The real problem of humanity and the solution of God

The real problem of humanity and the solution of God

ትክክለኛው የሰው ችግርና የእግዚአብሔር መፍትሄ

“ይህ ሕዝብ ወይም ነቢይ ወይም ካህን፦ የእግዚአብሔር ሸክም ምንድር ነው? ብሎ ቢጠይቅህ፥ አንተ፦ ሸክሙ እናንተ ናችሁ፥ እጥላችሁማለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፡ ትላቸዋለህ።” ትንቢተ ኤርምያስ 23፡33 ፡፡

በመምህር ጸጋ

ዛሬ ከአንድ ሰው ጋር ላስተዋውቃችሁ መጥቻለሁ፡፡ ከማን ጋር አትሉም? ዛሬ የማስተዋውቃችሁ ከአንድ  በጭራሽ አይታችሁት ሰምታችሁት ከማታውቁት ሰው ጋር ነው፡፡ ከጥላችሁ ይልቅ እጅግ በቅርባችሁ የሚኖር ለረጅም ጊዜ አብሮአችሁ የቆየ ሰው ቢሆንም ለምን እንደሆነ እንጃ እስከዛሬ አታውቁትም፡ መቼስ ማን ይሆን እያላችሁ ሳትጨነቁ አትቀሩም፡ እንግዲህ ዛሬ ለመተዋወቅ ተዘጋጁ፡፡ 

ታድያ እንዳትደነግጡ ጠንቀቅ በሉ፡፡ ሰውየው እጅግ የሚያስፈራ ስለሆነ ራሳችሁን አዘጋጁ፡፡ እንሆ ላስተዋውቃችሁ ያ ሰው እናንተ ናችሁ፡፡ የማስተዋውቃችሁ ከራሳችሁ ጋር ነው፡ ወንድሜ ራስህን አዘጋጅ፡፡ ያንን ሐሰተኛውን ኃጢአተኛውን ሥጋዊውን ክፉውን ገዳዩን ያንን አስቸገሪውን ሰው ታውቀዋለህ? ትዝ አለህ? አስታወስከው? አይዞህ ብዙም አትቸገርም ለማስታወስም አትሞክር ምክያቱም ያ ሰው አንተ ነህ፡፡ 

ብዙዎቻችን እንደምናስበውና እንደሚመስለን በምድር ላይ ብዙ ችግሮች የሉም ችግሩ አንድ ብቻ ሲሆን እርሱም ሰው ነው፡፡ ሰው ራሱ ችግር ሆኖ ብዙ ችግሮች እንዳሉ በማስመሰል ችግሮቹን ለመፍታት እየጣርኩ ነው ብሎ ይጮሃል። ጅራፍ ራስዋ መትታ ራስዋ ትጮሃለች እንደሚባለው ሰውም ራሱ ችግር ሆኖ ችግር በዛ እያለ ይናገራል።

አንድ ረጅምና ብዙ ፂም ያላቸው አባት ነበሩ ይባላል። ምግብ ሲበሉ ድንገት ሳያዩት የምግብ ፍርፋሪ ጺማቸው ጫካ ውስጥ ገብቶ ይሸሸጋል ይህ ጺማቸው ጫካ ውስጥ የተደበቀ ምግብ እየቆየ ሲሄድ መጥፎ ጠረን ይፈጥር ጀመረ፡፡ እኚህ አባት እጅግ ይቸገሩና ያስቸገራቸውን መጥፎ ጠረን ከየት እንደሚመጣ ለማግኘትና ለማስወገድ መፈለግ ቤታቸውንም መጥረግ ጀመሩ ቢፈልጉ ቢፈልጉ ሊያገኙት አልቻሉም፡፡ የክፋቱ ክፋት ደግሞ አፍጫቸው ስር መመሸጉ ነበር። አፍንጫቸው ስር ሆኖ ብዙ ሲያስቸግራቸው እሚያደርጉትን አጡና በኃዘንና በትካዜ ወይ አምላኬ እያሉ ጺማቸውን ማሻሸት ሲጀምሩ ድንገት ዱብ ብሎ ወደቀ፡፡ ሰውየም  ውይ እኔ ከሩቅ ስፈልግህ አንተ  እዚሁ አፍጫየ ስር ኖረሃል? አሉ ይባላል

ችግራችሁ አፍንጫችሁ ስር መሆኑን ስንቶታችሁ ታውቁ ይሆን? የምድር ችግርዋ አፍንጫዋ ስር ያለው አዳም ነው፡፡ ችግሩ ይህ እጅግ የቀረበን ችግር ማለትም ራሳችን ቶሎ የማይታየን መሆኑ ነው፡፡ ሁሉም ጣቱን ወደሌላው እየቀሰረ ችግሩ ያ ነው ችግሩ እነርሱ ናቸው ወዘተ ይላል፤፡ ቃየል መስዋእቱ ተቀባይነት የማጣቱ ምክንያት  ወንድሙ አቤል እንደሆነ አሰበ ስለዚህ  ገደለው፡፡ ነገር ግን  ችግሩ  ራሱ ቃኤል ነበር፡፡ በጣም የሚገርመው ሁላችንም ለራሳችን እንግዶች መሆናችን ነው፡፡ ከሌላው ሰው ጋር ሳይሆን ከራሳችን ጋር የሚያሰተዋውቀን የእግዚብሔር መልእክተኛ ያስፈልገናል፡፡ አንድ ቀን ንጉሥ ዳዊት የራሱ ማንነት ጠፋበት፡፡ ነቢዩ ናታን ንጉሥ ዳዊትን ከራሱ ጋር አስተዋወቀው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው ንጉሥ ዳዊት ስልጣኑን ተጠቅሞ የኦርዮን ሚስት ለራሱ ወሰደ፡፡ በዚህን ጊዜ እግዚአብሔር አምላክ አዘነና ነቢዩን ናታንን ላከበት፡፡ ነቢዩ ናታንም መጥቶ እንዲህ አለው፡፡ 

“በአንድ ከተማ አንዱ ባለጠጋ አንዱም ድሀ የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ። ባለጠጋውም እጅግ ብዙ በግና ላም ነበረው። ለድሀው ግን ከገዛት አንዲት ታናሽ በግ በቀር አንዳች አልነበረውም፤ አሳደጋትም፥ ከልጆቹም ጋር በእርሱ ዘንድ አደገች፤ እንጀራውንም ትበላ፥ ከዋንጫውም ትጠጣ፥ በብብቱም ትተኛ ነበር፥ እንደ ልጁም ነበረች። ወደ ባለጠጋውም እንግዳ በመጣ ጊዜ ከበጉና ከላሙ ወስዶ ለዚያ ወደ እርሱ ለመጣው እንግዳ ያዘጋጅለት ዘንድ ሳሳ፤ የዚያንም የድሀውን ሰው በግ ወስዶ ለዚያ ለመጣው ሰው አዘጋጀ። ዳዊትም በዚያ ሰው ላይ እጅግ ተቈጥቶ ናታንን፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ይህን ያደረገ ሰው የሞት ልጅ ነው። ይህን አድርጎአልና፥ አላዘነምና ስለ አንዲቱ በግ አራት ይመልስ አለው። ናታንም ዳዊትን አለው፦ ያ ሰው አንተ ነህ።” 2 ሳሙ 12፡1-7

ንጉሥ ዳዊት ይህንን እጅግ አሳዛኝ የሆነ ክፉ ድርጊት ሲሰማ እንዴት እንደተቆጣ ተመልከቱ እጅግ ተቆጣ ነው የሚለው፡፡ ሕያው እግዚአብሔርን! ይህን ያደረገ ሰው የሞት ልጅ ነው። ይህን አድርጎአልና፥ አላዘነምና ስለ አንዲቱ በግ አራት ይመልስ ነበር ያለው፡፡ ይህን ክፉ ነገር ያደረገው  ሰውየ እሩቅ ያለ መስሎት ሞት ይገባዋል ብሎ ሲፈርድ ነቢዩ  ናታን ግን ያ ሰው አንተ ነህ በማለት መለሰለት፡፡ ከራስ ጋር መተዋወቅ ይሏችኋል ይህ ነው፡፡ እጅግ ይገርማል ለካ ከራስ ጋር  ለመተዋወቅም የሚያስተዋውቅ ያስፈልጋል? አዎ ሰው ልቡ ስለታወረና ከእግዚአብሔር ብርሃን ስለራቀ ራሱን የሚያይበትና የሚያውቅበት መስተዋት የለውም፡፡ ስለዚህ በቃሉ ብርሃን ከራሱ ጋር የሚያስተዋውቀውና ወደ ንስሐ የሚመራው የእግዚአብሔር ቃል ያስፈልገዋል፡፡

