የሳምራዊትዋ ሴት ማስታወሻ
ሕይወቴና ታሪኬ ከሰው ጋረ አያስኬደኝም
ሕይወቴ ውበት የለውም
የሰዎች መጠቋቆሚያ ሆኜአለሁ
ትኩር ብየ እንኳ ሰዎችን መመልከት አልችልም
በቀትር ሁልጊዜ ምንጩ ባዶ ነበር።
ዛሬ ግን አንድ ሰው አገኘሁ
አለባበሱ የአይሁድ ነው
በዚህ ስፍራ ምን ያደርጋል?
ኢየሱስ ክርስቶስ ውሀ አጠጪኝ ብሎ ሲጠይቀኝ።
እንዴት ውሀ ይለምነኛል?
እንኳንስ ውሀ ሊለምነኝ አይሁዳዊ አናግሮኝ አያውቅም።
ንዴቴን በሚገልጽ ንግግር መቸም እናንተ አንድ ነገር ካልተቸገራችሁ አታናግሩንም
ብየ አሰብኩና አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት
ትለምናለህ? ብየ ከመለስኩለት በኋላ ልቤ ግን ይፈርድብኝ ጥያቄ ይጠይቀኝ ጀመር
ይህ ሰው ግን ንግግሩም እይታውም ለየት ያለ ይመስላል።
መልሱ እጅግ ያስገርማል።
ምንም ሳይኖረው ውሀ እሰጥሻለሁ ይለኛል
ያእቆብ አባታችን እንደሆነ ልነገርው ፈለግሁ
እኔም ከርሱ እንደማላንስ ላሳውቀው ፈለግሁ
እርሱ ግን እርሱ የሚሰጠኝ ውሀ ዘላለማዊ እንደሆነ ነገረኝ
ንግግሩ ግን ውስጥን ይመረምራል።
ከማንም ሰው ሰምቼ የማላውቀውን ንግግር ሰማሁ
በውስጤ ለዛለለም የሚፈልቅ የሕይወት ውሀ እንደሚያፈልቅልኝ ነገረኝ።
እኔም ደግሜ ወደዚህ ምንጭ መምጣት የሚያስቆምልኝ ካገኘሁ ደስ ይለኛል
እንዲያውም ከሰዎች እሰወራለሁ ብየ ደስ አለኝና ይህን ውሀ ስጠኝ አልኩት
ከዚያም አስደንጋጭ ጥያቄ ጠየቀኝ።
በጥያቄውም የሕይወቴን ቁስል ነካብኝ ባልሽን ጠርተሽ ነይ አለኝ፡
ስለዚህ ባል የለኝም አልኩት
እውነት በመናገሬ አሞገሰኝ
ባሌ ብለሽ ባለመጥራትሽ በትክክል ተናገርሽ አለኝ።
እንዲህ በክብር እያናገረኝ ያለው ሕይወቴን ሁሉ እያወቀ ነበር
የሕይወት ውሀንም እንደሚሰጠኝ ነገረኝ።
እኔም ነቢይ መሆኑን ተገነዘብክና እስከ ዛሬ ማንም ያልመለሰልኝንና ከባዱን
የኃይማኖት ጥያቄ ጠየቅኩት፡
አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ እናንተ ግን ሰው ሊሰግድ የሚገባው በኢየሩሳሌም ነው
ትላላችሁ ስለው
እርሱ ግን እንደ ኃይማኖተኛም አልመሰልኝም
እግዚአብሔር መንፈስ መሆኑን የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት
እንደሚሻ ነገረኝ
በመጨረሻም መሲህ ይመጣል እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል ብየ ልሰናበተው ስል
የምናገርሽ እርሱ እኔ ነኝ አለኝ
ይገርማል ይደንቃል መሲህ ሆኖ ሳለ አናገረኝ
ገመናየን ሁሉ እያወቀ አብሮኝ ቁጭ ብሎ ሰማኝ።
ለኃጢአቴ ቅጣት ሳይሆን የሕይወት ውሀ ሰጠኝ።
እንስራየን ትቼ ወደ ከተማ ሮጥኩ መቼም ሁለት ነገር ተሸክሜ መሮጥ አልችልም።
አንዱ ቀላልና በደስታ የሚሞላ አንዱ ግን ከባድ የእንስራ ውሀ። ስለዚህ እንስራውን
ትቼው ልቤ በደስታ እየዘለለ እግሬ እንደ ልጅነቴ ፈጠነ።
ወደ ከተማ ሄጄ ለሰዎች ሁሉ ተናገርኩ። የደስታየ ብዛት ፍርሃቴን ገፈፈልኝ። ምን
ይሉኛል ብየ አቀርቅሬ መሄዴን ረሳሁት። ቀና ብየ በደስታ ድምጽ መናገር ጀመርኩ፡
ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርሃቴ ለቆኝ በድፍረት ተናገርኩ
የሚገርመው አመኑኝ።
የምናገረው ነገር የሚታመን ሴት ሆንኩኝ
ከሰዎች ያጣሁትን ፍቅር ከዚህ ሰው አገኘሁ።
ከሰው ሁሉ ፊት የተናቅሁ የሆንኩትን አከበረኝ
አምስት ጊዜ አግብቼ የፈታሁትን ተቀበለኝ።
ይህን ሁሉ እያወቀ የከበረ ስጦታውን ሰጠኝ።
መለስ ብየ እርሱ ማን መሆኑን ከማወቄ በፊት እንዴት እንዳየሁት የጠየቅኩትን እስኪ
ላስብ ። እጅግ ሰቀጠጠኝ
ተራ አይሁዳዊ ሰው መስሎኝ ነበር
እንደ አይሁድ ትእቢተኛና የሚንቀኝ መስሎኝ ነበር።
ስለዚህ ልኩን ላሳየው ሞከርኩ
መቅጃ እንኳ እንደሌለው በመንገር እንደምበልጠው ልነግረው ሞከርኩ
ከአባታችን ከያእቆብ እንደማይበልጥ አሳየሁት
ያለኝን ሁሉ በመደርደር ከርሱ እንደምበልጥ ላሳየው ሞከርኩ
አርሱ ለካስ የዘላለም አምላክ ነበረ
ዝቅ ብሎ እንዲያናግረኝ ያስገደደው የርሱ ጥማት ሳይሆን የኔን ጥማት ለማርካት
ከጠፋሁበት ምድረ በዳ ሊያወጣኝ ነበረ
የሰማነውን ያየነውን ነገር ማን አምኖአል?
