November 18, 2021
The Glory of the Image of His Son
የልጁ መልክ ከፍታ።
«እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን።» 2.ቆሮ.3፡18
በመምህር ጸጋ
አይ ብርሃን ደስ ማለቱ የማይታየውን ማሳየቱ። በተለይ የቃሉ ብርሃን በበራ ቁጥር አባታችንና ዓላማውን ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። ይህ መልእክት የመጠራታችን ዓላማ ደረጃ በደረጃ ፍንትው አደርጎ በማሳየት የኋላችንን እየረሳን በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን የመጥራት ዋጋ ለማግኘት እንድንዘረጋ ያበረታታናል።የእግዚአብሔር ልጅ መሆንን ከሲኦል ወይም ከማንኛውም ቅጣትና ፍርድ የማምለጫ መንገድ ብቻ አድርጎ ከማሰብ ወጥተን ወራሾች ልንሆንን መወለዳችንንና የተባለልንን ርስት አሟጠን እስክንወርስ ድረስ ማደግ እንደሚያስፈልገን በማየት ከተቀመጥንበት የመዳንና የልጅነት መንደር ተነስተን ለፍጻሜው ክብር ጉዞን እንጀምራለን። ጉዞአችን የመሰላል ጉዞ መሆኑን በመረዳትም ካንዱ ደረጃ ወደሌላው ለመራመድ እንተጋለን።
ያእቆብ ከወንድሙ ኮብልሎ በሄደ ጊዜ በሎዛ ያየው መሰላል ለመንሳዊ ጉዞአችን ትልቅ ትርጉም አለው። መሰላል ከምድር እስከ ሰማይ ተተክሎ በላዩም እግዚአብሔር ቆሞበት መላእክት ሲወርዱበትና ሲወጡበት አየ። ከዚያም የክርስቶስ ምሳሌ የሆነውን ተንተርሶት የነበረውን ድንጋይ በማቆምና ዘይት በመቀባት የእግዚአብሔርን ቤት መሠረት አስቀመጠ። ይህ መሰላል ራሱ ክርስቶስ እንደሆነ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ይመስክራል።«ናትናኤልም መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ አለው።ኢየሱስም መልሶ፦ ከበለስ በታች አየሁህ ስላልሁህ አመንህን? ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ አለው።እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ አለው» (ዮሐ.1፡50-52)
አዎ ክርስቶስ ሰማይንና ምድርን ያገናኘ የማይነካካውን ያነካካ እውነተኛ መሰላል ነው። ለመሆኑ መሰላል ምንን ያሳየናል? መሰላል ቆመን ልንደርስበት ወደማንችልበት ከፍታ የምንወጣበት ነገር ነው። ስለዚህ እግዚአብሔርና የመጥራቱ ዋጋ ባለንበት ሆነን ልንደርስበት የማንችል ከፍ ያለ ነገር ነው። እጅጉን ከፍ ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ ከሐሳባችን ጋር ሲነጻጸር ሰማይ ከምድር እንደሚርቅ ወደሚርቀው ሐሳቡ ለመድረስ መሰላል ያስፈልገናል። ያለንበትን ዝቅታ ርቀት ያወቀው እግዚአብሔርም ክርስቶስን ወደርሱ የምንደርስበት መሰላል አድርጎ ሰጥቶናል። ክርስቶስን እንደመሰላል ካወቅነው የመሰላልን አሰራርና አጠቃቀም ደግሞ መረዳት ይኖርብናል። መሰላል በአንድ እርምጃ ከታች እስከላይ የምንደርስበት ሳይሆን ብዙ ደረጃዎች ያሉትና ካንዱ ደረጃ ወደሌላው ደረጃ እየተራመድን የምንወጣበት ነው። መሰላልን «መሰላል» ያስባለው የኛን እርምጃ የሚመጥኑ ብዙ ደረጃዎች ያሉት መሆኑና ረጅሙን ከፍታ በጥቂት በጥቂቱ እንድንወጣ ማድረጉ ነው። «የልጅነት መንፈስ» የተባለው ይህ መልእክት ይህንን ደረጃ በተግባራዊ መንገድ የሚያሳየንና ትልቅና ከፍ ያለ ወደሆነው ወደ እግዚአብሔርና ከፍ ወዳለው ሐሳቡ ደረጃ በደረጃ እንዴት እንደምንራመድ ያሳየናል። የተጠራንበት የእግዚአብሔር ዓላማ ገና በርሱ አምነን የእግዚአብሔር ልጆች ስንሆን የተፈጸመ ወይም እኛን ልጅ አድርጎ ብቻ ያለቀ ሳይሆን እነዚህ የዚህ መሳላል የመጀመሪያ ደረጃዎች መሆናቸውንና ከመዳንና ከልጅነት ተነስተን ከደህንነት ከፍታ ወደ ማይጠፋ ዘርነት ከማይጠፋ ዘርነት ወደ ልጅነት ክብር ከልጅነት ክብር ወደ ልጅነት መገለጥና ከዚያም በሚገለጡት ልጆች ወደሚሆነው የፍጥረት ነጻነት እያንደረደረ የተወሰነልንን ከፍታ ያሳየናል።
"እግዚአብሔር ጸሎትን የሚመልስ አምላክ ብቻ ሳይሆን ጸሎትንም የሚሰጥ አምላክ ነው። እርሱ ሳያውቀው ለአብርሃም ጸሎትን ያቀበለ ማን ሆነና? አብርሃም ለራሱ የጸለየ መስሎት የሚወርሰውን ልጅ ለማግኘት ቢጸልይም ሳያውቀው የእግዚአብሔርን መሻት እየጸለየ ነበር። ያ የልጅ አምሮት ያ የወራሽ ፍላጎት በአብርሃም ልብ ውስጥ ለጥቂት አመታት ከመንደዱ በፊት በእግዚአብሔር ልብ ለዘላለም ይንተከተክ ነበር። እግዚአብሔር ከልቡ ነዲድ በእምነት መንፈስ ለአብርሃም በማካፈሉ አብርሃምን እንደፈቃዱ የሚጸልይ አደረገው። የዘላለም ሐሳቡ በመንፈስ ቅዱስ በልባችን ላይ ሲፈስ ጸሎታችንን የማያቋርጥ ያደርገዋል። "
ይህንን የመሳላል ጉዞ ከጀመርን አንዱን ደረጃ ስንጨርስ ሌላውን እያየን አባታችን ወዳለበት ከፍታ ለመድረስ የኋላችንን እየረሳን የፊታችንን ለመያዝ እንዘረጋለን። እንደ ናትናኤል ባየነው እይታ ተደንቀን ሳንጨረስ «ከዚህ የሚበልጥ ታያለህ» የሚለውን የጌታን ድምጽ ስለምንሰማ አሁንም ወደ ከፍታው ጫፍ እንዘረጋለን። እግዚአብሔር በኛ መንፈሳዊ ቁመት ልክ ሳይሆን የዚህን መሳላል ጫፍ እስክንነካ ድረስ ከምንለምነውና ከምናስበው ሁሉ ይልቅ የሚበልጠውን በኛ ከመፈጸም አንጻር የሚሰራ አምላክ ነው። «እንግዲህ በእኛ እንደሚሠራው ኃይል መጠን ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ ለሚቻለው፥ ለእርሱ በቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ኢየሱስ እስከ ትውልዶች ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።» (ኤፌ.3፡20-21)
