January 9, 2021
እብዶች ብንሆን፥ ለእግዚአብሔር ነው።
የእግዚአብሔር ፍቅር
"እብዶች ብንሆን፥ ለእግዚአብሔር ነው፤ ባለ አእምሮዎች ብንሆን፥ ለእናንተ ነው።ይህን ስለቆረጥን የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ፤በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ።" 2. ቆሮ 5:13-15
በመምህር ጸጋ
እብድነት በአካል ከዚህች ዓለም ሳይወጡ በውስጣዊ ማንነት በልብና በኣእምሮ መውጣት ነው፡፡ እብድነት በራስ ዓለም መኖር ነው፡፡ እብዶች የየራሳቸው ኣለም አላቸው፡፡ ለዚህች ኣለም አብደው ለራሳቸው ዓለም ይነቃሉ፡፡ በሌላ እውነታ በሌላ አስተሳሰብ ይኖራሉ፡፡ ብቻቸውን ማውራት፤ ውጭ መተኛት፤ ግዴለሽ መሆን፤ አንድ ልብስ ብቻ መልበስ፤ የተቀዳደደ ልብስ መልበስ፤ አላማ አልባ ህይወት መኖር የእብዶች እውነታዎች ነው፡፡ ማኅበረሰቡ ነባራዊ ብሎ በመቀበል ከሚመላለስባቸውን ልማዶች ወጎችና ባህሎች ውጭ የሚመላለስ ሰው እብድ ሊባል ይችላል፡፡ ባለ ኣእምሮ ነኝ ለሚለው ሰው የእብዶች ዓለም እንደማይገባው ሁሉ ለነርሱ ደግሞ የባለ ኣእምሮው ኣለም አይገባቸውም፡፡ እነርሱ ሌላው ጥሩ ልብስ መልበሱ ለራሱ ብዙ መጨነቁ በእቅድ መኖሩ እና ብዙ ነገር ለማግኘት ደፋ ቀና ማለቱ ባለ ኣእምሮ ነኝ የሚለው ደግሞ የነርሱ እራቁትነትና ግዴለሽ መሆን ለምንም አለመጨነቅ ራሳቸውን መጣል ይገርመዋል ያሳዝነዋል፡፡ እብዶች ከዚህች ኣለም ማህበራዊ ህይወት የተገለሉና እንዳሉ እንኳ የማይቆጠሩ ናቸው፡፡ እብደት ከተለመደው ሁሉም ሰው ከተቀበለውና ከሚመላለስበት የህይወት ስርአት ውጭ መውጣት ማለት ነው ክርስትና ከተገለጸባቸው አንዱ እብድነት ነው፡፡
ይህንን እንደምሳሌ በመውሰድ ስለ ክርስትና ህይወት እንመልከት
ክርስቲያን የሆነ ሰው ከላይ እንዳየናቸው የዚህ ኣለም እብዶች ጨርቁን ጥሎ ባይሄድም ወይም ራሱን ባይስትም ነገር ግን ከነርሱ ጋር የሚያመሳስለው ነገር አለ፡፡ ይኸውም ከዚህች ኣለም በተቃራኒ መቆሙና የዚህች ጨለማ ኣለም ተቃራኒ የሆነ ህይወት መኖሩ ነው፡፡ ክርስትና ይህች ኣለም ወይም ምድራዊ ዘመዶቻችን ትክክል ብለው ከሚመላለሱት የህይወት ሥርአት እና እሽክርክሪት ያወጣናል፡፡ ክርስትና የራሱ ስርአተ ዑደት እሽክርክሪት ወይም ዛቢያ ያለው ሰማያዊ ህይወት ነው፡፡ ክርስትና መዘውሩ ክርስቶስ ነው፡፡ ክርስትና መሠረቱ ሰማያዊው መንግሥት ነው፡፡ ስለዚህ እኛ እውነተኛ ክርስቲያኖች ለአለማውያን ሞኞችና እብዶች ነን፡፡ ለዓለም ሳታብዱ ክርስቲያን መሆን አትችሉም፡፡ ክርስትና ሁሉም ሰው ተስማምቶ ከሚሮጥበት የዓለም የሩጫ ማሽን ትሬድሚል ወይም አዙሪት የሚያወጣ ሰማያዊ ህይወት ነው፡፡ የክርስትና መሠረትና ፍጻሜ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎቱን ሲጀምር በመጀመሪያ የተሰጠው ስም “እብድ” የሚል ነበር፡፡
ክርስቶስ ለዚህች ምድር ሚስጢር የሆነ አምላክ ነው፡፡ ማንነቱ ሚስጢር፤ ውልደቱ ሚስጢር፤ ህይወቱ ሚስጢር የሆነ አምላክነትንና ሰውነትን አዋህዶ የያዘ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው፡፡ አንዳንዱ የአዳም ልጅ፤ ሌላው የዮሴፍ ልጅ፤ አንዳንዱ ነቢይ፤ ሌሎቹ ሐሰተኛ ወዘተ ብለውታል፡፡ እንኳንስ ሌላው ህዝብ ቀርቶ ሁሉን ትተው የተከተሉት እና ቀረብ ብለው ይከተሉት የነበሩት ደቀ መዛሙርቱም በፍቅሩ ተነድፈው ቢከተሉትም ማንነቱን ግን ሙሉ በሙሉ አያውቅም ነበር፡፡ ለዚህም ነው ሰዎች የሰውን ልጆች ማን ይሉታል? ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ
