Jesus Christ the “Majority” One ብዙኃኑ አንድ

የእግዚአብሔር ፍቅር

“ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት አላቸው።”

ዮሐንስ 8:7

"ብዙኃኑ" አንድ ኢየሱስ ክርስቶስ

ከዚህ በታች ያለውን የወንጌል ድምጽ እንዲሰሙ በታላቅ ፍቅር እንጋብዝዎታለን፡፡

በመምህር ጸጋ

“ብዙኃኑ አንድ” የመለኮታዊው ቀመር እይታ፡፡

ዓለም በብዙኃኑ ድምጽ ወይም በኃያላኑ እጅ ትመራለች፡፡ በዓለም ቋሚ እውነት የሚባል የለም፡፡ ብዙኃኑ የተስማሙበት ሁሉ እውነት ነው ስለዚህ ይተገበራል፡፡ ያው ብዙኃኑ ተስማምተው ዛሬ እውነትና ትክክል ያሉት ነገ ሌሎች ከብዙኃኑ የበዙ ሐሰት ነው ካሉት ሐሰት ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በዓለም እውነት የሆነ እውነት የለም፡፡ አለ የሚባለው እውነት ብዙኃኑ በድምጻቸውና በፈቃዳቸው እውነት ያደረጉት እውነት ሲሆን ነገ ብዙኃኑ ልባቸውን ቀይረው ሐሰት ነው ይሉታል፡፡ ስለዚህ ሐሰት በድምጽ ብልጫ እውነት የሚባልባት እውነት በድምጽ ብልጫ ሐሰት የሚባልባት ዓለም ውስጥ ነው የምንኖረው፡፡ ብዙኃኑ የተስማሙበት ሁሉ እውነት ነው በምትለው ዓለም እውነት እየተገደለች እየተቀበረች እየተነሳች እንደገና እየተገደለች ትኖራለች፡፡ እውነትን ሊያጠፉ አይችሉምና እነርሱ እስኪጠፉ ድረስ እውነት በትንሣኤ እየለመለመች ትኖራለች፡፡ አንዱ ዮሴፍ በብዙኃኑ ወንድሞቹ የድምጽ ብልጫ ወደ ጉድጓድ ተጣለ ወደ ግብጽም ተሸጠ፡፡ ነገር ግን ከውድቀቱ ተነስቶ ለመለመ አፈራ፡፡  ብዙኃኑ የተስማሙበት ሁሉ እውነት ለሚመስለንና በብዙኃኑ ድምጽና ድርጊት ስንሰቃይ የምንኖር ሁሉ እውነተኛው እውነት በድምጽ ብልጫ ያልተገኘ መሆኑን በመረዳት ሐሴት እናድርግ፡፡ እውነት እግዚአብሔር ነው፡፡ እውነት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እኔ መንገድ እውነት ህይወትም ነኝ ብሎናልና፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስን ያመነ እውነት አለው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ይህንን ዘላለማዊ እውነት ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል፡፡

ብዙ ኃጢአተኞች ብዙ ድንጋይ እንጂ አንዲት እውነት የላቸውም፡፡

የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል  8 

1 ኢየሱስ ግን ወደ ደብረ ዘይት ሄደ።

2 ማለዳም ደግሞ ወደ መቅደስ ደረሰ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡ። ተቀምጦም ያስተምራቸው ነበር።

3 ጻፎችና ፈሪሳውያንም በምንዝር የተያዘችን ሴት ወደ እርሱ አመጡ በመካከልም እርሱዋን አቁመው፦

4 መምህር ሆይ፥ ይህች ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች።

5 ሙሴም እንደነዚህ ያሉት እንዲወገሩ በሕግ አዘዘን፤ አንተስ ስለ እርስዋ ምን ትላለህ? አሉት።

6 የሚከሱበትንም እንዲያገኙ ሊፈትኑት ይህን አሉ። ኢየሱስ ግን ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ፤

7 መላልሰው በጠየቁት ጊዜ ግን ቀና ብሎ፦ ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት አላቸው።

