በመምህር ጸጋ
እግዚአብሔር ይህንን ሁሉ ፍጥረት የፈጠረው የሚታየውንና የማይታየውን ሁሉ የሰራው ይህንን ውብ ፕላኔት ጨረቃን ጸሐይንና ከዋክብትን በመጨረሻም የሰውን ልጅ በራሱ መልክና አምሳል የፈጠረው ከምን ተነስቶ እንደሆነ ጠይቃችሁ ታውቃላሁ?? መቸም አንድ ነገር ሲሰራ ሲፈጠር መነሻ ምክንያት አለው፡፡ እንኳንስ ይህ ሁሉ ውስብስብ ንድፈ ፍጥረት ቀርቶ የሰው ልጅ እንኳ አንድ ነገር ሲሰራ በመጀመሪያ አስቦና አቅዶ ነው፡፡ ከተቀመጣችሁበት ወንበር ጀምሮ የምትጠቀሙባቸው ጥቃቅን እቃዎች ሁሉ ሳይቀሩ ለአንድ ዓላማ ታስበው የተሰሩ ናቸው፡፡ የምትነዱ መኪና የምትበሩበት አውሮፕላን በእጃችሁ የያዛችሁት ስልክ እና በቢሮአችሁ ያለው ኮምፒውተር ወዘተ ሰው ለተለያዩ ዓላማዎች አስቦና አቅዶ የፈጠራቸው ናቸው፡፡
“እግዚአብሔር ይህንን ሁሉ ፍጥረት የፈጠረው የሚታየውንና የማይታየውን ሁሉ የሰራው ይህንን ውብ ፕላኔት ጨረቃን ጸሐይንና ከዋክብትን በመጨረሻም የሰውን ልጅ በራሱ መልክና አምሳል የፈጠረው ከምን ተነስቶ እንደሆነ ጠይቃችሁ ታውቃላሁ??“
ችግር የፈጠራ ምክንያት ነው እንደሚባለው የሰው ልጅ ይህንን ሁሉ የቴክኖሎጂ ውጤት የሰራው ችግሩን ለማቃለል እና ከዚያም አልፎ ባለጸጋ ለመሆን ነው፡፡ ለምሳሌ ሰው ክንፍ ያለውና የሚበር ቢሆን ኖሮ መኪናም ሆነ አውሮፕላን ባልሰራም ነበር፡፡ እነዚህን ነገሮች እንዲሰራ ያስገደደው ውስንነቱና የያዘው አካል ልቡ የሚፈልገውን ያህል ፈጥኖ የሚፈልገው ቦታ ስለማይደርስለት ነው፡፡ እንደዚሁም ኢንተርኔትንና የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን የፈለሰፈው በጊዜና በቦታ ያለውን ውስንነት ለማስወገድ ሲሆን እንደምናየው ዓለም ወደ አንድ መንደር የተቀየረች ያህል የሰው ልጆች በፍጥነት የሚገናኙበት ሁኔታ ተፈጥሮአል፡፡
እንግዲህ ከዚህ እንደምናየው የሰው ልጅ የፈጠራቸውን ነገሮች ሁሉ የፈጠራቸው ችግሩን ለማቃለል ውስንነቱን ለመቅረፍና ክፋቱን ወይም ሥጋዊ ባህርዩን ለመግለጽ ነው፡፡ ከትናንሽ እስከ ትላልቅ የጦር መሳሪያዎችን የፈጠረውም በአንድ ጊዜ ብዙ ሰዎችን የመግደል ብቃቱን ለማሳደግ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ የምናየው ሰው የፈጠራቸውን ነገሮች የፈጠራቸው ማንነቱን ከሚያንጸባረቀው ባህርዩ ተነስቶ ችግሮቹን ለመፍታት ነው፡፡ ሰውስ ውስን ፍጥረት ስለሆነ ውስንነቱን ለማቃለልና ጉድለቱን ለመሙላት ይህን ሁሉ ፈጠረ፤ ምንም የሚጎድለው የሌለው ታላቅና የክብር አምላክ እግዚአብሔር ይህንን ሁሉ ፍጥረት የፈጠረው ለምን ይሆን? ጉድለቱን ለመሙላት እንዳንል ጉድለት የሌለው ፍጹም አምላክ ነው፡፡ እንግዲያውስ ስለምን ፈጠረው? እኛንስ ከፍጥረታት ሁሉ በላይ አክብሮ በመልኩና በአምሳሉ እንዲፈጥረን ያደረገው መነሻ ምክንያት ምን ይሆን? ለመልሱ በቀጣዩ ክፍል ይጠብቁን፡፡