“እነርሱም፦ አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት። ጌታም ጥያቄውን ወደነርሱ መለስ ብሎ “እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው። ጥያቄው ለነርሱም ቀላል አልሆነም፡፡ እንደ እውነቱ ሁሉም በአንድ ድምጽ ማን መሆኑን መናገር ነበረባቸው፡፡ ነገር ግን የክርስቶስን ማንነት እግዚአብሔር ያልገለጠለት ሰው ሊያውቀው አይችልምና እነርሱም ዝም አሉ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ግን የኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ተገለጠለት፡፡ “ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፦ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ።” አለው፡፡ {ማቴ. 16: 14- 17}
እንግዲህ ይህንን ማንነቱን ያላወቀችው ኣለም ክርስቶስን እስከመጨረሻው አሳደደችው፡፡
የምንኖሩባት ኣለም ክርስቶስን ጠልታ የሰቀለች፤ የምትኖሩበት ማሕበረሰብ ፈጣሪውን ክርስቶስን “አብደሃል” ያለ ሕብረተሰብ ነው፡፡ ክርስቶስ በነበረበት ማኅበረሰብ እብድ መባሉ ለማመን የሚከብድና አስገራሚ ነገር ቢሆንም ቃሉ ይህንን ያስረግጥልናል እናንብበው፡፡
ቅዱስ ማርቆስ ሁኔታውን እንዲህ ይተርክልናል፡፡
“ወደ ቤትም መጡ፤ እንጀራም መብላት ስንኳ እስኪሳናቸው ድረስ እንደ ገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ።ዘመዶቹም ሰምተው፦ አበደ ብለዋልና ሊይዙት ወጡ።ከኢየሩሳሌም የወረዱ ጻፎችም፦ ብዔል ዜቡል አለበት፤ ደግሞ፦ በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል ብለው ተናገሩ። እነርሱንም ወደ እርሱ ጠርቶ በምሳሌ አላቸው፦ ሰይጣን ሰይጣንን ሊያወጣው እንዴት ይችላል?መንግሥትም እርስ በርስዋ ከተለያየች ያች መንግሥት ልትቆም አትችልም፤ቤትም እርስ በርሱ ከተለያየ ያ ቤት ሊቆም አይችልም።ሰይጣንም ራሱን ተቃውሞ ከተለያየ፥ መጨረሻ ይሆንበታል እንጂ ሊቆም አይችልም።ነገር ግን አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ ዕቃውን ሊበዘብዝ የሚችል የለም፥ ከዚያም ወዲያ ቤቱን ይበዘብዛል።እውነት እላችኋለሁ፥ ለሰው ልጆች ኃጢአት ሁሉ የሚሳደቡትም ስድብ ሁሉ ይሰረይላቸዋል፤በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚሳደብ ሁሉ ግን የዘላለም ኃጢአት ዕዳ ይሆንበታል እንጂ ለዘላለም አይሰረይለትም። ርኵስ መንፈስ አለበት ይሉ ነበርና።” ማር 3፡20-30
ክርስትና ቆሞ ሲሄድ ክርስቶስ ነው፡፡ ክርስትና ክርስቶስ ተዘርቶ የበቀለ አዝመራ ነው፡ ክርስቶስ ለትውልዱ እብድ ነበር፡፡ ከነበረው ሲስተም፤ ከፖለቲካው፤ ከመቅደሱና ከሃይማኖቱ መሪዎች ውጭ ስለነበር አገልግሎቱን ሲጀምር “አበደ” ተባለ፡፡ ልጃሁ አብዶአል የሚል ወሬ ለቤተሰቡ ተላከ ተደናግጠው ሊያገኙት መጡ፡፡
"ክርስትና ቆሞ ሲሄድ ክርስቶስ ነው፡፡ ክርስትና ክርስቶስ ተዘርቶ የበቀለ አዝመራ ነው፡ ክርስቶስ ለትውልዱ እብድ ነበር፡፡ ከነበረው ሲስተም፤ ከፖለቲካው፤ ከመቅደሱና ከሃይማኖቱ መሪዎች ውጭ ስለነበር አገልግሎቱን ሲጀምር “አበደ” ተባለ፡፡ ልጃሁ አብዶአል የሚል ወሬ ለቤተሰቡ ተላከ ተደናግጠው ሊያገኙት መጡ፡፡"
በዚህ ክፍል በጣም አስገራሚ የሆነ ነገር እናስተውላለን፡፡ በዘመኑ በአይሁድ ማኅበረሰብ ተቀባይነት የነበራቸውና የሃይማኖት መሪዎች የሆኑት ፈሪሳውያን ብዙ ሕዝብ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሰበሰብ አዩና በቅናት መንፈስ ተሞልተው እርሱ መናፍስትን እያወጣ ያለው በአጋንንት ኃይል ነው ማለት ጀመሩ፡፡ እርሱም ሰይጣን ሰይጣንን ሊያወጣው እንዴት ይችላል? ሁለቱ የአንዱ መንግሥት ክፍል እስከሆኑ ድረስ አንዳቸው የሌላኛው ጠላት ሊሆኑ አይችሉም፡፡ እርስ በርስ የምትለያይ መንግሥት ደግሞ ትጠፋለች፡፡ ሰይጣንም እርስ በርሱ የሚለያይ ከሆነ መንግሥት አይኖረውም ነበር፡፡ ቤትም እንኳ የሚቆመው ተደጋግፎ ነው እንጂ ግድግዳው ከሌላው ግድግዳ መሠረቱ ከግድግዳው ከተለያየ እንደሚፈርስ ገለጠላቸው፡፡