ያለ መስተዋት ፊታችንን ማየት እንደማንችል ሁሉ ያለ እግዚአብሔር ቃል ውስጣችንን ማየት አንችልም፡፡ ስለዚህ ወደ እውነተኛው ብርሃን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እስክንመጣ ድረስ ራሳችን ችግር መሆናችንና በኃጢአት የሞትን መሆናችን አይገባንም፡፡ እንዲያውም ህግ ጥሰዋል በምንላቸው ሰዎች ላይ ለማስፈረድ ወደ እግዚአብሔር ይዘናቸው እንመጣለን፡፡ በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ምእራፍ ስምንት ላይ ያለው ታሪክ ይህንን ያስታውሰናል፡፡ ራሳቸውን በመስተዋት ያላዩ ጻፎችና ፈሪሳውያን አንዲትን በምንዝር የተያዘች ሴት ይዘው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ለክስ መጡ፡፡ ክሱ ግን በርስዋ ላይ ያነጣጠረ አልነበረም ተከሳሹ የተባረከው ጌታ ራሱ ነበር፡፡ የሚከሱበትን መንገድ እንዲያገኙ እርስዋን እንደማስረጃ ነው ያመጧት፡፡ ያላወቁት ነገር ግን እነርሱም ተከሳሽ ኃጢአተኞች መሆናቸው ነው፡፡ አንድ ሌባ ሌላውን ሌባ ይዞ ወደ ፖሊስ ሲመጣ ይታያችሁ፡፡ ችግሩ መስተዋት ስለሌላቸው ህይወታቸው በጨለማ ነውና ፊታቸው ምን እንደሚመስል አላወቁም፡፡ መጥተውም ልብንና ኩላሊት በሚመምረምረው የዓለም ብርሃን በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ቆሙ፡፡ ጨለማ ብርሃንን ሊከስ በፊቱ ቆመ፡፡ ጨለማ የሆነ ማንነት ይዘው ወደ ብርሃን ለፍርድ መጡ፡፡ “መላልሰው በጠየቁት ጊዜ ግን ቀና ብሎ፦ ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት አላቸው። ደግሞም ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ። እነርሱም ይህን ሲሰሙ ሕሊናቸው ወቀሳቸውና ከሽማግሌዎች ጀምረው እስከ ኋለኞች አንድ አንድ እያሉ ወጡ፤ ኢየሱስም ብቻውን ቀረ ሴቲቱም በመካከል ቆማ ነበረች።” የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል 8፤7-9፡፡ 

ብርሃን የሆነው ጌታ ሲናገር በቃሉ የብርሃኑን ጨረር ህሊናቸው ላይ አበራው፡  ለመጀመሪያ ጊዜ ራሳቸውን አዩ፡ ከማያውቁት ራሳቸው ጋር አስተዋወቃቸው፡፡ እጅግ ደነገጡ አንድ አንድ እያሉም ከፊቱ ሸሹ፡፡ ያ ሰው አንተ ነህ እርስዋ እናንተ ናችሁ በርስዋና በናንተ መካከል ልዩነት የለም አላቸው፡፡ ምንም ልዩነት እንደሌላቸውም በብርሃኑ አሳያቸው፡፡ ሊከሱ የመጡት ተከሰው ሄዱ፡፡ ደስ የሚለው ግን አልፈረደባቸው፡፡ ይልቅስ በብርሃኑ ህሊናቸውን በመፈተሽ እውነተኛ ማንነታቸውን በማሳየት ህሊናቸው እንዲወቀስ ረዳቸው፡፡ ምክንያቱም እርሱ  የመጣው የሰውን ልጅ ሊመልስ ሊያድን ነውና፡፡ ብዙ ጊዜ የምንገረመው አመነዘረች በተባለችው ሴት አለመፍረዱ ነው፡ ነገር ግን በነርሱም ላይ ነው ያልፈረደው፡፡ ኃጢአተኞች መሆናቸውን አጋልጦ ግን አልፈረደባቸውም ይልቅስ ማንነታቸውን እንዲያዩና ወደርሱ እንዲመለሱ ብርሃን ሆነላቸው፡፡ ዓላማው የሞተውን ኃጢአተኛውን ማንነታቸውን አሳይቶ በንስሐ እንዲመለሱ ማድረግ ነው፡፡ ፍቅር የሆነ ጌታ ለተከሳሽዋም ለከሳሾችም ምህረትንና ፍቅርን አወጀ፡፡ የወንጌሉን ቃል ሰምተን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ስንመጣ ትክከለኛ ማንነታችንን ያሳየናል፡፡ አሳይቶ ግን አይፈርድብንም ይልቅስ ለንስሐ ይጠራናል፡፡ 