8 ደግሞም ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ።

9 እነርሱም ይህን ሲሰሙ ሕሊናቸው ወቀሳቸውና ከሽማግሌዎች ጀምረው እስከ ኋለኞች አንድ አንድ እያሉ ወጡ፤ ኢየሱስም ብቻውን ቀረ ሴቲቱም በመካከል ቆማ ነበረች።

10 ኢየሱስም ቀና ብሎ ከሴቲቱ በቀር ማንንም ባላየ ጊዜ፦ አንቺ ሴት፥ እነዚያ ከሳሾችሽ ወዴት አሉ? የፈረደብሽ የለምን? አላት።

11 እርስዋም፦ ጌታ ሆይ፥ አንድ ስንኳ አለች። ኢየሱስም፦ እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ አላት።

በብዙኃኑ ድምጽ የሚመሩት ጻፎችና ፈሪሳዊያን በማለዳ አንዲትን በአመንዝራነት የተያዘች ሴት ሊወግሩ እግረ መንገዳቸውን ግን ኢየሱስ ክርስቶስን ሊፈትኑባት ወደርሱ ይዘዋት መጡ፡፡ እነዚህ በድምጽ ብልጫ በተገኘ እውነት የሚያምኑ ብዙኃን እውነተኛ እውነት ወደሆነው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ይዘዋት መጡ፡፡ ብዙኃኑ ወደ አንዱ ይዘዋት መጡ፡፡ ይህ አንድ ግን እውነተኛና ዘለዓለማዊ እውነት የእውነትም መሠረት ነውና ብዙኃኑ አንድ ሊባል ተገብቶታል፡፡ አንድ ነው ነገር ግን ሁሉን ያሸንፋል አንድ ነው  ነገር ግን ጻድቅ ፈራጅ ነው፡፡ አንድ ነው ነገር ግን ዘላለማዊ አምላክ ነው አንድ ነው ነገር ግን ሁሉን ቻይ አምላክ ነው፡፡ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ እነዚህ ከሳሾች የያዙት እውነት በድምጽ ብልጫ የተፈጠረ የሰው እውነት ነውና በራሱ መለኪያም የወደቀ ነው፡፡ አንዲት ሴት ብቻዋን አታመነዝርም፡፡ ስታመነዝር ከተያዘች አብሯት ሲያመነዝር የነበረ ወንድ አለ፡፡ እነዚህ በእውነት ያልቆሙ ብዙኃን ግን እርሱን ትተው እርስዋን ብቻ ይዘዋት መጡ፡፡ ይህች ሴት ተባብረው በአንድ ድምጽ ሊገድልዋት ተስማምተው በእጆቻቸው ብዙ ድንጋዮችን ይዘው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ አመጥዋት፡፡ አሁን በብዙኃኑ አንድ እና በኅዳጣኑ ብዙኃን መካከል ቆማለች፡፡ ደጋግመው በጠየቁት ጊዜ የነርሱን ሰራሽ እውነት የሚሽር እውነተኛ እውነት ከብዙኃኑ አንድ ከከርስቶስ አንደበት ተሰማ፡፡ “ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት አላቸው።” ለመሆኑ ይህን ብሎ የፈረደው ለምንድን ነው? ድንገት አንድ ጻድቅ በመካከላቸው ቢገኝና ወግሮ ቢገድላትስ? እንዲህ በማለቱ ይህችን ሴት አደጋ ላይ አልጣላትንም? ትሉ ይሆን? ኦ ይህንንማ በአምላክነቱ ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡ እርሱ ከሰማየ ሰማያት የወረደው ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ለምን ሆነና? በሰው ልጆች መካከል አንድም ጻድቅ ስለሌለ አይደለምን? ስለዚህም  ነገር አስቀድሞ በነቢዩ ኢሳይያስ ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር “እውነትም ታጥቶአል፥ ከክፋትም የራቀ ሰው ለብዝበዛ ሆኖአል። እግዚአብሔርም አየ ፍርድም ስለሌለ ተከፋ፡፡

 

