ለሰው ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ

የእግዚአብሔር ፍቅር

“መልአኩም እንዲህ አላቸው፦ እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።”

የሉቃስ ወንጌል 2:10 -11

በመምህር ጸጋ

ሰላም የሰው ልጆች እንደምን አላችሁ?

ዛሬ ለሰው ሁሉ የሚሆን መልእክት አለኝ

ሰው የሆነ ሁሉ ይህ መልእክት ለርሱ ነው

ሰዎች የሆናችሁ ሁሉ ይህ መልእክት ለእናንተ ነው፡፡

  •  በእግዚአብሔር የተፈጠራችሁ
  • በእግዚአብሔር የተወደዳችሁ
  • እርሱ የሰጠውን አየር ለምትተነፍሱ
  • እርሱ የሰጠውን ጸሐይ ለምትሞቁ
  • እርሱ የሚያዘንበውን ዝናብ ለምታገኙ
  • እርሱ ያበቀለውን እህል ለምትመገቡ
  • እርሱ በፈጠራትና ባስዋባት ምድር ለምትኖሩ የሰው ልጆች ሁሉ
  • ዛሬ አንድ የሚገርም ነገር የተከናወነበት ቀን ነው፡፡
  • ይህን ሁሉ የፈጠረው 
  • ሰውን በመልኩ ፈጥሮ እዚህች ምድር ላይ ያስቀመጠው
  • ሁሉን የሚችለው 
  • ዩኒቨርስን በቃሉ ያጸና 
  • የከዋክብትን እና የፕላኒቶቶችን ምህዋር የዘረጋ እርሱ ታናሽ ህጻን ሆኖ ተወለደ፡፡
  • ፈጣሪ ወደ ፈጠራት ምድር ሰው ሆኖ ገባ፡፡

 

በዚህ ዓለም ብዙ ነገሮች ሁላችንንም በእኩል ደረጃ አያስደስቱንም፡፡

አንዳንዶቻችንን የሚያስደስተን ሌሎኞቻችንን ሊያስከፋን ይችላል፡፡

አንድ ሚስጢር ግን አለ ሁላችንን ያስደሰተ ወይም ሊያስደስት የሚችል፡፡

ምክንያቱም ለሁላችንም የሚያስፈልግ ስለሆነ ነው እና 

ለሁላችንም የተደረገ የተሰጠ ስለሆነ

ንጹህ አየር መተንፈስ 

ምግብ መመገብ 

ውሀ መጠጣት 

ሁላችንም የምንፈልገው ነገር ነው፡፡

የትኛውንም ሃይማኖት ብንከተል 

የትኛውንም ዓይነት ቋንቋ ብንናገር 

የየትኛውም አገር ዜጋ እንሁን እነዚህን ነገሮች እንፈልጋቸዋለን፡፡ ከነዚህ ሁሉ በላይ ለሁላችንም ለሰው ልጆች ሁሉ በእኩል ደረጃ የሚያስፈልገን ደግሞ እግዚአብሔር አምላክ ነው፡፡

መንጋቸውን ለመጠበቅ በሜዳ ያደሩት መንጋውን ለመጠበቅ ክብሩን ትቶ በሜዳ ያደረውን ጌታ በግርግም ተኝቶ አገኙት፡፡

ለሰው ሁሉ የሆነ ታላቅ ደስታ 

 

“መልአኩም እንዲህ አላቸው፦ እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤

ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።”

የሉቃስ ወንጌል 2:10 -11

 

“ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር።” የዮሐንስ ወንጌል 1:9

 

ብዙ ክርስቲያኖች የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ለነርሱ ብቻ ይመስላቸዋል፡፡ 

ሌሎች ሰዎችም የልደቱ ጉዳይ የኛ ብቻ ይመስላቸዋል

እኛም የኛ ብቻ ይመስለናል

የተለያዩ ሃየማኖቶች የየራሳቸው በዓላት አሏቸው

ስለዚህ የኢየሱስ ክርስቶስንም መወለድ ለክርስቲያኖች ብቻ ተብሎ ይታሰባል፡፡

እውነታው ግን

የክርስቶስ መወለድ ለሰው ሁሉ ነው

እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ዓለም የላከው

የዓለሙ ሁሉ ፈጣሪ ሰው ሆኖ የተወለደው ለተወሰኑ ሰዎች ሳይሆን ለሰው ልጆች ሁሉ ነው፡፡  

ሰው ከሆንክ  ክርስቶስ ላንተ ነው የተወለደው

ክርስቶስ የተወለደው ለሁሉም ሰው ነው

 

ውሀ

እንጀራ

የጸሐይ ብርሃን

አየር ለሁሉም ናቸው

እነዚህ ውድ ነገሮች ለተወሰኑ ሃይማኖቶች ቢሰጡ ኖሮ ብላችሁ አስቡ፡፡

 

ኢየሱስ ክርስቶስ 

የዓለም ብርሃን እውነተኛው ጸሐይ ነው

ኢየሱስ ክርስቶስ የህይወት እንጀራ ተብሎአል

ኢየሱስ ክርስቶስ የህይወት ውሀ ተብሏል

በነዚህ የተመሰለው ለሁሉም ስለሆነ ነው

ክርስቶን የሚያምኑ ክርስቲያኖች ቢባሉም ኢየሱስ ክርስቶስ የክርስቲያኖች ብቻ አይደለም የሁሉም ነው

 

አንዳንድ ክርስቲያኖች የመወለዱ የምስራች የመሰቀሉ የምስራች መነገር ያለበት እንደነርሱ ክርስቲያን ለሆነ ሰው ብቻ ይመስላቸዋል፡

ለዚህም ነው ብዙዎቻችን የሌላ ሃይማኖት ተከታይ የሆነውን ሰው እንኳን ደስ አለህ ኢየሱስ ክርስቶስ ተወለደ የማንለው፡፡ 

እውነቱ ግን 

እንዲያውም የመወለዱ ዜና መነገር ያለበት ላላወቁት ላላመኑት ነው

የአባት ፍቅር

ከዚህ በታች ያለውን የወንጌል ድምጽ እንዲሰሙ በታላቅ ፍቅር እንጋብዝዎታለን፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ  የሆነውን አስደናቂ ነገር ላንብብላችሁ፡፡

“በዚያም ወራት ዓለሙ ሁሉ እንዲጻፍ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣች።

ቄሬኔዎስ በሶርያ አገር ገዥ በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመሪያ ጽሕፈት ሆነ። ሁሉም እያንዳንዱ ይጻፍ ዘንድ ወደ ከተማው ሄደ። ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ ቤተ ልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ፥ ፀንሳ ከነበረች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ወጣ። በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፥ የበኵር ልጅዋንም ወለደች፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው።”

የሉቃስ ወንጌል 2፡1-7

ይህ ወቅት ለቅድስት ድንግል ማርያም እና ለቅዱስ ዮሴፍ የማይመች ጊዜ ነው፡፡

መውለጃዋ ጊዜ ሲደርስ ነው ከባዱ የሮማ ንጉሥ አዋጅ የታወጀው

መውለጃዋ ለደረሰ ነፍሰ ጡር የእግር ጉዞ ከባድ ነው

እንኳንስ ጉዞ በቤት ተቀምጣም ብዙ መከራ አለባት፡፡

ነገር ግን አዋጁ አስቸኳይ የንጉሥ አዋጅ ነበረና ሊሄዱ ግድ ሆነባቸው

በዚህ ሁሉ በማይመች ሁኔታ ግን የእግዚአብሔር የዘላለም ሐሳብ ይፈጸም ነበር፡

ማርያምንና ዮሴፍን ወደዚህ ጉዞ ያመጣቸው የምድራዊው ንጉሥ አዋጅ ይምሰል እንጂ ከርሱ አስቀድሞ ከዘላለም የታወጀ የሰማያዊው ንጉሥ አዋጅ አለ፡፡ ክርስቶስ በዳዊት ከተማ በቤተልሄም ይወለድ ዘንድ ግድ ነው፡፡

እንግዲያውስ በትክክል ስናስተውለው ምድራዊው ንጉሥ ሳይሆን ኢየሱስን በቤተ ልሄም እንዲወለድ ያስገደደው እግዚአብሔር ራሱ ነው 

ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሄም ይወለድ ዘንድ ምድራዊውን ንጉሥ አዋጅ እንዲያውጅ ሆነ፡፡ ወደ ሌላ አገር ሳይሆን ወደ ግብጽ የተሰደደውም ልጄን ከግብጽ ጠራሁት የተባለው ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡

 በምድር ላይ ሁሉም የሚፈጸመው የእግዚአብሔርን የፈቃድ መስመር ተከትሎ ነው፡፡ ሰማይና ምድር የእግዚአብሔርን ሐሳብና ፈቃድ ተከትለው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ጽንፈ ዓለሙ የሚሽከረከረው በእግዚአብሔር ፈቃድ ዙሪያ ነው፡፡ 

አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር በህይወታችን አስገዳጅ ነገር የሚያመጣው

የማይመቸንን ነገር የሚያመጣው በኛ የሚፈጽመው ቃል ስላለ ነው፡፡

ቅድስት ድንግል ማርያምና ቅዱስ ዮሴፍ በዚህ ወቅት ምንም ተአምር ቢፈጠር ለጉዞ አይነሱም፡፡

ሴት መውለጃው ሲደርስ በቤተ ተቀምጦ ለመውለድ የሚያስፈልገውን ዝግጅት ሁሉ ይደረጋል እንጂ ለጉዞ አይወጣም

በሰው ልጅ አእምሮ ስናስበው ምጥ እየደረሰ ጉዞ የለም፡፡

ስለዚህ እግዚአብሔር የሚያስገድድ አዋጅ እንዲወጣ ሆነ፡፡ ያ ሁሉ አዋጅ የዚያ ሁሉ ሰው ጉዞና ቆጠራ አንድ ትንሽ የሚመስል ግን የዘላለም ልጅ ይወለድ ዘንድ ነው፡፡ 