ከህዝቡ አለቆች ጋር በድፍረት በመነጋገሩና ስህተታቸውን በመግለጡ ብዙ ህዝብ እንድሰማው መሰብሰቡን ያዩ ሰዎች “አብዶአል” የሚል ስም ሰጡት፡፡ እርሱ ግን ምሳሌውንም በመቀጠል አንድ ሰው ከርሱ የሚበልጠውን ኃይለኛ ሳያሸንፍና ሳያስር በኃይለኛው ቤት ያለውን ሊበዘብዝ እንደማይችል ይህም ማለት አጋንንትን ከሰው ላይ እያወጣ ያለው ባለቤቱ ከነበረው ከሰይጣን ይልቅ የበረታ ስለሆነ እንደሆነ ነገራቸው፡፡ በመጨረሻም በብኤል ዜቡል አጋንንትን ያወጣል በማለት በርሱ ውስጥ ሆኖ አጋንንትን እያባረረ ያለውን የእግዚአብሔርን መንፈስ ስለሆነ እየተቃወሙ ያሉት መንፈስ ቅዱስን የሰደበ ኃጢአቱ አይሰረይለትም በማለት በጣም አስደንጋጭ የሆነ ነገር ተናገራቸው፡፡
በእንደዚህ ኣይነት ሁኔታ የእግዚአብሔርን መንግሥት እየገለጠና ሕዝቡም በታላቅ ደስታ እርሱን ለመስማት ቤቱን አጨናንቀውት ባለ ሁኔታ ነበር “ልጃችሁ አብዶአል” የሚል ወሬ ወደ ቤተሰቦቹ የደረሰው፡፡ ቤተሰቦቹም አበደ ብለዋልና ሊይዙት መጡ ይላል፡፡ ሊይዙት መጡ የሚለው ቃልም እጅግ ያስገርማል፡፡ ልክ አንድን ኣእምሮውን የሳተና ትእዛዝ የማይቀበልን ሰው ሰዎች ተረባርበው በጉልበት እንደሚይዙት ኢየሱስ ክርስቶስ አበደ ብለው ሊይዙት መጡ፡፡ የሰው ሐሳብ እጅግ ይገርማል፡፡ በታላቅ ኃይል እየተንቀሳቀሰና እየተገለጠ የእግዚአብሔርን መንግሥት እየገለጠ የዲያብሎስን መንግሥት እያፈረሰ ምርኮኞችን ነጻ እያወጣ ያለውን ኃያሉን ንጉሥ የዳዊትን ልጅ ክርስቶስን በነርሱ ጉልበት ሊይዙት በፈቃዳቸው ሊያስሩትና ሊገድቡት መጡ፡፡ በእግዚአብሔር እይታ ያበዱት እነርሱ ነበሩ፡፡ እንዴት ሰው እግዚአብሔርን ሊይዝና ሊያስቆም ይነሳል? ይህንን ያልተረዱት ግን ሞከሩት፡፡
ታሪኩ እንዲህ ይቀጥላል፡፡ እናቱና ወንድሞቹ አበደ የሚለውን ወሬ ሰምተው ከመጡ በኋላ ከህዝቡ ብዛት የተነሳ መግባት አቃታቸው፡፡
“እናቱና ወንድሞቹም መጡ በውጭም ቆመው ወደ እርሱ ልከው አስጠሩት። ብዙ ሰዎችም በዙሪያው ተቀምጠው ነበሩና፦ እነሆ፥ እናትህ ወንድሞችህም በውጭ ቆመው ይፈልጉሃል አሉት። መልሶም፦ እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነ ማን ናቸው? አላቸው። በዙሪያው ተቀምጠው ወደ ነበሩትም ተመለከተና፦ እነሆ እናቴ ወንድሞቼም። የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ ነው እኅቴም እናቴም አለ።” ማር 3፤31- 35
ቅዱስ ማቴዎስ የበለጠ ሲገልጥልን ደግሞ ጌታችንና መድኃኒታችን እጁን ዘርግቶ እያሳየ እንሆ ወንድሞቼ የሚለው ሁሉንም ትተው በመንግሥቱ ኃይል ተስበው በፍቅሩ ተማርከው የተከተሉትና ወደርሱ ጠጋ ብለው የተቀመጡትን ደቀ መዛሙርቱን እንደሆነ ያሳየናል፡፡
“እጁንም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ፦ እነሆ እናቴና ወንድሞቼ፤ በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ እኅቴም እናቴም ነውና አለ።” ማቴ. 12:49-50
እነዚህ ክርስቶስ ወንድሞቼ የሚላቸው አበደ ከሚለው ዓለም ተለይተው ከርሱ ጋር የሆኑ ናቸው፡፡
ስለዚህ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ማለት ኢየሱስን አበደ ከሚለው ማኅበረሰብ ተለይቶ አበደ ከተባለው ጋር አንድ በመሆን ለዚህች ዓለም ያበደ ነው፡፡ በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱም ተከትለውት አበዱ ማለት ነው፡፡ ኣለም ክርስቶስን ስላላወቀችው የርሱንም ተከታዮች አላወቀቻቸውም ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በአንደኛይቱ መልእክቱ ሲመሰክር
“የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ፥ እንዲሁም ነን። ስለዚህ ምክንያት ዓለም እርሱን ስላላወቀው እኛን አያውቀንም።” ይለናል፡፡ {1ኛ የዮሐንስ መልእክት 3፤1}