አመጣጡ የማይታመን ነው
ዝቅታው የማይታመን ነው
ፍቅሩ የማይታመን ነው
ትእግስቱ የማይታመን ነው
ቅዱስ ሆኖ ሳለ ያንን ሁሉ የሕይወቴን ኃጢአት እያየ
በቁጣ እንኳ አልተናገረኝም።
አይሁዳዊ ሰው ስትሆን ያልኩት ያ የዘላለም አምላክ ነበረ
መቅጃ የለህም ያልኩት ውቅያኖስን በእፍኙ የሰፈረውን ነበረ
ከያእቆብ ያሳነስኩት የያእቆብን አምላክ ነበረ።
አቤት ምህረት አቤት ፍቅር.…
ማነሱ፤ ደም ግባት የሌለው መሆኑ፤ የባሪያን መልክ መያዙ ፤ የሰው ልጅ አምላክነቱን
እንዳያይ ጋረደው።
በታናሽነቱ ውስጥ የታየው ውበትና ፍቅር ግን ያልተገመቱ የተናቁ ሰዎችን ማረከ።
ከእነዚህም አንድዋ እኔ ነኝ።
እኛስ??
ይህች ሳምራዊት ሴት ማናት? ማነው?
ይህችን ሴት እንዲህ ከተቀበለ እኛንስ?
በዚህች ዓለም ከስንት ነገር ጋር ተጋብተናል?ስንት ጊዜ አግብተን ፈትተናል?
ስንት ጊዜ ከብዙ ከሚያረክስ ነገር ጋር ተጋብተናል ተባብረናል።
ይህን ሁሉ እያወቀ የሕይወት ውሀ እንኩ ይለናል።
ውሀ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑን ብታውቂስ ኖሮ
ብናውቅስ ኖሮ?
የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል?የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን
ተገልጦአል?
ትንቢተ ኢሳይያስ 53
1 የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጦአል? 2
በፊቱ እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል፤ መልክና ውበት
የለውም፥ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም።
3 የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፤ ሰውም ፊቱን
እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፥ እኛም አላከበርነውም።
ዮሐ.12
35 ኢየሱስም፦ ገና ጥቂት ጊዜ ብርሃን ከእናንተ ጋር ነው። ጨለማ እንዳይደርስባችሁ
ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ በጨለማም የሚመላለስ ወዴት እንዲሄድ አያውቅም። 36
የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃኑ እመኑ አላቸው። ኢየሱስም
ይህን ተናግሮ ሄደና ተሰወረባቸው።
37-38 ነገር ግን ይህን ያህል ምልክት በፊታቸው ምንም ቢያደርግ፤ ነቢዩ ኢሳይያስ፦
ጌታ ሆይ፥ ማን ምስክርነታችንን አመነ? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገለጠ? ብሎ
የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ በእርሱ አላመኑም።
39-40 ኢሳይያስ ደግሞ፦ በዓይኖቻቸው እንዳያዩ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥
እንዳይመለሱም፥ እኔም እንዳልፈውሳቸው፥ ዓይኖቻቸውን አሳወረ ልባቸውንም
አደነደነ ብሎአልና ስለዚህ ማመን አቃታቸው።
41 ክብሩን ስለ አየ ኢሳይያስ ይህን አለ፥ ስለ እርሱም ተናገረ።
42 ከዚህም ጋር ከአለቆች ደግሞ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ ነገር ግን ከምኵራብ
እንዳያስወጡአቸው በፈሪሳውያን ምክንያት አልመሰከሩለትም፤
43 ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ወደዋልና።
44 ኢየሱስም ጮኸ፥ እንዲህም አለ፦ በእኔ የሚያምን በላከኝ ማመኑ ነው እንጂ በእኔ
አይደለም፤
45 እኔንም የሚያይ የላከኝን ያያል።
46 በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ።
47 ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁምና ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀው
ቢኖር የምፈርድበት እኔ አይደለሁም።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን።
መምህር ጸጋ።
ፕሌኖ ቴክሳስ