በአውግስጦስ ዘንድ ዋናው ነገር የሰው መቆጠር ሲሆን በእግዚአብሔር ዘንድ ዋናው ነገር የክርስቶስ በቤተልሄም መወለድ ነበር፡፡  

አሁን በማይመች ሁኔታ ውስጥ ያላችሁ 

ማደሪያ የሌላችሁ 

ባላችሁበት ደስ ይበላችሁ፡፡

ካላችሁበት ሊያነሳችሁ የመጣው ጌታ 

ድህነታችሁን 

መገፋታችሁን 

መቸገራችሁን ሊካፍል እናንተ ወዳላችሁበት ዝቅታ ወርዶ በበረት ተወለደላችሁ፡፡ 

ሌላው በዚህ ክፍል የምንመለከተው የመወለዱን የምስራች ቀድመው የሰሙት እረኞች መሆናቸው  ነው፡፡ 

ቅዱስ ሉቃስ እንዲህ ይተርክልናል፡፡

“በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው፦ እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ።” ሉቃ 2፤8-12

መሲሁ በተወለደባት ሌሊት ሰው ሁሉ በሞቀ ቤቱ ተኝቶአል፡፡ ስለዚህ ያ ሰማይንና ምድርን የፈጠረው፤ ያ እፍ ብሎ እስትንፋስን ለሰው ልጅ የሰጠው፤ ያ ሰውን በአምሳሉ የፈጠረው፤ ያ ሰማይና ምድር ከፊቱ የሚሸሹት ጌታ ትንሽ ህጻን ልጅ ሆኖ ተወልዶ ያለምንም አጃቢ በበረት ተገኘ፡፡ በብርዳማው ሌሊት እናቱ ብርድ እንዳይነካው በጨርቅ ጠቅልላዋለች፡፡ ይህ ሁሉ ድንቅ ሲፈጸም የዘላለም ተስፋ፤ የሰው ልጆች ብርሃን፤ የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ወደ ዓለም ሲገባ ሁሉም ጸጥና ረጭ ያለ ነበር፡፡ ፈጣሪ ነኝና እልፍ አእላፍ መላእክት ያጅቡኝ ቀሳውስት ይክበቡኝ ሳይል በእንስሳት በተሞላ በረት ተወለደ፡፡ ይህንን ድንቅ ሥራ እንዲያዩና እንዲመሰከሩ የተመረጡት እረኞች ነበሩ፡፡ እረኛ ነውና በእረኞች ሊመሰከርለት ተወሰነ፡፡ ያለነርሱ በዚያች ሌሊት ምቾቱን ትቶ ወደርሱ የሚመጣ አይገኝም፡፡ እረኞቹ ግን መንጋቸውን የሚወዱት ታማኝ እረኞች ናቸውና መንጋቸውን ለመጠበቅ በሜዳ አድረው ነበር፡፡ ይህም ባህርያቸው እርሱን ለመጎብኘት እድልን ሰጣቸው፡፡ መንጋውን ለመጠበቅ በሜዳ አድሮአልና መንጋቸውን ለመጠበቅ በሜዳ ያደሩ እረኞች ጎበኙት፡፡ እረኝነት በሰው ዘንድ ሲታይ ዝቅ ያለ ስፍራ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ እረኞች በዙሪያቸው ካለው ማኅበረሰብ ከነገሥታቱ፤ ከካህናቱ ሁሉ ይልቅ ባነሰ ስፍራ ነበሩ፡፡ በዚያች ሌሊት መንጋቸውን ለመጠበቅ ከመንጋው ጋር በሜዳ ማደራቸውም የሚመች አልነበረም፡፡ ሰው በቤቱ ሲሆን ይሞቀዋል ከብርድ ይድናል ተመችቶት ይተኛል፡፡ እነዚህ እረኞች ግን ምቾታቸውን ስለመንጋቸው ሲሉ የተውና በማይመች ሜዳ ያደሩ ነበሩ፡፡ በዚህ በማይመች ስፍራ ማደራቸው ግ ን በሚመች ስፍራ በቤተ መንግሥት ባማሩ ህንጻዎች ተመችቶአቸው የተኙ ሰዎች ያላዩትንና ያላገኙትን እድል እንዲያገኙ ምክን ያት ሆነላቸው፡፡ መላእክቱ የምስራቹን ለመንገር ያገኙት እነዚህን እረኞች ነው፡፡ 

በዚህም የምናስተውለው ብዙ የማይመቹ ቦታዎችና ሁኔታዎች ለእግዚአብሔር ግን የሚመቹ መሆናቸውን ነው፡፡ በህይወታችን የማይመቹ በሚመስሉን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ስንሆን መልካም እረኛ የሆነው እግዚአብሔር ፈቃዱን በልባችን ያፈሳል ዓላማውን በህይወታችን ይፈጽማል፡፡