በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፡፡
“መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፥ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥” 1 ቆሮ 1፤22-23
ቅዱስ ጳውሎስ በሥጋ ከአይሁድ ዘር እንደሆነ የታወቀ ቢሆንም በዚህ ስፍራ ግን ራሱን ከአይሁድ ህዝብ ውጭ አድርጎ መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ ካለ በኋላ እኛ ግን በማለት ራሱን ከሌላ ወገን ጋር ይቆጥራል፡፡ እርሱ ራሱ ከአይሁድ ሆኖ እንዴት ወደ ውጭ እያመለከተ ሁለተኛ ወገንን በሚጠቁም መልክ አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ ብሎ ይናገራል?? ለመሆኑ ራሱን አስገብቶ እኛ ግን ብሎ የጠቀሰው ወገንስ የቱ ነው? ኦ ይህ ቅዱስ ጥያቄ ነው መልሱ ደግሞ ቅድስተ ቅዱሳን፡፡ እርስዎም ከሚኖሩበት ካደጉበት የኔ ካሉት ምድራዊ ዘርና ባህል ከተላበሰ የሞተ ማህበረሰብ ወጥተው እነርሱ ብለው ይናገሩ ዘንድ ቅዱሱ ወንጌል የሚያለብስዎትን አዲሱን ሰው ለመልበስ ቃሉን በእምነት ይስሙ፡፡