በአብርሃም ልብ ከነበረው ልጅን መሻት ይልቅ በእግዚአብሔር ልብ የነበረው ልጅን የመስጠት ዓላማ የሰፋ ነው። አብርሃምና ሣራ ሳይሞቱ ዘራቸውን ለመተካት ከእድሜ ጋር እሽቅድድምድም ይዘው ነበር። የልባቸው መሻት ልጅ አይተው መሳምና መታነጽ እንጂ ከዚያ የዘለለ አልነበረም። ስለዚህ ከዚህች ዓለም ሳይሰናበቱ ዘራቸውን በምድር ሊያስቀጥል የሚችልን ልጅ ፈለጉ። እግዚአብሔር ግን በነርሱና በሚሰጣቸው ልጅ እነርሱ ከፈለጉትና ከሚጠብቁት እጅጉን የላቀ ዓላማ ነበረው። በዚያ ልጅ ብዙ ልጆችን ሊወልድ፣ ህዝብን ሊያበዛ፣ አገርን ሊመሰርት፣ መንግሥትን ሊገልጥ፣ ማደሪያውን ሊሰራ … ይንቀሳቀስ ነበር። በነአብርሃም ልብ ውስጥ ያለውንና በእግዚአብሔር ልብ ያለውን ሐሳብ ስናወዳድረው የትየሌሌ የሆነ ርቀት አለው። ከምንለምነው በላይ አብልጦ የሚያደርገው እኮ ልመናችን እርሱ ሊያደርገው ያለውን ዓላማና ሐሳብ ስለማይመጥን ነው።ምናልባት የኛ ጸሎት ብዙ የእግዚአብሔር መልስ ግን ትንሽ ይመስለን ይሆናል። ቃሉ የሚለን ግን እግዚአብሔር በኛ ሕይወት ሊፈጽመው ከሚፈልገው ሐሳቡ ጋር ሲወዳደር የኛ ጸሎት ትንሽ ነው እያለን ነው።ሌላው ብዙ ጊዜ ልመናችን በኛና በፍላጎታችን ልክ ነው። ወደ መንፈሱ ስንገባ ግን ከኛ መሻት ተሻግረን የርሱን ዘላለማዊ ዓላማ ስለምናይ ጸሎታችንም ዘላለማዊ ዓላማውን የሚያክል ይሆናል። በኛ ውስጥ ሆኖ ድካማችንን የሚያግዝ መንፈስ የተሰጠን እኮ እንዴት እንደምንጸልይ ስለማናውቅ ነው። «እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃል፥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና።» (ሮሜ.8፡26-27) ለመሆኑ እንዴት እንደምንጸልይ አናውቅም እንዴ? እንኳንስ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ሰው ይቅርና ሰው ሁሉ በሚመስለውና በሚገባው መንገድ ወደ አምላክ ይጸልይ የለምን? እኛ ክርስቲያኖችማ እንዴት እንደምንጸለይ ከማወቅ አልፈን በጣም የሰለጠነና ሲወርድ ሲዋረድ በመጣ የአጸላለይ መንገድ የተካንን፣ የተመረጡ ሃይማኖታዊ ቃላትን እየደረደርን የምንጸልይ አይደለንም? እንደዚህ ከሆነ እንዴት እንደምንጸልይ አናውቅም የተባልነው ለምንድን ነው? በእግዚአብሔር እይታ የዘላለም ሐሳቡን በመንፈሱ አይቶ በዚያው ባሳየው መንፈስ ያንኑ የዘላለም አሳቡ እንዲፈጸም የማይቃትት ሰው እንዴት እንደሚጸልይ አያውቅም። በመሆኑም የራሳችንን ሐሳብ “ጸሎት” ብለን ከመጸለያችን በፊት እንደ ሐዋርያት ጸሎትን አስተምረን ብለን ረቢውን መጠየቅ ጥበብ ነው። ለመሆኑ ጸሎትን እንዲያስተምራቸው የጠየቁት እነ ጴጥሮስ መፀለይን ስለማያውቁ ነውን? የአብርሃም ዘር የመቅደሱ ሰዎች ሆነው ጸሎትን አያውቁም ማለት የሚቻል አይመስለኝም። ያልተማሩ ቢባሉም አነሰም በዛ የአይሁድ ህዝብ የሚያውቀውን ሃይማኖታዊ ጸሎት የሚያውቁ ይመስለኛል። ከሆነ ለምን ጠየቁ? የተከተሉት ጌታ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ከተለመደው የሰው ስርአት የተለየ መሆኑን አስተውለዋልና የርሱን ፍለጋ እንዲያሳያቸው ከመሻት ነው።
የአባት ፍቅር