እርሱን ያላወቀችው ዓለም የርሱ የሆኑትን እውነተኛ ክርስቲያኖች ልታውቃቸው አትችልም፡፡ ብዙ ያላደጉ ክርስቲያኖች የሚቸገሩት ዓለምም እግዚአብሔርም እንዲያውቃቸው ስለሚፈልጉ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ከሆንን ግን እርሱን ያላወቀች ዓለም እኛን ልታውቀን አትችልም፡፡ እርሱን ሳታውቅ እኛን ካወቀችን ከርሱ የተለየን ወይም ከርስዋ ጋር ነን ማለት ነው፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሆንን ግን ለዓለም ሁልጊዜ ሚስጢርና እንቆቅልሽ ነን፡፡ ያዩናል ግን አያውቁንም፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንኳንስ ለዚህ ዓለም በሰማያዊ ስፍራ ላሉትም ሚስጢር ናት፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ከእግዚአብሔር ተወልደን የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንን ነው፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ዮሐንስ “ዓለም ክርስቶስን እንደማታውቀውና እኛንም እንደማታውቀን ከመናገሩ በፊት የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደሰጠን እዩ እንዲሁም ነን” በማለት ነው የሚጀምረው፡፡ ዓለም እንዳታውቀን ያደረገው ከእግዚአብሔር መወለዳችን ነው፡፡ ከእግዚአብሔር መወለድ በመንፈስ ቅዱስ የሚከናወን ድንቅ ሰማያዊ ሚስጢር ነው፡፡ ይህንን ድንቅ ሚስጢር ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ ሲነግረው እንዲህ አለው፡፡ “ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። ኒቆዲሞስም፦ ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? አለው። ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው። ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ። ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው።” የዮሐንስ ወንጌል 3፤3-8
የአባት ፍቅር
Join us today Membrs log inከዚህ በታች ያለውን የወንጌል ድምጽ እንዲሰሙ በታላቅ ፍቅር እንጋብዝዎታለን፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=5I8ey_UUVGAከመንፈስ የመወለድ ወይም ከላይ ከእግዚአብሔር የመወለድ ሚስጢር የሙሴን ህግ ጠንቅቆ ለሚያውቀው ለረቢው ለኒቆዲሞስ ለመረዳት የሚከብድ ነገር ሆኖበታል፡፡ እንደገና ወደ እናት ማህጸን መመለስና መወለድ መስሎታል፡፡ ሰማያዊው ረቢ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ይህ ሚስጢር ሰማያዊ እና በመንፈስ ቅዱስ የሚከወን እንደሆነ መሰከረለት፡፡ ከዚህም የተነሳ ከመንፈስ የተወለደ ሰው ባህርይ ምን እንደሚመስል ሲያስረዳው ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል ድምጹን ትሰማለህ ነገር ግን ከወዴት እንደመጣ ወዴትም እንደሚሄድ አታውቅም ከመንፈስ የተወለደም እንደዚሁ ነው አለው፡፡ ከመንፈስ ቅዱስ ተወልደን የእግዚአብሔር ልጆች ስንሆን ከዓለም እይታና እውቀት እንሰወራለን ድምጻችንን ወንጌላችንን ትሰማለች ከወዴት እንደመጣን ወዴትም እንደምንሄድ ግን ማወቅ አትችልም፡፡ ምህዋራችን በሰማይ ስለሆነ እንቅስቃሴአችን በእግዚአብሔር ፈቃድ የሚመራ ስለሆነ ዓለም ልታውቀውም ልትቆጣጠረውም አትችልም፡፡ የክርስትና ህይወት ከዓለም ጠቢባን እና ከምድር ፍልስፍና ውጭ ነው፡፡ በመሆኑም ከመንፈስ ቅዱስ ተወልደን የሥጋን ዓለም ስንለቅ እና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ መመላለስ ስንጀምር ለዓለም እንቆቅልሽ እንሆናለን፡፡ የዓለማውያን አካሄድና የኛ አካሄድ የነርሱ አስተሳሰብና የኛ ይለያያል፡፡ ሥጋና መንፈስ የብርሃንና የጨለማ ያህል የተለያዩ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከሥጋ የተወለደና ከመንፈስ የተወለደ በምንም ተአምር ሊግባቡ አይችሉም፡፡ አካሄዳቸውም ተቃራኒ ሲሆን ሊስማሙ የማይችሉ ጠላቶችም ናቸው፡፡ በመሆኑም እውነተኛ ክርስቲያን ማለትም ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ በሥጋ ካሉት የድሮ ዘመዶቹና ጓደኞቹ ሁሉ ጋር ሊስማማ አይችልም፡፡ በዚህን ጊዜ ሥጋውያኑ አበደ ይሉታል፡፡ የነርሱን የሥጋ ሥራ ባለመከተሉና እነርሱ በሚፈሱበት ቦይ ባለመፍሰሱ ለነርሱ እንደ እብድ ይቆጠራል፡፡ የርሱ መንገድና የነርሱ መንገድ ፈጽሞ የተለያየ ነው፡፡ ከመንፈስ ቅዱስ ዳግም የተወለደ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ፈቃድና ለእግዚአብሔር ፈቃድ ተወልዶአል፡፡ ሲወለድ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ገብቶአል፡፡ አሁን በርሱ ላይ የሰለጠነችው የእግዚአብሔር መንግሥት ናት፡፡ ምልልሱም ሐሳቡም የሰማዩ ፈቃድ ብቻ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሳናስተውል ስንቀር ሥጋውያንና ዓለማውያን ሰዎች እንዲረዱን ራሳችንን ለማብራራት እንሞክራለን፡፡ ይህ ግን በጨለማ ያለን ሰው ማየት አለብህ ብሎ የማስገደድ ያህል ነው፡፡ ነገር ግን ዓይናቸው ተከፍቶ እንደኛ ዳግም ተወልደው ወደ ብርሃን መንግሥት እስካልገቡ ድረስ ሊረዱን አይችሉም፡፡ ዳግም ልደት የልዩነቱ ጅማሬ ነው፡፡ ዳግም የተወለደ ሰው በሥጋ ካለ ሰው ጋር በዘር ተለያይቶአል፡፡ ነፋስ እንደማይጨበጥ ሁሉ ከመንፈስ የተወለዱ ሁሉ ለዚህች ዓለም አይገኙም አይጨበጡም፡፡ ከመንፈስ የተወለዱ ሁሉ የዚህች ዓለም ክፍል አይደሉም፡፡ በዚህች ዓለም ያሉት የተወለዱባትንና የገቡባትን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማምጣት ነው፡፡ በዳግም ልደት ወደ ላይኛው ጽንፈ ክበብ ገብተናል፡፡
ስለዚህ እነዚህ በክርስቶስ ፍቅር ተማርከው የተከተሉትና እርሱ ወዳለበት ጽንፈ ክበብ የገቡት ክርስቲያኖች እንደ እብዶች ተቆጠሩ፡፡ እርሱን ያሳደደችው ዓለም እነርሱንም አሳደደቻቸው፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህ እንደሚመጣ አስቀድሞ አይቶ እንዲህ ብሎአቸው ነበር “ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ። ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል። ባርያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ። እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው እንደ ሆኑ ቃላችሁን ደግሞ ይጠብቃሉ። ዳሩ ግን የላከኝን አያውቁምና ይህን ሁሉ ስለ ስሜ ያደርጉባችኋል።” የዮሐንስ ወንጌል 15፤18-21
እንደተናገረውም ዓለም ናቀቻቸው አሳደደቻቸው፡፡ ከዓለም ስርዐተ ምህዋር ስለወጡ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ስለተነዱ ለዓለም እንግዶች ሆኑ፡፡ ተናቁ መዘበቻ ሆኑ እንደ እብድም ተቆጠሩ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሁኔታ ሲናገር “ለዓለም ለመላእክትም ለሰዎችም መጫወቻ ሆነናልና፤ እግዚአብሔር እኛን ሐዋርያቱን ሞት እንደ ተፈረደባቸው ሰዎች ከሁሉ ይልቅ የኋለኞች እንዳደረገን ይመስለኛልና።” ይለናል፡፡ {1 ቆሮ 4፤9} ዓለም አልተገባቻቸውምና በየዋሻው በየተራራው ተቅበዘበዙ እንደ ዱር አራዊት ታደኑ፡፡ ስለዚህም ይኸው ቅዱስ ሐዋርያ በሌላኛው መልእክቱ ሲናግር “ስላንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን” ብሎ በደስታ ተቀኘ፡፡