  ሰው ግን በየጠዋቱ አፈሩን ለማየት ወደ መስተዋት እየሄደ ህሊናውን ነፍሱን መንፈሱን ለማየት ግን ወደ እግዚአብሔር ቃል አይመጣም፡፡ ስለዚህ ራሱን ሳያውቅ ለዘመናት ይኖራል፡፡ ራሱን ካላየ ደግሞ ችግሩ ሁሉ ከርሱ ውጭ የሚመጣ ይመስለዋል፡፡ ችግሩን ለማግኘትና መፍትሄ ለመፈለግም ማዶ ማዶ እያማተረ ይኖራል፡፡  እግዚአብሔር በአንድ ወቅት ነቢዩን ኤርሚያስ እንዲህ አለው፡፡

“ይህ ሕዝብ ወይም ነቢይ ወይም ካህን፦ የእግዚአብሔር ሸክም ምንድር ነው? ብሎ ቢጠይቅህ፥ አንተ፦ ሸክሙ እናንተ ናችሁ፥ እጥላችሁማለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፡ ትላቸዋለህ።” ትንቢተ ኤርምያስ 23፡33 ፡፡ የእስራኤል ህዝብ ራሳቸው ችግር ሆነ ራሳቸው ሸክም ሆነው የእግዚአብሔር ሸክም ምንድን ነው? ብለው ይጠይቁ ነበር፡ እግዚአብሔር ደግሞ ሸክሙ እናንተ ናችሁ አላቸው፡፡ ዛሬም ብዙ ሰዎች በምድር እየሆነ ያለው አመጽና ክፋት ሲያዩ ሸክሙ ማነው? ችግሩ ማነው? ይህ ሁሉ ግፍና በደል እየተፈጸመ ያለው በማነው? እያሉ ሲጠይቁ ይሰማል፡፡ እግዚአብሔር በቃሉ ሲመልስ ደግሞ ሸክሙ ችግሩ  እናንተ ናችሁ ይላል፡፡  ወንድሞቼና እህቶቼ ምድርን እንዲህ እያንገዳገዳት ያለው ችግር ሌላ ምንም ሳይሆን አሮጌው ሰው የሞተው ሰው በአየር አለቃው በሰይጣን ፈቃድ እየተመላለሰ ያለው ሰው ነው፡፡ አንዳንዶችም የችግሩ ሁሉ ምክንያት ሰይጣን ነው ብለው ለብቻው ሲያሸክሙት ይታያል፡፡ እውነታው ግ ን ሰይጣን የችግሩ ምንጭ ቢሆን ያ የሰይጣን ክፋትና ኃጢአት እየተገለጠ ያለው ግን በሰው  ነው፡፡ 

ስለዚህ ሌላው ቀርቶ የችግሩ ሁሉ ምንጭ የሆነው ሰይጣንም ሁለተኛ ደረጃ ነው፡፡ ያለሰው ክፋቱን አይገልጥምና፡ ከሰይጣን ጋር አብሮ ከእግዚአብሔር የኮበለለውና በስጋና በሞት የሚኖረው አሮጌው ሰው የሰማይም የምድርም ችግር ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር ለእስራኤል ህዝብ ሲናገር ሸክሙ እናንተ ናችሁ እንዳለው ሁሉ አሁንም የዚህች ምድር ሸክም ሰው ማለትም አሮጌው ማለትም በሰባት ቢልዮን የተባዛው አንድ አሮጌ ሰው ነው፡፡ ምድር የሰባት ቢልዮን የአዳም ልጆችን ሬሳ ተሸክማ ከብዶአት እየተንገዳገደች ነው፡፡ ሬሳ ከባድ ነው ይባላል፡፡ አዳም ደግሞ ያችን አትብላ የተባለውን ዛፍ በልቶ ሞቶአል፡፡ በእግዚአብሔር ፊት አዳም የሞተ ፍጥረት ነው፡፡  ስለዚህ ምድር ልትሸከመው ከብዶአታል፡፡ በርሱ ምክንያት ምድር ተበላሸች፡፡ “ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ተበላሸች፤ ምድርም ግፍን ተሞላች።እግዚአብሔርም ምድርን አየ፥ እነሆም ተበላሸች፤ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በምድር ላይ መንገዱን አበላሽቶ ነበርና።” ኦሪት ዘፍጥረት 6፡11-12፡፡ 

ምድር የሰው አመጽ ከብዷት እንደ ሰከረ ሰው እየተንገዳገደች ነው፡፡ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ “ምድር ተሰባበረች፥ ምድር ፈጽማ ደቀቀች፥ ምድር ተነዋወጠች። ምድር እንደ ሰካር ሰው ትንገዳገዳለች፥ እንደ ዳስም ትወዛወዛለች፤ መተላለፍዋ ይከብድባታል፥ ትወድቅማለች ደግማም አትነሣም።” ትንቢተ ኢሳይያስ 24፡19-20

በአየር አለቃው  ፈቃድ ሥር የሚመላለሱት እና ሙታን የሆኑት የአዳም ልጆች ከእንስሳነት አልፈው ወደ አውሬነት ተሸጋግረዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲናገር እንዲህ ይለናል፡፡

“ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፥ አንድ ስንኳ የለም። ጕሮሮአቸው እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፥ በመላሳቸውም ሸንግለዋል፤ የእባብ መርዝ ከከንፈሮቻቸው በታች አለ፤ አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቶበታል፤ እግሮቻቸው ደምን ለማፍሰስ ፈጣኖች ናቸው፤ ጥፋትና ጉስቁልና በመንገዳቸው ይገኛል፥ የሰላምንም መንገድ አያውቁም። በዓይኖቻቸው ፊት እግዚአብሔርን መፍራት የለም።” ሮሜ 3፡11-18

የምድር መልክ ይህ ነው፡፡ የሰባት ቢልዮኑ የዓለም መልክ ይህ ነው፡፡ የሰው ትክክለኛ መልክ ይህ ነው፡፡ ይህንን ትክክለኛ ፊታችሁን ቀርጾ የሚያሳያችሁ የፎቶግራፍ ካሜራ የለም፡፡ ይህንን የሚያሳያችሁ የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው፡፡ በትክክል ማንነታችሁን ስታዩ በምድር ላይ እንደርሱ የምትፈሩት ነገር አይኖርም፡፡ አንበሳን ነበርን ወይንም አስፈሪ የሚባሉ አራዊትን አትፈሩም፡ ማንነታችሁ ከነርሱ ሁሉ ይበልጣል፡፡ እነርሱ ከጥርሳቸው በስተቀር የሚገድሉበት የሚናከሱበት የላቸውም፡፡ ሰው ግን ወንድሙን የሚጨርስበት ሮኬት ሚሳይል ታንክ ኒኩሌር ሰርቶ ታጥቆአል፡፡ ስለዚህ የሰው የሞተ ማንነት ከአራዊት ሁሉ የከፋ አራዊት ነው፡፡ ትክከለኛው የሰው  መልክ በዚህ ቅዱስ ቃል ግልጥ ብሎ ተቀምጦአል፡፡ መታወቂያችሁ ፓስፖርታችሁ የሚላችሁን አይደላችሁም፡፡ ከነዚህ ባህርያት አንዱም በመታወቂያችሁ ላይ አልተጻፈም፡፡ ምክንያቱም የዚህ ዓለም ገዢ ዲያብሎስ ጨለማ የሆነውን ማንነታችሁን እንድታዩ አይወድምና ይህን አያሳያችሁም፡፡ ጤነኛ ነኝ ጻድቅ ነኝ ትክክል ነኝ እያላችሁ ወደ ሞት እንድትሄዱ ይፈልጋል፡፡ ቸሩና መኃሪው እግዚአብሔር ግን የሰው ልጆችን  ከዚህ ከሞተ ማንነት፤ ከዚህ ሰይጣናዊ ማንነት፤ ከዚህ ሰው ገደልኩ ብሎ ከሚፎክርና ከሚደሰት ማንነት፤ ከዚህ ከአራዊት ከባሰ  ማንነት፤ ከዚህ በእባቡ መርዝ ከተሞላው ማንነት ይወጡ ዘንድ ነው የምሕረት መንገዱን ዘርግቶአል፡ በመጀመሪያ በራሳቸው ሥራ መጽደቅ ወይም ወደርሱ መድረስ እንደማይችሉ ያውቁ ዘንድ ህጉን ገለጠ፡፡ ህጉ ማንነታችንን የሚያጋልጥ መስተዋት ሲሆን ክፉ ማንነታችንን እያሳየ ከዚህ ክፉ ማንነት  ወደ ሚያድነን ክርስቶስ ይጠቁመናል ይመራናል፡፡ ህጉ እንደ ህክምና ምርመራ ነው፡፡ ምርመራ አደርጋችሁ ማለት ታከማችሁ ማለት አይደለም፡፡ ምርመራ የምናደርገው ያለብንን በሽታ ለማወቅ ነው፡፡ ካወቅን በኋላ ግን በምርመራው ውጤ መሠረት ወደ መድኃኒት እንላካለን ወይም መድኃኒት ይታዘዝልናል፡፡ እግዚአብሔርም በህጉ መረመረን በሽታችንንም አሳየን፡፡ ምርመራው በመጀመሪያ  በራሳችን መዳን እንደማንችል በማሳየት ተስፋ አስቆረጠን፡፡  እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ 