Join us today Membrs log inከዚህ በታች ያለውን የወንጌል ድምጽ እንዲሰሙ በታላቅ ፍቅር እንጋብዝዎታለን፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=5I8ey_UUVGA
እግዚአብሔር ጸሎትን የሚመልስ አምላክ ብቻ ሳይሆን ጸሎትንም የሚሰጥ አምላክ ነው። እርሱ ሳያውቀው ለአብርሃም ጸሎትን ያቀበለ ማን ሆነና? አብርሃም ለራሱ የጸለየ መስሎት የሚወርሰውን ልጅ ለማግኘት ቢጸልይም ሳያውቀው የእግዚአብሔርን መሻት እየጸለየ ነበር። ያ የልጅ አምሮት ያ የወራሽ ፍላጎት በአብርሃም ልብ ውስጥ ለጥቂት አመታት ከመንደዱ በፊት በእግዚአብሔር ልብ ለዘላለም ይንተከተክ ነበር። እግዚአብሔር ከልቡ ነዲድ በእምነት መንፈስ ለአብርሃም በማካፈሉ አብርሃምን እንደፈቃዱ የሚጸልይ አደረገው። የዘላለም ሐሳቡ በመንፈስ ቅዱስ በልባችን ላይ ሲፈስ ጸሎታችንን የማያቋርጥ ያደርገዋል። ጸሎቱ የዛለለም ሐሳቡ እኩያ ወይም ግልጦት ስለሆነ ያ ሐሳብ እስኪፈጸም ድረስ የጸሎቱ ነበልባል ከውስጣችን አይጠፋም። ሐሳቡ እስኪፈጸም ድረስ ጸሎቱ ይነዳል። በዚህን ጊዜ ሳያቋርጡ መጸለይ ህግ ሳይሆን ህይወት ይሆንልናል። አብርሃም ካገኘው ልጅ እኩል ያድግ ጀመር። ልጁ ሲያድግ አብርሃምም አደገ። ልጁ ጡት ሲጥል አብርሃምም ከወተት ወደ አጥንት አስተሳሰብ ተሸጋገረ። ይስሐቅ ጡት ሲጥል ሣራም ከምድር ከአጋር ትጠባው ከነበረው የመታነጽ ተስፋ ጡት ጣለች። የተሰጣቸው የተስፋ ልጅ ከተወለደ በኋላ እነ አብርሃም እንደበፊቱ መሆን አልቻሉም። እነርሱም ብዙ ነገር እየጣሉ ወደፊት ይራመዱ ነበር። ይስሐቅ የሣራን ጡት ሲጥል አብርሃምና ሣራ ደግሞ የአስተሳሰባቸውን ጡት እየጣሉ ለእግዚአብሔር እያደጉለት ነበር። ጉዳዩ የነርሱን ጸሎት ብቻ የመመለስ ቢሆን ኖሮ ታሪኩ ልጅ ሲያገኙ ያበቃ ነበር። ነገር ግን አብርሃም ጉዞውን ቀጠለ። ጌታ የሰጠውን ልጅ ሊሰዋ ወደ ሞሪያ ምድር ሄደ። ልጁ ለእግዚአብሔር ተጋደመ ተሰዋ ከዚያም ተነሳ ተገለጠ። ከመሰዊያው በኋላ ይስሐቅ የአብርሃም ልጅ ብቻ ሳይሆን ሌላን ማእረግ ጨመረ። በመታዘዝ ያለፈ፤ ለእግዚአብሔር የተሰዋ፤ ከሙታን የተነሳ በኃይል የአብርሃም ልጅ ሆኖ የተገለጠ ተባለ። ይህ ሁሉ በመንፈሳዊ መረዳት ነው። አብርሃም አሁንም ልቡ መቃጠሉን አላቆመም እንደገና ተራመደ፡ ለዚህ ልጅ የምትመጥን ሚስት ለማግኘት ትእዛዝ አወጣ። ከሩቅ ምድር ለልጁ ለይስሐቅ ሚስት እንዲያመጣለት አገልጋዩን በመሃላ አዘዘው፡፡ ሚስቱም ከሩቅ ምድር መጣች በሣራ ድንኳን ከይስሐቅ ጋር ተዋሃደች። ከዚህ በኋላ አብርሃም ጉዞውን ፈጸመ። ተሰውሮ በይስሐቅ በኩል ይታይና ይተረክ ጀመረ። ይስሐቅ አብርሃምን ወረሰው። ሊገልጠው ወረሰው። በነገድ ተባዛ ህዝብ ሆነ መንግሥት ሆነ፡፡ አብርሃም አንድ ብቻ መሆኑ ቀርቶ በህዝብና በመንግሥት በብዙ ልጆቹ ተገለጠ። በዚህ ውስጥ የአባታችን የእግዚአብሔር ዓላማና የልቡ መሻት አይታያችሁምን? እግዚአብሔር እኛን ልጆች አድርጎ በመውለድ አልጨረሰም። የወለደን ሊያሳድገንና ወራሾች ሊያደርገን መንግሥት ሊያደርገን ራሱን ሊያወርሰንና መልኩን ሊገልጥብን ነውና ይህንን ለመፈጸም