላ ለምድር ታቀብላታለች። እንደዚሁም የዓለም ብርሃን የሆነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ የቤዛነት ሥራውን ከፈጸመ በኋላ ወደ ክብሩ ሲመለስ ብርሃኑን ያንጸባረቀባትንና የሚያንጸባርቅባትን ቤተ ክርስቲያን የክብር ወንጌል ብርሃን የሆነውን ክርስቶስን  ሞልቶ ለዚህ ዓለም እንድታበራ ለምድር በቀረበ ሰማያዊ ስፍራ አስቀመጣት። ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ድንቅ የማንጸባረቅ አገልግሎት ሲናገር፦
“ጳውሎስና በርናባስም ገልጠው፦ የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ ይነገር ዘንድ ያስፈልጋል፤ ከገፋችሁትና የዘላለም ሕይወት እንዳይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ ግን፥ እነሆ፥ ወደ አሕዛብ ዘወር እንላለን። እንዲሁ ጌታ፦ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለማዳን ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ ብሎ አዞናልና አሉ። አሕዛብም ሰምተው ደስ አላቸው የእግዚአብሔርንም ቃል አከበሩ፥ ለዘላለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ አመኑ፤” ሐዋ.13፡46-48
እንደዚሁም በሌላው መልእክቱ ስለዚህ ብርሃን እና እንዴት እንደሚበራ ሲመሰክር።

“ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉ ነው። ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፥ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ። ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደ ሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና፥ ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባሪያዎች እናደርጋለን። በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ፦ በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና።” 2.ቆሮ.3-6
እንግዲህ በዚህ ሁሉ የምንረዳው እውነተኛይቱ ቤተ  ክርስቲያን በዚህ ዓለም ያለችው ይህንን ሰማያዊ ብርሃን ይህንን የሥላሴ ሕይወት ይህንን የተለየ ህብረት ፍቅርና አንድነት ለማንጸባረቅና እግዚአብሔርን ለመተረክ ነው።
ይህ ሚስጢር ለበራላችሁና ከእውነተኛው ጸሐይ ከክርስቶስ ኢየሱስ ብርሃንን ተቀብላችሁ በዚህች ጨለማ ዓለም ለማንጸባረቅ የተመረጣችሁ ሁሉ በዚህ ሕይወት ነጸብራቅ ትመላለሱ ዘንድ የብርሃኑ ሕይወት ይብዛላችሁ።

← Teachings