በክርስቶስ ፍቅር ተማርኮ ወደዚህ የእብዶች ማኅበር ዘግየት ብሎ የገባው ቅዱስ ጳውሎስም ቅዱሱን ወንጌል በንጉሥ አግሪጳ ፊት ሲሰብክ ከንጉሡ ጋር የነበረው የይሁዳ ገዢ ፊልክስ ሁሉም ነገር ከኣእምሮው በላይ የሆነ ሞኝነት ስለሆነበት
“ፊስጦስ በታላቅ ድምፅ፦ ጳውሎስ ሆይ፥ አብድሃል እኮ፤ ብዙ ትምህርትህ ወደ እብደት ያዞርሃል አለው። ጳውሎስ ግን እንዲህ አለ፦ ክቡር ፊስጦስ ሆይ፥ የእውነትንና የአእምሮን ነገር እናገራለሁ እንጂ እብደትስ የለብኝም። በእርሱ ፊት ደግሞ በግልጥ የምናገረው ንጉሥ ይህን ነገር ያውቃል፤ ከዚህ ነገር አንዳች እንዳይሰወርበት ተረድቼአለሁና፤ ይህ በስውር የተደረገ አይደለምና።” ሐዋ።26፤24-26
ለነገሥታትና ለጥበበኞች የእግዚአብሔር ወንጌል የክርስቶስ መሞትና ከሙታን መነሳት የእግዚአብሔር ጽድቅና ፍርድ ነገር በአጠቃላይ የመስቀሉ ቃል ሞኝነት ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሞኝ ስለተባለበት ወንጌል በሌላኛው መልእክቱ ሲናገር፡፡
“እብዶች ብንሆን፥ ለእግዚአብሔር ነው፤ ባለ አእምሮዎች ብንሆን፥ ለእናንተ ነው።
ይህን ስለቆረጥን የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ፤
በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ።” ይለናል፡፡
2 .ቆሮ 5፡13 -15
የእግዚአብሔር ለሆነው ሐሳብ ስለተሸነፍን የርሱ ፈቃድና ዓላማ መገለጫዎች ስለሆንን የራሳችንን አሮጌ ማንነት አጥተናል፡፡ ሰዎች የድሮ ማንነታችንን ፈልገው አጥተውታል ስለዚህ እብዶች፤ ራሳቸውን የሳቱ፤ ማንነታቸውን ያጡ፤ ብለውናል፡፡ እብዶች ብንሆንም ማለትም ራሳችንን ብናጣ ከማንነታችን ውጭ ብንሆንም ለእግዚአብሔር ነው ይለናል ሐዋርያው፡፡ ሰው የራሱን ማንነት ሲያጣ፤ ከክርስቶስ ጋር መነሳቱን አምኖ አዲስ ፍጥረትነትን ሲለብስ፤ ድሮ በሮጌው ማንነቱ ለሚያውቁት ሰዎች እየጠፋ ነው፡፡ ያንን የሚያውቁትን አሮጌ ሰው ሲያጡትና በርሱ ምትክ በእግዚአብሔር ሐሳብና ፈቃድ የተሞላ አዲስ ፍጥረት ሲያዩ ያንን ሰው አበደ ይሉታል፡፡ ምክንያቱም ቋንቋው ሐሳቡ ከነርሱ የተለየ ሰማያዊ ስለሆነ አይገባቸውምና ያበደ ይስመስላቸዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በመቀጠል የክርስቶስን ተከታዮች ወደዚህ ማንነት ያመጣቸውን ምክንያትና አካሄድ ሲዘረዝር “ይህን ስለቆረጥን የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና አንዱ ስለሁሉ ሞተ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ።” ይለናል፡፡ ወደዚህ፡ ዓለማውያን እብድነት ወደሚሉት ህይወት ያስገባን የክርስቶስ ፍቅር ነው፡፡ እርሱ ስለሁላችን በፍቅር መሞቱ እኛን ለራሳችን እንድንሞትና ለርሱ እንድንሆን አስገድዶናል፡፡ ስለዚህ የድሮ ማንነታችንን ለርሱ እንዲሞት ፈቅደን የርሱን ማንነት በመሞላታችን እብዶች ብንሆን ደስ ይለናል፡፡ ይህን የምናደርገው በፍቅሩ ተማርከን ተሸንፈን ነው፡፡ ፍቅሩ ማንነታችንን ጭምር አስክዶናል፡፡ እርሱ ራሱን ስለኛ ስላጣ ማለትም ነፍሱን ስለሰጠ ይህ ራሱን እስከመስጠት ያደረሰው ፍቅር እኛንም ማንነታችንን ስለርሱ እንድናጣ አድርጎናል፡፡ ስለዚህ አሁን እግዚአብሔር ይኖርብናል እንጂ እኛ አንኖርም እያለን ነው፡፡ ማበድ ማለት ከማንነት ውጭ መሆን ነው፡፡ ማበድ ማንነትን ሙሉ በሙሉ ማጣት ማለት ነው፡፡
እብደቱ አንዳንዶ እንደሚያደርጉት መጮህ ወይም ያለ ሥርአት መመላለስ አይደለም፡፡ ለዚህች ምድር በማይገባና በማይስማማ ሰማያዊ ሕይወት መመላለስ እንጂ፡፡ ይህ ቅዱስ እብደት ማንነትን ለክርስቶስ አሳልፎ መስጠትና በአዲሱ ህይወት ከርሱ ጋር መመላለስ ነው፡፡