“አፍም ሁሉ ይዘጋ ዘንድ ዓለምም ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ይሆን ዘንድ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንዲናገር እናውቃለን፤ ይህም የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው፤ ኃጢአት በሕግ ይታወቃልና።” ሮሜ 3፤19-20

ይህንን ካሳየን በኋላ ከእግዚብሔር የተዘጋጀልንን የተሰጠንን መዳን እንዲህ ያውጅልናል፡፡

“አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፥ እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤ ልዩነት የለምና፤ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ። እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፥” ሮሜ 3፡21-25

የምስራች ከገባንበት ጉድጓድ የሚያወጣን የፍቅር ገመድ ተዘረጋልን፡፡ አንድም ሳይቀር ሁላችንም ሞተናል ጠፍተናል፡፡ የክብር መልካችንን አጥተን የጨለማ መልክ ለብሰናል፡፡ 

መመለስ ብንፈልግ እንኳ በራሳችን ጥረት መመለስ አንችልም፡፡ የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት አይጸድቅም፡፡ አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጣልን፡፡ “እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ” ተባለለት፡ ማቴ 1፤23፡፡ ከኃጢአት የሚያድነው ብቸኛው የሰው ልጆች መድኃኒት ተገለጠ፡፡ ከኃጢአት የሚያድን እርሱ ብቻ ነው፡፡ አሮጌውን ሰው ከኛ ላይ ገፎ አዲሱን የሚያለብሰን እርሱ ብቻ ነው፡፡ በዓለም ላይ ሌላ መድኃኒት የለም፡፡ የጥበበኞች ጥበብ የተራቀቁት የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ሳይንቲስቶች ምርምር ከዚህ ክፉ ሰውነት አያድንም፡፡ የምድር ነገሥታትና የሃይማኖት መሪዎች ከዚህ ማንነት አያድኑም፡፡ ምክንያቱም ሁሉም እርሱ ናቸውና፡፡ ጥበበኛ ፈላስፋ ንጉሥ የአገር መሪ የሃይማኖት መሪ እርሱ ራሱ በሽታ የሆነው አዳም ነውና መዳን ከርሱ ዘንድ የለም፡፡ አዳም ካባ እየቀያየረ አንድ ጊዜ ሃይማኖተኛ ሌላ ጊዜ ጥበበኛ አንድ አንድ ጊዜ ቀማኛ ሌላ ጊዜ ዳኛ  እየሆነ ቢመጣም ያው አንዱ የሞተው አዳም ነው፡፡ የአዳም ዘር ሁሉ የሞተ ነው፡፡ ሲያታልል ነው እንጂ ከአዳም ልጆች አንዱ መንፈሳዊ አንዱ ዓለማዊ የሚባል ልጅ የለም፡፡ ከአንዱ ከሞተው ስለተወለዱ ልጆቹ ሁሉ ሙታን ናቸው፡፡   ከዚህ ክፉ ሊያድንነና ከክፋታችን ሁሉ እየመለሰ ሊባርከን ከሰማይ የመጣው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ህይወት የሆነው ጌታ አዳም ሞቶ በገደላቸው ሙታን መካከል ቆሞም እንዲህ አለ 

“እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ።” የሐዋርያው የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል 5፡24-25

አስቀድሞ የወረስነውን ሞት ያወረሰን የፊተኛው አዳም ነበር፡ እርሱ ሞቶ ስለገደለን ሙታን ሆንን፡፡ ይህን ሁሉ የአዳም ልጅ የገደለው በአንድ ሰው በአዳም የገባው ሞት ነበረ፡፡ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ” ሮሜ 5፡11፡፡ እግዚአብሔር ግን በምሕረቱ ባለጠጋ ስለሆነ ከሞተው አዳም ወጥተን ሕዋያን እንድንሆን ሕይወት የሆነውን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ላከልን፡፡ በፊተኛው አዳም ሞት ወደ ዓለም እንደገባና ወደሰው ሁሉ እንደደረሰ በኋለኛው አዳም በክርስቶስ ህይወት ወደ አለም  መጣ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በፍተኛው አዳም የገባውን ሞትና በኋለኛው አዳም የገባውን ህይወት እያነጻጸረ ሲጽፍ እንዲህ ይለናል፡፡

“ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን እንደዚያው አይደለም፤ በአንድ ሰው በደል ብዙዎቹ ሞተዋልና፥ ነገር ግን የእግዚአብሔር ጸጋና በአንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የሆነው ስጦታ ከዚያ ይልቅ ለብዙዎች በዛ።

አንድ ሰውም ኃጢአትን በማድረጉ እንደ ሆነው መጠን እንደዚያው ስጦታው አይደለም፤ ፍርድ ከአንድ ሰው ለኵነኔ መጥቶአልና፥ ስጦታው ግን በብዙ በደል ለማጽደቅ መጣ።

በአንዱም በደል ሞት በአንዱ በኩል ከነገሠ፥ ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ።

እንግዲህ በአንድ በደል ምክንያት ፍርድ ለኵነኔ ወደ ሰው ሁሉ እንደ መጣ፥ እንዲሁም በአንድ ጽድቅ ምክንያት ስጦታው ሕይወትን ለማጽደቅ ወደ ሰው ሁሉ መጣ።

በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።” ሮሜ 5፤15-19

እንግዲህ ችግሩ የሞተው አዳም መሆኑን ተመልከቱ በምድር ላይ እየተፈጸሙ ያሉት ነገሮች ሁሉ በሞተው አዳም የሚፈጸሙ ናቸው፡፡ የሞተው አዳም ፍሬ ክፋት አመጸኝነት መጋደል ጥላቻ በአጠቃላይ ምድርን እያጥለቀለቃት ያለው የአመጽ ጉርፍ ሲሆን መፍትሄው ደግሞ ከዚህ ከሞተ አዳም ወጥተን ህይወትን የሚሰጥ ወደሆነው አዳም ወደ ጌታችንና ወደ መድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መሻገር ነው፡፡ ህይወቱን ስናገኝ አዲስ ፍጥረት እንሆናለን፡፡ ችግሩ አሮጌው ሰዋችን ነበረ አሁን መፍትሄው አዲሱ ሰዋችን ሆነ፡፡ ከኛ ጋር ተጣብቆ ራሱ ችግር ሆኖ ሌላ ችግር ሲያሳየን የከረመው ማንነታችን ተጋለጠ በኢየሱስ ክርስቶስ ስራም ከኛ ተገፈፈ፡፡ በትንሳኤው አዲሱን ሰው አለበሰን፡፡ እጅግ የወደደንና ከሞተው ማንነታችን አውጥቶ አዲስ ማንነት የሰጠን እግዚአብሔር ስሙ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን፡፡

“በአንዱም በደል ሞት በአንዱ በኩል ከነገሠ፥ ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ። እንግዲህ በአንድ በደል ምክንያት ፍርድ ለኵነኔ ወደ ሰው ሁሉ እንደ መጣ፥ እንዲሁም በአንድ ጽድቅ ምክንያት ስጦታው ሕይወትን ለማጽደቅ ወደ ሰው ሁሉ መጣ።” ሮሜ 5፡17-18

2 thoughts on “The real problem of humanity and the solution of God”

    1. Amen Glory be to our to our Lord Jesus Christ. Thank you for visiting our website dear sister and we hope you will come back again and enjoy more messages. Blessings.

Leave a Comment