Pay attention to what you hear

የእግዚአብሔር ፍቅር

“አላቸውም፦ ምን እንድትሰሙ ተጠበቁ።”

የማርቆስ ወንጌል 4፥24

በመምህር ጸጋ

ያገኘውነው ሁሉ እንደማንበላ ያገኘነውን ሁሉ ልንሰማ አይገባም፡፡

ያገኘነው ሁሉ ከበላን እንደምንታመም የተነገረውን ሁሉ ከሰማን እንታመማለን፡፡ አሁን በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የታመሙት ለሚበሉት የሚጠነቀቁትን ያህል ለሚሰሙት ስለማይጠነቀቁ፡፡ 

በተለይ በዚህ በማሕበራዊ መገናኛ ስትሰሟቸው ከምትውሉ ሰዎች ውስጥ ዘጠና ከመቶው መርዘኞች ናቸው፡፡ የእባብ መርዝ ከከንፈሮቻቸው በታች አለ፡፡ ከዚህ ለመዳን  ጆሮዎቻችሁን ለእግዚአብሔር ቃል ቀድሱ፡፡ የምንሰማውን ካልመረጥን የምንኖረውን መምረጥ አንችልም፡፡ የምንኖረው ሰምተን ያመነውን ነውና፡፡ የምንሰማው ነገር የእግሮቻችንን አካሄድ ይቃኛል፡፡ እግሮቻቸውን ከመራመዳቸው በፊት አይናችን ልባችንና ፈቃዳችን ይራመዳል፡፡ ውስጣችን ወደመራው ውጫችን ይጓዛል፡፡ ሰዎች ወደ ወደሚፈልጉት አቅጣጫ ሊወስዷችሁ ሲጀምሮ እግሮቻችሁን በመጎተት አይጀምሩም፡፡ በንግግራቸው ሐሳባችሁን በማበላሸትና በአመለካከታቸው እናንተን በመቃኘት ነው የሚጀምሩት፡፡ አንድ ጊዜ በሐሳባቸውና በንግግራቸው ከተሞላችሁ በሁላ እንቢ ማለት አትችሉም፡፡ አካላችሁን አእምሮአችሁን የሚቆጣጠረው የተሞላችሁት ነገር ነው፡፡ በመጠጥ የሰከረ ሰው በልቡ እንዳሰብ አይራመድም የጠጣው መጠጥ በሚፈልገው እንጂ፡፡ ለዚህም ነው እግሮቹ ሲወላገዱና ሰሜንና ደቡብ ምእራብና ምስራቅ ሲረግጡ የምታዩት፡፡ የጠጣው መጠጥ ብልቶቹን ተቆጣጥሮአቸዋል፡፡ እንደዚሁም በክፉ ሰዎች በምድራዊያን በፖለቲከኞች ክፉ ሐሳብ ከተመረዛችሁና ቁጭ ብላችሁ ክፉ ንግግራቸውን ከጠጣችሁ ከዚያ በኋላ እግሮቻችሁን አካሄዳችሁን የሚገዛው ያ ክፉ ሐሳብ ነው፡፡ ሰው መስማት ያለበት የእግዚአብሔርን ቃል ብቻ ነው፤፡ የእግዚአብሔር ቃል ስንሰማ ያ ለህይወታችን መድኃኒት ፈውስ እርካታ ጥጋብ ነው፡፡ ውሀ የጠማው ሰው ውሀ ሲጠጣ እንደሚረካና እንደሚለመልም የእግዚአብሔር ቃል ያለሰልሳል፡፡  ለዚህም ነው ቅዱስ ዳዊት ሲናገር  “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል። እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።” የሚለው፡፡ መዝ 1፤1-3

ቃሉን በቀንና በሌሊት ስናስብ በወንዝ ዳር እንደተተከለች ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ እንሆናለን፡፡ የምንገበውን ነው የምንመስለው፡፡ የምንሰማውንና የምናምነውን ነው በተግባራችን በኑሮአችን የምናሳየው፡፡ ከተሞላነው ውጭ ልንሆን አንችልም፡፡ ስለዚህ እኛ ክርስቲያኖች ለምንሰማው መጠንቀቅ የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ይገባናል፡፡