ሰውም እንደሌለ አየ፥ ወደ እርሱ የሚማልድ እንደሌለ ተረዳ ተደነቀም፤ ስለዚህ የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት፥ ጽድቁም አገዘው። ጽድቅንም እንደ ጥሩር ለበሰ፥ በራሱም ላይ የማዳንን ራስ ቍር አደረገ፤ የበቀልንም ልብስ ለበሰ፥ በቅንዓትም መጐናጸፊያ ተጐናጸፈ።” ኢሳ 59፡15-17፡፡ የእግዚአብሔር ክንድ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ የሰው ልጆችን ሊያድን የመጣው ሁሉም ስለወደቁ ስለሞቱና ከርሱ ስለራቁ ነው፡፡ በነርሱ መካከል አንድስ እንኳ ጻድቅ የለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ከነቢዩ ጋር በመስማማት እንዲህ ይለናል፡፡ “ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፥ አንድ ስንኳ የለም።ጕሮሮአቸው እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፥ በመላሳቸውም ሸንግለዋል፤ የእባብ መርዝ ከከንፈሮቻቸው በታች አለ፤አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቶበታል፤እግሮቻቸው ደምን ለማፍሰስ ፈጣኖች ናቸው፤ጥፋትና ጉስቁልና በመንገዳቸው ይገኛል፥የሰላምንም መንገድ አያውቁም። በዓይኖቻቸው ፊት እግዚአብሔርን መፍራት የለም።” ሮሜ 3፡11-18 ይህ እንግዲህ የሰው ልጆች ሁሉ ማንነት ነው፡፡ ይህችን ሴት ለመውገር ድንጋይ ይዘው በፊት የቆሙትም እነዚህ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ ይውገራት ሲል አንድም እንኳ እጁን ለማንሳት አቅምን የሚያገኝ እንደሌለ በማወቅ ነው፡፡ 