ክርስቶስ እንዲኖርብን፤ እርሱ ህይወታችን እንዲሆን ራሳችንን አሳልፈን ስንሰጠው ያን ጊዜ ነው ለዚህች ዓለም ያበድነው፡፡ ያን ጊዜ ነው ዓለም ያጣችን፡፡ በዓለም እንኖራለን እንጂ ለዓለም አንኖርም፡ እያለን የለንም፡፡ ዓለም ለምንም ነገር ልትጠቀምብን አትችልም፡፡ በመንፈስ ተወልደን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ስንገባ እና ንጉሳችን እግዚአብሔር ሲሆን ዓለም በኛ ላይ የነበረው ስልጣንዋ ተገፎአል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በገላትያ መልእክቱ ከዓለም ጋር የተለያየንበት ድንቅ አሰራር ሲናገር
“ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ። በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና።” ይለናል፡፡ {ገላ 6 14 15 ፡፡} ከዓለም ጋር የተለያየነው በሞት ነው፡፡ እኛ ለርስዋ ሞተናል እርስዋ ለኛ ሞታለች፡፡ ስለዚህ በዓለም ፖለቲካና ሰው ሰራሽ ሃይማኖት ውስጥ ሁሉ ምንም ክፍል የለንም፡፡
ከዚህች ዓለም ስርአትና ፓለቲካ ጋር ተስማምተው የሚኖሩ ሁሉ አላበዱም በመሆኑም ክርስቲያን አልሆኑም፡፡ ብዙ የዋሆች ለዓለም ሞተን ክርስቲያን ሆነናል ካሉ በኋላ በፖለቲካው በዓመጹ፤ በዘረኝነቱ፤ ገንዘብን በማሳደዱ አንድ ላይ ሲሮጡ ይታያል፡፡ ለፖለቲካው ለገንዘቡ ለዘረኝነቱ ካልሞቱ ለየትኛው ዓለም ነው የሞቱት? ከዚህ ሌላ ዓለም የሚባል ነገር አለ እንዴ? ኧረ በጭራሽ የለም፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች በክርስቶስ መስቀል አብረው መሰቀላቸውን በማመን ይህችን ዓለም ተሰናብተዋታል፡፡ እንደዚሁም የጥምቀቱን መቃብር በመሻገር በዳግም ልደት የተባረከችውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ወርሰዋታል፡፡ ምልልሳቸውና ምህዋራቸው የመንፈሱ ነፋስ ነው፡፤ እርሱ ወደነፈሰበት ይነፍሳሉ፡ የበጉ ልጆች ሆነዋልና በጉ ወደሚሄድበት ሁሉ ይሄዳሉ፡፡ ከርሱ ለይቶ ሲያቅበዘብዛቸው የነበረው አሮጌ ሰው ስለተገፈፈላቸው አሁን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ የሆነ ሌላ ፈቃድ የላቸውም፡፡ ስለዚህ በዚህ ምድር ያላቸው ኑሮ እንደ ጌታቸው እንደ ክርስቶስ የእግዚአብሔርን መንግሥት መግለጥ ነው፡፡ የመንግሥቱ ኃይል እየተገለጠ አጋንንንት ሲወጡና ሰዎች ከእስራት ሲፈቱ ልክ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደተደረገው ሁሉ አበዱ መባላቸው የግድ ይሆናል፡፡ የድሮ የሥጋ ዘመዶቻችን እኛን ይዘው እነርሱ ወዳሉበት ጨለማ ለመመለስ መሞከራቸው አይቀርም፡፡
በውጭ ያሉና በውስጥ ያሉ ዘመዶቻችን
“ካበድን” ወይም ባለ አእምሮ ከሆንን በኋላ ሁለት ቤተሰብ ይኖረናል እነርሱም በውጭ ያሉና በውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ ባለ አእምሮዎች እንደሆንን የሚያውቁና ያበድን የመሰላቸው ናቸው፡፡
አስቀድመን ያየነውን የቅዱስ ማርቆስን ወንጌል ደግመን እናንብበው፡፡
“እናቱና ወንድሞቹም መጡ በውጭም ቆመው ወደ እርሱ ልከው አስጠሩት። ብዙ ሰዎችም በዙሪያው ተቀምጠው ነበሩና፦ እነሆ፥ እናትህ ወንድሞችህም በውጭ ቆመው ይፈልጉሃል አሉት። መልሶም፦ እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነ ማን ናቸው? አላቸው። በዙሪያው ተቀምጠው ወደ ነበሩትም ተመለከተና፦ እነሆ እናቴ ወንድሞቼም። የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ ነው እኅቴም እናቴም አለ።” ማር 3፤31- 35
