የእግዚአብሔር ፍቅር
ክፍል ሶስት
እግዚአብሔርም፦ ብርሃን ይሁን አለ፤ ብርሃንም ሆነ። ዘፍ.1:3 ብርሃን የህይወት ምንጭ ነው፡፡ ብርሃን ከሌለ ህይወት የለም፡፡ ስለዚህ ህይወት ያላቸውን ፍጥረታት ለማምጣት ብርሃን ይሁን በማለት ጀመረ፡፡ ከዚያም በውሀና በጭለማ ተወርሳ መልክ አልባና ባዶ የነበረችውን ምድር ያስውባት ጀመር፡፡ ከጠፈር በላይ ያለውን እና ከጠፈር በታች ያሉትን ውሆች በመለየት ጠፈሩን አደረገ፡፡ ከጠፈር በታች ያለውን ውሀ ወደ አንድ ቦታ ይሰብሰብ በማለት የብሱንና ባህሩን ለየ፡፡ በመቀጠልም የብስዋ የተገለጠው ምድር ዘርን የሚሰጥ ሳርንና ቡቃያን የሚያፈራውንም ዛፍ ሁሉ እንድታበቅል አዘዛት እንዲሁም ሆነ፡፡ ጸሐይንና ጨረቃንም በምድር ላይ እንዲያበሩ በሰማይ ጠፈር አኖራቸው፡፡ በመቀጠልም በባህር ላይ የሚኖሩትንና የሚንቀሳቀሱትን አሳዎችንና እና ሌሎችንም ፍጥረታት ፈጠረ፡፡ ከዚህም በኋላ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን እንስሳትን ሁሉ ፈጠረ፡፡ ይህንን ሁሉ ሲፈጥር አንድ የተለየ ፍጥረትን በልቡ ይዞ እያሰበ ነበር፡፡ ያም ልዩ ፍጥረት የከበረው የሰው ልጅ ወይም እኔና እናንተ ነበርን፡፡ አዳምና ሄዋን በልደታቸው ቀን ያገኙት ስጦታ ምድርን ከነሙሉ ፍጥረትዋ ነበር፡፡ ሰውን በልቡ ያኖረውና እጅግ የሚወደው ፍጥረት ነው፡፡ ምድርን እንደዚህ ካስዋበለትና ካሸበረቃት በኋላ ክብሩንና መንግሥቱንም በምድር ላይ ሊገልጥበት የሚፈልገውን ይህንን እጅግ የተወደደ ሰው በስድስተኛው ቀን ፈጠረው፡፡ ቃሉ እንዲህ ይላል፡፡ እግዚአብሔር የምድር አራዊትን እንደ ወገኑ አደረገ፥ እንስሳውንም እንደ ወገኑ፥ የመሬት ተንቀሳቃሾችንም እንደ ወገኑ አደረገ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ። እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።” {ኦሪት ዘፍጥረት 1:25-27}:: ይህንን ቃል አስተውለን ስንመለከተው እጅግ የሚገርም እና ልባችንን በፍስሐ የሚሞላ ነው፡፡ ከላይ ጀምሮ ስናነበው ሁሉንም እንደ ወገኑ እንደወገኑ አደረገ እያለ ይመጣና ሰው ላይ ሲደርስ ግ ን እንደወገኑ የሚለውን ቃል አይጠቀምም፡፡ ምክንያቱም ሰው የራሱ ወገን አይደለምና፡፡ እንግዲህ ሰው እንደወገኑ ካልተባለ የማን ወገን ነው? “እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።” ምድር ህያዋን ፍጥረታትን ታውጣ ፍሬ ያላቸውን ዛፎች ታብቅል እያለ በቃሉ ሲያዝና ሲፈጥር የነበረው እግዚአብሔር ሰው ላይ ሲደርስ ግ ን ለሌላ ወይም ለሰው ለራሱ ሳይሆን ለራሱ ተናገረ፡፡ እግዚአብሔርም አለ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር የሚለው ቃል ስሉስ እግዚአብሔር በስሉስነቱ ለራሱ የተናገረው ስሉስ ቅዱስ የሆነው እግዚአብሔር ነው፡፡ ሰው ለመፍጠር የራሱን መልክ ተመለከተና በመልካችን እንደምሳሌአችን እንፍጠር አለ፡፡ ሰውንም በመልኩ ፈጠረ፡፡ ይህ እጅግ የሚገርም ፍቅር ነው፡፡ ይህ ልብን የሚያቀልጥ ኃያል ፍቅር ነው፡፡ እግዚአብሔር እኔን አንቺን አንተን በመልኩ ፈጠረ፡፡ በእግዚአብሔር መልክ መፈጠር እንዴት የሚደንቅ ክብር እንደሆነ አስባችሁ ታውቃላሁ? አስተውለን ስነመለከተው ይህ የፍቅር ጥግ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ ፈጠረው፡፡ መልኩን በማልበስ መልኩን በማተም ፍቅሩን ገለጸው፡፡ መልኩ የፍቅሩ ማህተም ነው፡፡ ነገሥታት ወይም ባለስልጣኖች ፊርማቸው ማህተማቸው የከበረ ነው፡፡ ስልጣናቸውን ክብራቸውን የሚያስተላልፉበት ነው፡፡ ነገር ግ ን ማህተማቸው ውጫዊ ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን እጅግ ስለወደደን እና ከፍቅር ልቡ ስላመጣን በመልኩ በባህርዩ በራሱ አተመን፡፡ {ይቀጥላል}