 ይህን በሰሙ ጊዜ ግን እንኳንስ ድንጋዩን ሊወረውሩ ይዘውት መቆም አልቻሉም፡፡ እንኳንስ ይዘውት ሊቆሙ ባዶ እጃቸውንም ሊቆሙ አልቻሉም፡፡ አንድ አንድ እያሉ ወጡ፡፡ በእውነት ፊት ሐሰት አይቆምምና፡፡ በድምጽ ብልጫ የተገኘ የሰው እውነትም በእውነተኛው እውነት እርቃኑን ይቀራል፡፡ የብዙ ኃጢአተኞች ድምጽ አንዲት እውነት ሊያመነጭ አይችልምና፡፡ ብዙ ኃጢአተኞች ብዙ ድንጋይ እንጂ አንዲት እውነት የላቸውም፡፡ ስለዚህ የከበብዋት ኃጢአተኞች አንድ አንድ እያሉ ከወጡ በኋላ ይህች ሴት ከብዙኃኑ አንድ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ብቻ ቀረች፡፡ አዎ አንድ ብቻውን ቢሆንም ሰማይንና ምድርን ያጸና እውነት ነው፡፡ አንድ ብቻውን ቢሆንም የእግዚአብሔር ሙላት ሁሉ በርሱ የተገለጠ እውነት ነው፡፡ እርሱ ብቻውን ቢሆን ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ በእኛ ያደረ ነው፡፡ እርሱ ብቻውን ቢሆንም የእውነት ሚዛንና መለኪያ ነው፡፡ እርሱ ብቻውን ቢሆንም ጸሐይን እና ከዋክብትን በእጁ የያዘ የጽንፈ ዓለሙን ሁሉ ምሕዋር በዓይኖቹ የሚዘውር ነው፡፡ ጻድቅ ዳኛ ርህሩህ አባት በፊትዋ ተቀምጦአል፡፡ ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ ይውገራት ሲል ሰምታዋለች፡፡ ከነርሱም ኃጢአት የሌለበት አንድም እንኳ ስላልተገኘ ሁሉም ሸሽተው ወጥተዋል፡፡ አሁን በፊቱ የቆመችው ጌታ ግ ን ኃጢአት የሌለበት ቅዱስና ጻድቅ ነው፡፡ እርሱ ኃጢአት የለበትምና በርስዋ ላይ የመፍረስ ስልጣን አለው፡፡ ቢፈርድባት ደግሞ ድንጋይ ማንሳትም አያሻውም እስትፋስዋ በእጁ ነውና፡፡ እንግዲህ ይህ ጻድቅ ፈራጅ ምን ይላት ይሆን? ፍርዱን ከርሱ አንደበት እንስማ፡፡ “ኢየሱስም ቀና ብሎ ከሴቲቱ በቀር ማንንም ባላየ ጊዜ፦ አንቺ ሴት፥ እነዚያ ከሳሾችሽ ወዴት አሉ? የፈረደብሽ የለምን? አላት። እርስዋም፦ ጌታ ሆይ፥ አንድ ስንኳ አለች። ኢየሱስም፦ እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ አላት።”  አዎ ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ ይውገራት ሲል የሙሴን ህግ ይሽራል ብለው ለሚከሱት በመጡበት መንገድ ለመመለስ እንጂ እውነት ይህች ሴት እንድትወገር ፈልጎ አልነበረም፡፡ ቢሆንማ ኖሮ የጽድቅ ራስ የሆነው እርሱ እስትንፋስዋን በእጁ የያዘ እርሱ እንሆ በፊትዋ አለ፡፡ እርሱ የመጣው የጠፋውን ፈልጎ ሊያገኝ ኃጢአተኛውን ከወደቀበት ሊያነሳ የሰውን ልጅ ሁሉ ከሞት ሊያድን እንጂ ለፈርድ አልነበረምና “እኔም አልፈርድብሽም ሂጂ  ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ አላት” ኦ ይህ እንዴት ልብን የሚያዘልል የፍቅር ፍርድ ነው፡፡ ይህ እንዴት ዓይነት ርህራሄ ነው? በጽንፈ ዓለሙ ላይ የመጨረሻው ጻድቅና የመጨረሻዋ ኃጢአተኛ ሲገናኙ የተገለጠው ይህ ፍርድ የሁላችንንም ልብ ያዘልላል፡፡ በተለይ ይህች ሴት እኛን ሁሉ የወከለች እንደሆነች የተረዳነውን ሁሉ የበለጠ ያስደስታል፡፡ ጻድቁ ጌታ አፍቃሪው አባት ለኛ ያለው ልብ ምን እንደሚመስል ግልጥ አድርጎ የሚያሳየን ፍርድ ነው፡፡ እርሱ እንደ ከሳሾችዋ አሁን ያደረገችውን ኃጢአት ብቻ ሳይሆን ሁለንተናዋን የሚያነቡ ዓይኖች ያሉት አምላክ ነው፡፡ የርስዋን ኃጢአት ሲያነቡለት የነርሱን ስላነበበላቸው ነው ወጥተው የሄዱት፡፡ ሁለንተናዋ በፊቱ የተራቆተና የተገለጠ ቢሆንም እኔም አልፈርድብሽም ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ አላት፡፡ ይህም ድምጹ የርሱ ዓላማ እኛን ከኃጢአት ማዳን ከፍርድ ከኩነኔ ማዳን እንጂ ሌላ እንዳልሆነ ያሳየናል፡፡