በዚህ ክፍል ሁለት ቤተ ሰብ እናያለን፡፡ በውጭ ያሉና በውስጥ ያሉ፡፡ በውስጥ ያሉት ደቀ መዛሙርቱ ናቸው፡፡ የእግዚአብሔርን መንግሥት ተቀብለዋታል፡፡ ከንጉሱ አፍ በሚወጣው የህይወት ቃል ተማርከዋል፡፡ የአባቱን ፈቃድ ሊያደርጉ የራሳቸውን ፈቃድ ጥለዋል፡፡ ያላቸውን ሁሉ ትተው ክርስቶስን ተከትለዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸውን ሁሉ ትተው የርሱ ቤተሰብ ሆነዋል፡፡ በውጭ ያሉት ቤተሰቦቹ ከቤቱ ብቻ ሳይሆን ከሐሳቡም ውጭ ናቸው፡፡ ወደዚህች ዓለም የመጣበትን የኣባቱን ፈቃድ መፈጸም እብደት መስሎአቸው ከሥራው ሊያደናቅፉትና ሊወስዱት መጥተዋል፡፡ ሲመጡ ግን በሌሎች ዘመዶች ተከቦ አገኙት፡፡ ስለዚህ በውጭ ቆመው እያስጠሩት ነው፡፡ በጣም ደጎችና ለርሱ የሚያስቡ ናቸው፡፡ የኛ ወገን ሆኖ እንዴት አበደ ይባላል? በሚል ተቆርቋሪነት እነርሱ እብድነት ከሚሉት መንገድ ሊያድኑት ነው የመጡት፡፡ ነገር ግን ከቤቱ ብቻ ሳይሆን ከፈቃዱ ውጭ ነበሩ፡፡ በርሱ እየተገለጠች ያለችውን የእግዚአብሔር መንግሥት ነው ለመያዝ እየሞከሩ ያሉት፡፡ እርሱ ግን እጁን ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ እንሆ ወንድሞቼ እናቴ አባቴ በማለት አሳያቸው፡፡ የርሱ ወንድሞችና ቤተሰብ ወደራሳቸው ፈቃድ የሚጎትቱት ሳይሆኑ በርሱ ተሸንፈው የተጎተቱት ናቸው፡፡ የርሱ ቤተሰቦች በፍቅሩ ማእበል ተወስደው በእግዚአብሔር መንግስት ከርሱ ጋር የሚንፈላሰሱት ናቸው፡፡ በኛም እየሆነ ያለው ይኸው ነው፡፡ ለሥጋ ቤተሰቦቻችን አብደንባቸዋል፡፡ እነርሱን ካሰራቸው ዓለማዊ ወግና ሥርዓት ልማድና ምድራዊነት እስራት በመንፈሱ ኃይል በጣጥሰን ስለወጣን አበዱ ይሉናል፡፡ መጀመሪያውኑ ጤነኞች ብንሆን ኖሮ አሁን አበድን ቢባል አይገርምም፡፡ ድሮውንም በሰይጣን ምክንያት የሳትንና ያበደን፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ቤት የጠፋን እና የኮበለልን የክብር ልብሳችንን ትተን ቅጠል ያገለደምን መሆኑ ተረስቶ አሁን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ስንመለስ አበድን መባሉ ግን የትክክለኛዎቹ እብዶች ወሬ ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው አንድ ሰው ጨርቁን ጥሎ በአደባባይ ሲራቆትና ማድረግ የማይገባውን ሲያደርግ አበደ ይባላል፡፡ ይህንን በመንፈሳዊ ትርጉሙ ስናይ በመጀመሪያ ያበደው የሰው ልጆች አባት የሆነው አዳም ነው፡፡ አዳም ያበደው ክብሩን ገፎ ቅጠል ሲለብስ አይደለምን? እስካሁንም ድረስ እብደቱ ብሶበት በንስሐ ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ የክብር ልብሱን ከመልበስ ይልቅ የቅጠል ልብሱን እያሻሻለና እያዘመነ በዚህች ዓለም ይቅበዘበዛል፡፡ ይህ ያልገባቸው የድሮ ዘመዶቻችን እነርሱ ራሳቸው የእብድ ዘር መሆናቸውን ስለማያውቁ ከአዳም እብደት ወጥተን ወደ ክርስቶስ ስንጠጋና በርሱ ፈቃድ መመላለስ ስንጀምር አበዱ ይሉናል፡፡ ይህም በክርስቶስ በጌታችን የጀመሩት ስለሆነ አይገርመንም፡፡ በመሆኑም ከዓለምና ከሥጋ ዘመዶቻችሁ ለሚሰጣችሁ ስም ብዙ አትደነቁ፡፡ ከምንከተለው ከቅዱሱ ጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ የበለጠ ስም አይሰጣችሁም፡፡ የጽድቅ መሠረትና መለኪያ የሆነው እርሱ አበደ እና ሳተ ከተባለ እኛማ በርሱ ሥራ ከዚህች የእብዶች ማጎሪያ ከሆነች ዓለም ያመለጥን ደካሞች ብዙ ስም ቢሰጠን ምን ይገርማል፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን አምነው ስንከተለው የሚደርስብንን አስቀድሞ በማየት እንዲህ ብሎ ነበር፡፡
“ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።” ማቴ 5፤11-12
ስለዚህ የጌታችንን እና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል በማሰብ ሁላችንንም እንጽናና፡፡
Facebook-f Youtube