አካላችሁን አእምሮአችሁን የሚቆጣጠረው የተሞላችሁት ነገር ነው፡፡ በመጠጥ የሰከረ ሰው በልቡ እንዳሰብ አይራመድም የጠጣው መጠጥ በሚፈልገው እንጂ፡፡ ለዚህም ነው እግሮቹ ሲወላገዱና ሰሜንና ደቡብ ምእራብና ምስራቅ ሲረግጡ የምታዩት፡፡ የጠጣው መጠጥ ብልቶቹን ተቆጣጥሮአቸዋል፡፡ እንደዚሁም በክፉ ሰዎች በምድራዊያን በፖለቲከኞች ክፉ ሐሳብ ከተመረዛችሁና ቁጭ ብላችሁ ክፉ ንግግራቸውን ከጠጣችሁ ከዚያ በኋላ እግሮቻችሁን አካሄዳችሁን የሚገዛው ያ ክፉ ሐሳብ ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ለወንጌል ልጁ ለጢሞቴዎስ በላከው መልእክቱ ሰዎች ህይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሱበት ዘመን እንደሚመጣና ህይወትን ከሚሰጠው ቃል ይልቅ ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ማለትም ጊዜአዊ ደስታን የሚሰጧቸውን አስተማሪዎች መስማት እንደሚወዱ እንደዚህ በማለት ይጽፍለታል፡፡“በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤ ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም። ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን  ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ።እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፥ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ።”

2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 4፡1-4

የወንጌል ልጁን ጢሞቴዎስን በኤፌሶን ሲተወውም ክርስቲያኖች ከክርስቶስ ወንጌል ውጭ ተረትንና መጨረሻ የሌለውን የትውልዶች ታሪክ እንዳያደምጡ እንዲያዛቸው እንዲህ  ይመክረዋል፡፡ 

“ወደ መቄዶንያ በሄድሁ ጊዜ፥ አንዳንዶች ልዩ ትምህርትን እንዳያስተምሩና ወደ ተረት መጨረሻም ወደሌለው ወደ ትውልዶች ታሪክ እንዳያደምጡ ልታዛቸው በኤፌሶን ትቀመጥ ዘንድ ለመንሁህ፤ እንደ እነዚህ ያሉ ነገሮች ክርክርን ያመጣሉና በእምነት ግን ላለ ለእግዚአብሔር መጋቢነት አይጠቅሙም።” 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 1፥3-4

የአባት ፍቅር

ከዚህ በታች ያለውን የወንጌል ድምጽ እንዲሰሙ በታላቅ ፍቅር እንጋብዝዎታለን፡፡

ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሆይ ከአባቶቻችን ከሐዋርያት የተቀበልነው ወንጌል ተረትንና መጨረሻ የሌለውን ታሪክ እንዳናዳምጥ ይልቅስ ህይወት ያለውን ቃል ብቻ እንድንመገብ ይመክረናል፡፡ እኛም ከምንሰማው በመጠበቅና መርጠን በመስማት መንፈሳዊ ህይወታችንን እንጠብቅ፡፡ ምናልባት ጆሮ ክፍት ስለሆነ የማንፈልገውን ላለመስማት እንዴት እንድፈነው? ትሉ ይሆናል፡፡ ጆሮ ግን በር አለው በሩ ከውስጥ ከልብ በኩል ነው፡፡ በማስተዋል ቁልፍ ከውስጥ ቆልፉት ከዚያ ወደ ጆሮአችሁ የመጣው ሁሉ ልባችሁ ውስጥ ሳይደርስና ሐሳባችሁን ሳያበላሽ ነጥሮ ይመለሳል፡፡ 

ምን እንድት ሰሙ ተጠበቁ፡ እግዚአብሔር ሁላችሁንም ይባርክ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡

የሥላሴ ማኅበር፤፡

እባክዎትን ለሌሎች ያካፍሉ፡፡

 

Leave a Comment