ወንድሞቼ እህቶቼ እናንተስ በብዙዎች ተከበዋችኋል? የስንት ሐይማኖተኞች የስንት ጥበበኞች የስንት ፖለቲከኞች የስንት አመጸኞች ኮቴ በጆሮአችሁ ይሰማል? የምትኖሩባት ዓለም በሚፈርዱባችሁና በድንጋይ ወግረው ሊያጠፏችሁ በሚፈልጉ ሰዎች የተሞላች ናት፡፡ የእግዚአብሔር ፖሊስ ነን የሚሉት ሐይማኖተኞቹም ከሁሉ ይልቅ የከፉት ናቸው፡፡ እነዚህ የሐይማኖት መሪዎች የአይሁድን ህዝብ በማነሳሳት በብዙኃኑ ድምጽ የእውነትን ጌታ ያሰቀሉ ናቸው፡፡ ዓለም ጥበበኞችዋም ነገሥታትዋም የሐይማኖት መሪዎችዋም የእውነት ጠላቶች ናቸው፡፡ በነርሱ ዘንድ ሁሉ በድምጽ ብልጫ ይወሰናል፡፡ ህዝብ ተሰብስቦ እውነት ይሰቀል ካለ ይሰቀላል፡፡ ይቀበር ካለ ይቀበራል፡፡ እውነት በነርሱ ዘንድ የለምና የፍለጉትን ይገድላሉ የፈለጉትን ይኮንናሉ፡፡ 

ይህች ዓለም ምንም በደል ያልተገኘበትን የፍቅር ጌታም በድምጽ ብልጫ ሰቅላ ገድላዋለች፡፡ ስቀለው ስቀለው የሚለው የካህናት አለቆችና የአይሁድ ህዝብ ድምጽ የጲላጦስ ስስ ህሊና አሸንፎ ከገረፈው በኋላ እንዲሰቅሉት አሳልፎ ሰጠው፡፡ ከከተማቸው አውጥተው  በጎዳና ዳር ላይ ከሰቀሉት በኋላም አላፊ አግዳሚው ሁሉ ሲፈርድበትና ሲሳለቅበት ዋለ፡፡ የክብር ጌታ የእውነት ራስ በሁለት ወንበዴዎች መካከል ተሰቅሎ ከአመጸኞች ጋር ተቆጠረ፡፡ ዓለም የፈጠራትን ጌታ እንዲህ ከፈረደችበት እኛንም የርሱን ተከታዮች እንዴት? ስለዚህ እነዚህ ነፍሰ ገዳዮች በየቀኑ ይከቡናል፡፡ 