በመንፈሱ እየተራመደ ነው። ይህ ሲበራልን “ክርስቲያን ተብየ ከተጠራሁ ይበቃኛል” በሚለው የሰነፎች መዝሙር ውስጥ አንከርምም። ልጅ ከመባል ጡት የጣለ ልጅ ወደ መባል፣ ጡት የጣለ ልጅ ከመባል የተሰዋ ልጅ ወደ መባል፣ የተሰዋ ልጅ ከመባል በኃይል የተገለጠ ልጅ ወደ መባል በኃይል ከመገለጥ በህይወት ወደ መብዛት እንሸጋገራለን። ከዚያም በመወለዳችን ከሆነው ይልቅ በመገለጣችን የሚሆነው ክብር ሲበልጥና ፍጥረትን ከተያዘበት ባርነት ነጻ ሲያወጣ በማየት የዘላለሙን አባት እናመሰግናለን።
በልጅነት ውስጥ የአባት መልክ (ባህርይ) አለ። በአባት መልክ ውስጥ ደግሞ የአባት ዓላማ አለ። ስለዚህ እግዚአብሔር በክርስቶስ ልጆችን በመልኩ የወለደው በመልኩ ውስጥ ያለውን ዓላማ ለመግለጥ ነው።
«ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ሲያመጣ የመዳናቸውን ራስ በመከራ ይፈጽም ዘንድ፥ ከእርሱ የተነሣ ሁሉ በእርሱም ሁሉ ለሆነ፥ ለእርሱ ተገብቶታልና።» (እብ.2፡10)
ይህ ቃል ክርስቶስ በመከራ ያለፈበትን ዓላማ ከዚህ በፊት ከሰማነው ለየት ባለ መንገድ ያሳየናል። ብዙ ሰዎችን ከሲኦል ሲያድን ሳይሆን ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ሲያመጣ ነው የሚለው። ልጆችን ነው ወደ ክብር ሊያመጣ ነው የፈለገው። ይህም ልጅነት የመጨረሻ እንዳልሆነ የሚያሳየን ነው። ልጆች እንዲድኑና ልጆች እንዲሆኑ ብቻ ሳይሆን ወደ ክብር እንዲመጡ ዋጋ ከፍሎአል። ይህ ክብር እርሱ ራሱ ያለበትና የገለጠው ክብር ነው። አንድያ ልጅ ሆኖ ሲገለጥ እንዲህ ተባለለት። «ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።» (ዮሐ.1፡14) ይህንን ለመጀመሪያ ጊዜ ከአባቱ ዘንድ በመውጣት ለጥቂቶች ያሳየውን ክብር በትንሳኤው ልጆች ባደረጋቸው በብዙ ልጆች ለመግለጥና የአባቱን ክብር ለመተረክ እየሰራ ነው። በርሱ በተገለጠው የአባት ክብር ነጻ የወጣነውና ወደ ልጅነቱ ክብር የደረስነው ልጆች ይህንን ክብር ተላብሰን ስንገለጥ የፍጥረት እረፍት ይሆናል። ፍጥረትም የልጆቹን ኮቴ በመከተል ነጻ መውጣት ብቻ ሳይሆን ወደ እግዚአብሔር ልጆች ክብር ይደርስ ዘንድ በዘላለም ሐሳቡ መስመር ይራመዳል። ነጻነትም ልጅነትም ያለው በዚህ ክብር መገለጥ ውስጥ ሲሆን ይህ ክብር ደግሞ የአባት መልክና የክብር መንጸባርቅ ነው።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡
“ሕፃኑም አደገ፥ ጡትንም ከመጥባት ተቋረጠ፤ አብርሃምም ይስሐቅን ጡት ባስጣለበት ቀን ትልቅ ግብዣን አደረገ።” ዘፍ 21:8
“ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና፤ ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በስራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።” እብ 5፡13-14
0% መምህር ጸጋ፡፡