እኛም በነርሱ መካከ ስንኖር ከበባቸው ነፍሳችንን ያስጨንቃታል፡፡ ሰዎች ለጮሁበት ካልጮሃችሁ ለቆሙበት ካልቆማችሁ የወደዱትን ካልወደዳችሁ ያሰቡትን ካላሰባችሁ የደገፉትን ካልደገፋችሁ በድንጋይ ሊወግሯችሁ ይሰበሰባሉ፡፡ ምናልባት አሁን ድንጋዩ የቃላት ድንጋይ የሐሰትና የሃሜት ስምን የማጥፋት የአድማ ድንጋይ ሊሆን ይችላል፡፡ ማህበራዊ ሚድያዎች ይህንን ድንጋይ ወርውሮ ለመምታት እንዲያመቹ ሆነው የተሸመኑ ናቸው፡፡ ባህር ማዶ ያለውን እና በአካል አይተውት የማያውቁትን ሰው እንኳ ለመውገር አመቻችቶ አቅርቦ ይሰጣችኋል፡፡ በማሕበራዊ ሚዲያ አለም አቀፍ የመውገርና የመግደል ሥራ ሲሰራ ይውላል ያድራል፡፡ በዚህ ሁሉ በከበባችሁ ገዳይ መካከል ግን አንድ እውነተኛ አፍቃሪና መኃሪ ዳኛ ቆሞአል፡፡ የዚህን ሁሉ ከባቢ ድምጽና ጫጭታ በአንድ ድምጽ የሚሽር ጻድቅ ዳኛ አለ፡፡ ይህም ዳኛ ለዚህች ሴት እኔም አልፈርድብሽም ብሎ የኃጢአትን ስርየት የሰጣት የፍቅር ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እንደ በደላችን ሳይሆን እንደ ምህረቱ እንደ ጥፋታችን ሳይሆን እንደ ፍቅሩ ጥልቀት የሚበይንልን የሚፈርድብን ሳይሆን የሚፈርድብን ይህ የፍቅር ጌታ ብቻ ነው፡፡ ዓለም ሁሉ ከሚያጅበንና ከሚያጨበጭብልን  ድንጋይ ተሸካሚው ማኅበረሰብ ከሚቀበለን ይልቅ ይህ ድንቅ ጌታ ከኛ ጋር ሆኖ ዓለም ሁሉ ቢከዳን ይሻለናል፡፡ እርሱ ከዓለም ሁሉ በላይ ነው፡፡ አህዛብም ሁሉ በገንቦ እንዳለች ጠብታ ናቸው፡፡ ታላቁና የተፈራው ንጉሥ ሄሮድስ በክርስቶስ ፊት ቀበሮ ነው፡፡ ወደ ቤተ መንግሥቱ እንዲመጣና እንዲያየው መል እክተኞች ሲልክበት እንደዘመኑ የሐይማኖት መሪዎች ተከበርኩ ብሎ አልሄደም፡፡ ይልቅስ ሄዳችሁ ለዚያች ቀበሮ እንዲህ እንዲህ በሏት አላቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁሉ ያነሰ ሆኖ ቢገለጥም ከሁሉ በላይ የሆነ አምላክ ነው፡፡ የአውግስጦስ ዙፋን የጴላጦስ ስልጣን  የሄሮድስ ሰይፍ ለርሱ ምንም ናቸው፡፡ ሊገድለው ስልጣን እንዳለው በሚናገረው በጲላጦስ ፊት ቆሞ እውነትን የመሰከረ እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል በማለት ያወጀ የእውነት ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ይህን ጌታ በክብሩ ስናየውና ፈለጉን ስንከተል ከርሱ ሌላ የሚበዛብን ከርሱ ሌላ ታላቅ የሚሆንብን ማንም የለም፡፡ እርሱ ለኛ ከምድር አህዛብ ሁሉ ይበዛል፡፡ እርሱ ለኛ አንድ ሆኖ ብዙ ነው፡፡ አሮጌው አዳም እራሱን አባዝቶ ሰባት ቢልዮን ደርሻለሁ ቢለንም ሰባቱ ቢልዮኖች ያው የአንዱ አዳም ዝርዝር ሳንቲሞች መሆናቸውን እናውቃለን፡፡ አንድም ሆነው ብዙ አያስፈሩንም፡፡ ስለዚህ ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር ሆነን በእምነት እንደዚህ እናውጃለን 





እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል? ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም? እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፥ የሚኰንንስ ማን ነው? የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።” ሮሜ 8፡31-39

ለኛ ብዙኃኑ ጠማማውና ዓመጸኛው የዚህ ዓለም ህዝብ ሳይሆን የብዙኃኑ ብዙኃን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ብዙኃን ነን ብለው በዙሪያችን የሚጮሁትን የሞትን ድምጾች በአንድ ቃል የሚሽር የሊባኖሱን ዝግባ የሚሰብርና ምድረ በዳውን የሚያናውጥ ድምጽ ያለው የድል ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ስለዚህ የከበበ ሁሉ የሚጮህብን ሁሉ ሞትን የሚያውጅብን ሁሉ አያስፈራንም፡፡ በኛ ብርታት ሳይሆን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን፡፡  የተከበብነው ብቻችንን ብንሆን እንፈራ እንደነግጥ ነበር፡፡ ነገር ግን የተከበብነው ከርሱ ጋር ነው፡፡ እርሱ ከከበቡንና ሊወግሩን ድንጋይ ካነሱት ጋር ሳይሆን ከኛ ጋር ነው፡፡ “በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም፤ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፥ ነበልባሉም አይፈጅህም።” ብሎናልና በቃሉ መርከብ ውስጥ ሆነን ይህንን ሁሉ እንሻገራለን፡፡  ዓለምን የሚያሸንፈው በርሱ ላይ ያለን እምነት ነው፡፡ አሸንፎ አሸናፊዎች አድርጎናልና፡፡ ስለዚህ አሸነፈ ማሸነፋችንን ድል ነሳ ስንል ድል መንሳታችንን እያወጅን ነው፡፡  በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሳቱ ለሚያዞረን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *