They came to show Him the beauty of the Temple and then ..የተማረኩበትን ሊያሳዩት ሲመጡ ሊሆን ያለውን አሳያቸው፡፡

የኛን ከምናሳየው የርሱን ያሳየን

“ኢየሱስም ከመቅደስ ወጥቶ ሄደ፥ ደቀ መዛሙርቱም የመቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ቀረቡ።እርሱ ግን መልሶ፦ ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው።” የማቴዎስ ወንጌል 24:1-2

በመምህር ጸጋ

ደብረ ዘይት የኛን ውበት የምናሳይበት ሳይሆን የርሱን ውበት የምናይበት ከፍታ

ውበትና ደም ግባት የሌለው ሆኖ ወደ ተዋበችው ከተማ የመጣው ጌታ፡፡

የዘለዓለም አምላክ የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰው ልጅ ፍቅር ተጎትቶ ከሰማየ ሰማያት በወረደበትና ራሱን አዋርዶ በዚህች ምድር በሚመላለስበት ጊዜ ኢየሩሳሌም ግን አሸብርቃ ነበር፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ የእግዚአብሔር ክንድ የሆነው ጌታችንና መድኃኒታችን እኛን ለማዳን ራሱን ባዶ አድርጎ የሚገለጥበትን ሁኔታ ብዙ ዘመናት ቀድም ብሎ እንዲህ ብሎ ተናግሮአል፡፡

“የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጦአል?

በፊቱ እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል፤ መልክና ውበት የለውም፥ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም።

የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፤ ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፥ እኛም አላከበርነውም።

ለነርሱ ወደ ገሊላ ባህር፤ ወደ ጥብርያዶስ ባህር፤ ወደ ቢታንያ መንደር፤ ወደ ሳምራዊያን ከተማ መሄድ ውርደት ነው ስለዚህ አያደርጉትም፡፡ እነርሱ ከመቅደሱ በጣም ቀርበው ወዳሉት መንደሮች መውረድ አቃታቸው እርሱ ግን በአእላፍ መላእክት፤ በሃያ አራቱ ሽማግሌዎች፤ በአራቱ እንስሳት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እየተባለ ቀንና ሌሊት ሲመሰገንበት ከሚኖረው የዘላለም ክብሩ ወርዶ ወደኛ መጣ፡፡ የሰማይ አምላክ በምድር ያሉ አገልጋዮቹን ቀደማቸው፡፡

በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው።”  ትንቢተ ኢሳይያስ 53፡1-4

ይህ ትንቢት የሚፈጸምበት ዘመን ሲደርስም ጌታችንና መድኃኒታችን እንደ ትንቢቱ ቃል በሰው ሲታሰብ ሊታመን በማይችል ሁኔታ ራሱን ዝቅ አድርጎ በቤተ ልሔም ከተማ በበረት ተወለደ በድሆች መንደር በናዝሬትም አደገ፡፡ ከደረቅ መሬት እንደ ሥር ያደገው ማለትም ያለ ዘርዐ ብእሲ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ጌታችንና መድኃኒታችን የወደቀውንና ኃጢአተኛውን የሰውን ልጅ ዓይን እንኳ የሚስብ ውበት የሌለው ሆኖ ተገለጠ፡፡ ባየነው ጊዜ እንወደው ዘንድ ደም ግባት የለውም፡ የተናቀ ከሰውም የተጠላ ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት ማለትም ይህንንስ አላየውም ብሎ ፊቱን የሚዞርበት ሆኖ ተገለጠ፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን በዚህ መጠን በሆነ መዋረድ ከሰውም አንሶ የባሪያን መልክ ይዞ ሲገለጥ በዘመኑ የነበሩት የሃይማኖት መምህራንና ቀሳውስት የመቅደሱም ካህናት ግን እዩኝ እዩኝ የሚል ግርማ የሚሰጣቸውን ዘርፋፋ ቀሚስና የተለያዩ የሃይማኖት ስሞች ይዘው በህዝቡ መካከል ይመላለሱ ነበር፡፡ በገበያና በመቅደስ መምህር ሆይ መምህር ሆይ መባልን ይወዱ ይባሉም ነበር፡፡ እነርሱን ለማየትና ለማግኘት ህዝቡ ወደ መቅደሱ ሲሄድ የቻለ ሲያገኛቸው ያልቻለም ባለማግኘቱ ሲያዝን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በመንደሮች እና አሳ በሚያጠምዱባቸው የባህር ዳርቻዎች ይመላለስ ነበር፡፡ ካህናቱን ለማግኘት እድል የሌላቸው ድሆችና መበለቶች አሳ አጥማጆችና ቀራጮች ኢየሱስ ክርስቶስን ግን በግላጭ ማግኘት ይችሉ ነበር፡፡ የቀራጮች ዋና የሆነ ዘኬዎስ ኢየሱስ ክርስቶስን በርቀት ዛፍ ላይ ሆኖ ለማየት ሲሞክር ትሁቱ ጌታ ግን ና ውረድ እኔ ራሴ ወደ ቤትህ እገባለሁ ብሎ ከርሱ ጋር ሊውል ገባ፡፡ ክብራቸውን ያለ ልክ የሚጠብቁትን የሃይማኖት መሪዎችን የማግኘት እድል የሌለው ድሃ ህዝብ የሰማይን አምላክ ግን ራሱን ዝቅ አድርጎ ወዳለበት ዝቅታ መጥቶለታልና በግላጭ አገኘው፡፡ ካህናቱ ፈሪሳውያኑ እነርሱ የናቁትን ህዝብ እርሱ ሄዶ ሲያገኘውና ሲያገለግለው የኃጢአተኞች ወዳጅ ብለው ሰየሙት፡፡ ኦ ይህ ስም እንዴት ደስ ይላል፡፡ እርሱ የኃጢአተኞች ወዳጅ ባይሆን ኖሮማ የኛ መጨረሻ ምን ይሆን ነበር? የፍቅር ጌታ ራሱን አዋርዶ የኃጢአተኞች ወዳጅ ሆኖ በፍቅር እጆቹ ስለዳሰሰን እኮ ነው ዛሬ ክርስትያኖች የእግዚአብሔር ልጆች የሆነው፡፡ ያሸበረቀው መቅደስ ሳያድነን በመቅደሱ የሚካሄደው ሃይማኖታዊ ስርዓት ከኃጢአት ቀንበር ሳያወጣን የመቅደሱ ካህናት ወደኛ መቅረብ ተጸይፈው ህይወታችንን እና ኑሮአችን በመቅደሱ ማማ በክብር ስፍራቸው ሆነው አሻግረው እየተመለከቱ ሲፈርዱብን እርስ ግን እኛ ወዳለንበት መንደር መጣ፡፡ እርሱ ቅዱስ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ደቀመዛሙርት ያገኛቸው ወደ መቅደሱ መጥተው ሳይሆን እርሱ አሳ ወደሚያጠምዱበት ወደዚያ አሳ አሳ ወደሚሸተው የገሊላ ባህር ዳርቻ መጥቶ ነው፡፡ ቀራጩን ሌዊን ያገኘው ሌዊ ወደ መቅደሱ መጥቶ ሳይሆን እርሱ ወደ መቅረጫው ስፍራ ሄዶ ነው፡፡ በዘመኑ የነበሩት የመቅደሱ አገልጋዮችና ካህናት ከሃዲው ሄሮድስ አንቆጥቁጦ በሰራላቸው መቅደስ ተቀምጠው ነበር፡፡  ለነርሱ ወደ ገሊላ ባህር፤ ወደ ጥብርያዶስ ባህር፤ ወደ ቢታንያ መንደር፤ ወደ ሳምራዊያን ከተማ መሄድ ውርደት ነው ስለዚህ አያደርጉትም፡፡ እነርሱ ከመቅደሱ በጣም ቀርበው ወዳሉት መንደሮች መውረድ አቃታቸው እርሱ ግን በአእላፍ መላእክት፤ በሃያ አራቱ ሽማግሌዎች፤ በአራቱ እንስሳት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እየተባለ ቀንና ሌሊት ሲመሰገንበት ከሚኖረው የዘላለም ክብሩ ወርዶ ወደኛ መጣ፡፡ የሰማይ አምላክ በምድር ያሉ አገልጋዮቹን ቀደማቸው፡፡

የአባት ፍቅር

ከዚህ በታች ያለውን የወንጌል ድምጽ እንዲሰሙ በታላቅ ፍቅር እንጋብዝዎታለን፡፡

በዚህን ጊዜ ኢየሩሳሌም ደማቅ ከተማ ነበረች፡፡ በሮማ መንግሥት ስር በመሆንዋ ምክንያት ብዙ ፖለቲካዊ ጥቅማ ጥቅሞችን የምታገኝ ከዓለም ዙሪያ ብዙ ሰዎች የሚጎበኝዋት የሃይማኖትና የንግድ ማዕከል የሆነች ደማቅ ከተማ ነበረች፡፡ ንጉሱ ሄሮድስ በካህናት አለቆቹ በኩል ህዝቡን ለመግዛት እንዲያመቸው አርባ ስድስት ዓመት የፈጀ ታላቅና ውብ መቅደስ አሰርቶላቸው ነበር፡፡ መቅደሱ ከዚያም ቀደም ብሎ ከባቢሎን ምርኮ በኋላ ውብ ሆኖ ተሰርቶ ነበር፡፡  ሄሮዶቱስ የተባለው ታሪክ ጸሐፊ ስለዚህ መቅደስ ሲናገር ከሩቅ ሲያዩት የበረዶ ክምር የሚመስል እጅግ ነጭ እና የሚስብ ነበረ ይለናል፡፡ እንግዲህ ይህች በእንደዚህ ዓይነት ውበት አሸብርቃ የሰዎችን ሁሉ ዓይን ትማርክ የነበረች ከተማ ራሱን አዋርዶ የሰው ልጆችን ለማዳን ከሰማየ ሰማያት የወረደውን ጌታ ውስጣዊ ውበት ልታይ አልቻለችም፡፡ የሰዎች ሁሉ ዓይን በምድራዊ ክብር፤ በመቅደሱ ውበት፤ በሃይማኖት ስርዐቱና በካህናቱ ውበት ተይዞ ነበርና ቅዱሱን ጌታ ሊቀበሉት አልቻሉም፡፡ ስለዚህ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተማይቱን አየና እንዲህ ብሎ አለቀሰላት፡፡ 

“ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት፥ እንዲህ እያለ፦ ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል። ወራት ይመጣብሻልና፥ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤ አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፥ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፥ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና።” የቅዱስ ሉቃስ ወንጌል 19፤41-44

የህዝቡና የካህናቱ ብቻ ሳይሆን የደቀመዛሙርቱም ዓይኖች በመቅደሱ ውበት ተማርከው ነበር፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን እነርሱ የሚያዩትን ውጫዊ ውበት ሳይሆን በውስጡ ያለውን የረከሰ ነገር በመመልከት ያ ሁሉ ውበት ከፍርድ እንደማያድናቸው፤ በሰው ፊት የተዋቡ ቢሆኑም በእግዚአብሔር ፊት ግን የተለሰኑ መቃብሮች መሆናቸውን ይነግራቸው ጀመር፡፡ 

በሙሴ ወንበር ላይ የተቀመጡት ጸሐፍትና ፈሪሳውያን በርሱ ዓይን ምን እንደሚመስሉ ሲናገር 

“በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሎ ነገራቸው ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል።

ስለዚህ ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም፥ ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ።

ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፥ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም።

ለሰውም እንዲታዩ ሥራቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ስለዚህ አሽንክታባቸውን ያሰፋሉ ዘርፉንም ያስረዝማሉ፥

በምሳም የከበሬታ ስፍራ፥ በምኵራብም የከበሬታ ወንበር፥

በገበያም ሰላምታና፦ መምህር ሆይ መምህር ሆይ ተብለው እንዲጠሩ ይወዳሉ።

የቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል 23፤1-7

ደቀ መዛሙርቱ የነርሱን ፈለግ እንዳይከተሉ ከመከረ በኋላም ስለጻፎቹንስ ፈሪሳውያኑ እንዲህ በማለት ቀጠለ

“እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ፥ ወዮላችሁ እናንተ አትገቡም የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ።

እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በጸሎት ርዝመት እያመካኛችሁ የመበለቶችን ቤት ስለምትበሉ፥ ወዮላችሁ፤ ስለዚህ የባሰ ፍርድ ትቀበላላችሁ።

እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ አንድ ሰው ልታሳምኑ በባሕርና በደረቅ ስለምትዞሩ፥ በሆነም ጊዜ ከእናንተ ይልቅ ሁለት እጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት፥ ወዮላችሁ።

እናንተ፦ ማንም በቤተ መቅደስ የሚምል ምንም የለበትም፤ ማንም በቤተ መቅደስ ወርቅ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል የምትሉ፥ ዕውሮች መሪዎች፥ ወዮላችሁ።

እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፥ ማናቸው ይበልጣል? ወርቁ ነውን? ወይስ ወርቁን የቀደሰው ቤተ መቅደስ?

ደግማችሁም፦ ማንም በመሠዊያው የሚምል ምንም የለበትም፤ ማንም በላዩ ባለው መባ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል ትላላችሁ።

እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፥ ማናቸው ይበልጣል? መባው ነውን? ወይስ መባውን የሚቀድሰው መሠዊያው?

እንግዲህ በመሠዊያው የሚምለው በእርሱና በእርሱ ላይ ባለው ሁሉ ይምላል፤

በቤተ መቅደስም የሚምለው በእርሱና በእርሱ በሚኖረው ይምላል፤

በሰማይም የሚምለው በእግዚአብሔር ዙፋንና በእርሱ ላይ በተቀመጠው ይምላል።

እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ፥ ወዮላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር። እናንተ ዕውሮች መሪዎች፥ ትንኝን የምታጠሩ ግመልንም የምትውጡ።

እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ስለምታጠሩ፥ ወዮላችሁ። አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፥ ውጭው ደግሞ ጥሩ እንዲሆን አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጡን አጥራ።

እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጡ ግን የሙታን አጥንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ።

እንዲሁ እናንተ ደግሞ በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን ትታያላችሁ፥ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ዓመፀኝነት ሞልቶባችኋል።

እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ የጻድቃንንም መቃብር ስለምታስጌጡና፦

በአባቶቻችን ዘመን ኖረን በሆነስ በነቢያት ደም ባልተባበርናቸውም ነበር ስለምትሉ፥ ወዮላችሁ።

እንግዲያስ የነቢያት ገዳዮች ልጆች እንደሆናችሁ በራሳችሁ ላይ ትመሰክራላችሁ።

እናንተ ደግሞ የአባቶቻችሁን መስፈሪያ ሙሉ።

እናንተ እባቦች፥ የእፉኝት ልጆች፥ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?

ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤

ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ።

እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል።

የቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል 23፤13 -36 

እንግዲህ ያ ሁሉ የሃይማኖት ውበት ያ ሁሉ ውጫዊ ክብር በእግዚአብሔር ፊት ሲታይና ሲመዘን እንደዚህ የረከሰና የተዋረደ ነበር፡፡  

ጌታችንና መድኃኒታችን ይህንን ተናግሮ ከጨረሸ በኋላ እንዲህ በማለት ንግግሩን ሲደመድም 

“ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም።

እነሆ፥ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል።

እላችኋለሁና፥ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም።”  በማለት ለከተማይቱ አለቀሰ፡፡ ማቴ 23፤37-38

ከዚህ በኋላ ነበር በዛሬው ዕለት ደብረ ዘይትን ለመዘከርና ነገረ ምጽአቱን ለማሰብ የምንናንበውን ስለ መጨረሻው ዘመን የተናገረውን ቃል ለደቀ መዛሙርቱ ያስተማራቸው፡፡ ትምህርቱን እንዲያስተምራቸው መነሻ የሆነውም የነርሱ የራሳቸው ጥያቄ ነበር፡፡ 

ሊያሳዩት የቀረቡትን እርሱ አሳያቸው፡፡

ይህንን ተናግሮ ከመቅደሱ ወጥቶ በሚሄድበት ጊዜ  ደቀመዛሙርቱ የመቅደሱን ድንጋዮች ውበት ሊያሳዩት ቀረቡ፡፡ 

 “ኢየሱስም ከመቅደስ ወጥቶ ሄደ፥ ደቀ መዛሙርቱም የመቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ቀረቡ።”የማቴዎስ ወንጌል 24፤1 

ኢየሱስ ክርስቶስ  ከመቅደሱ ወጥቶ ሲሄድ እንደነርሱ በመቅደሱ ውበት አለመማረኩን ያዩት ደቀ መዛሙርትም በደንብ አስተውሎ አላየው ይሆናል ብለው ነበር ይህንን ጥያቄ ያቀረቡለት፡፡

የእግዚአብሔርን ውበት ክርስቶስን የድንጋዮችን ውበት ሊያሳዩት ቀረቡ፡፡ የውበት ሁሉ ፍጻሜ የሆነውን ክርስቶስን ሌላ ውብ ነገር ሊያሳዩት ሞከሩ፡፡ ከንግግራቸው እንደምናስተውለው እነርሱም እንደሌሎቹ በመቅደሱ ድንጋዮች ውበት እጅግ ተማርከው ነበር፡፡ እርሱ ግን እነርሱ እንዲያይ የጠየቁትን ትቶ እርሱ እንዲያዩ የሚፈልገውን እንዲህ በማለት ያሳያቸው ጀመር፡፡ 

“እርሱ ግን መልሶ፦ ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው።

እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፦ ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት።

ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ።

ብዙዎች፦ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ።

ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው።

ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፥ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤

እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።

በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፥ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።

በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፤

ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ፤

ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።” የቅዱስ ማቴዎ ወንጌል 24፤2-13

አዎ ሄሮድስ የሠራላቸው አርባ ስድስት ዓመት የፈጀው ያ የሚመኩበት መቅደስ ከሚመጣው ፍርድ አያድናችው፡፡ ከምንም የማያድን ምድራዊና ውጫዊ የሆነ ሃይማኖታዊ ውበት ነው የነበራቸው፡፡ ዓርባ ስድስት ዓመት ፈጅቶ የተሰራው አንጸባራቂ መቅደስም ሆነ በሰዎች ፊት የሚከበሩበት ካባና ስም በእግዚአብሔር ፊት የተዋረደ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሲያያቸው ምንም ክብር የሌላቸው አስመሳዮችና በውጭ ብቻ አምረው የሚታዩ የተለሰኑ መቃብሮች ነበሩ፡፡ በዚያ በሚታየው ውጫዊ እና ሃይማኖታዊ ብልጭልጭታ እየተታለሉ ሊያድናቸው ራሱን አዋርዶ የመጣው ጌታ ገፉት፡፡ 

በመሆኑም ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም። እነሆ፥ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል በማለት በፍቅር አነባላቸው፡፡

በዚህ ትምህርቱም በመቅደሱ ውበት የተማረከውን የደቀመዛሙርቱን ልቡናና ዓይን ወደ ትክክለኛው እይታ መለሰው፡፡ አሁን ለጊዜው አምሮ የሚታየውን፤ አሁን ሰዎች የሚመኩበትን ውጫዊ የሃይማኖት ስርዓት ትተው ከፍርድና ከሞት የሚያድናቸውን ጌታ እንዲያዩ በቃሉ አስተማራቸው፡፡ በሰው ዓይን ሲታይ ሁሉ ነገር መልካም ቢመስልም፤ ነገ መልካም ይሆናል የሚል የሃይማኖት መሪዎችና የፖለቲከኞች ከንቱ ተስፋ ቢኖርም ዓለምን በእጁ የያዘው ጌታ ግን በእርግጥ ሊሆን ያለውን እውነት አሳያቸው፡፡

የመቅደስ ውበትና የሃይማኖት ስርአት ሰውን ከፍርድ አያድነውም፡፡ ሰውን ከፍርድ የሚያድነው በንሥሐ ወደ እግዚአብሔር መመለሱና በክርስቶስ አምኖ እውነተኛ ክርስቲያን መሆኑ ብቻ ነው፡፡  

እጅግ የሚያሳዝነው ዛሬም ከደቀ መዛሙርቱ ሳንማር  እርሱ የሚያሳየንን ማየት ትተን የኛ የሆነውን ለርሱ ለማሳየት ጥረታችንን መቀጠላችን ነው፡፡ እኛ ውብ የምንለውን ሁሉ ለማሳየት ስንጥር እርሱ እንድናይለት የሚፈልገውን ማየት አቅቶናል፡፡ ፍርድ ከደጅ ቀርቦ እያለ እኛ ብዙ ነገር ለርሱ ለማሳየት እንገነባለን፡

ወንድሞቼና እህቶቼ ዛሬስ እናንተ ውብ የምትሉትን ልታሳዩት እየሞከራችሁ ነው ወይስ እርሱ የሚያሳያችሁን እያያችሁ ይሆን? እናንተ ለርሱ ሠራንለት የምትሉትን ውብ ነገር እንዲመርቅላችሁ እየጠራችሁት ነው ወይስ እርሱ የሚላችሁን እያደረጋችሁ ነው? ዛሬ ደብረ ዘይት ሲታሰብ ይህ ቃል የሚታሰብበት ቀን ነው፡፡ እንግዲህ ዓይኑ ለተከፈተ ደብረ ዘይት ማለት ይህ ነው፤፡ ደብረ ዘይት ማለት የሰውና የሃይማኖት  ውበት በእግዚአብሔር ብርሃን የተፈተሸበትና የተጋለጠበት፤ የደቀ መዛሙርቱ ዓይን ከሚማርከው የመቅደሱ ድንጋይ ወደ ክርስቶስ ዘወር ያለበት ቀን ነው፡፡ እነርሱ ጊዜአዊውን ሰው ሰራሽ የሆነው ውጫዊ የሆነውን ውበት ሊያሳዩት ሲቀርቡ እርሱ ግን እውነተኛውን ነገር አሳያቸው፡፡ ፍርድ ሊመጣ እንደሆነ፤ ዘመን ሊፈጸም እንደሆነ፤ የሰው ልጅ የሰራውና የሚመካበት  ነገር ሁሉ የሚፈርስበት ጊዜ እንደቀረበ አስተማራቸው፡፡ 

ወንድሞቼና እህቶቼ እነዚህ ጌታችንና መድኃኒታችን ለደቀ መዛሙርቱ የተናገራቸው ህያው ቃላት ከነርሱ ዘመን ይልቅ በኛ ዘመን በሙላት እየተፈጸሙ ነው፡፡ ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፥ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። የተባለው ቃል ይኸው እለት እለት በዐይናችን ፊት ሲፈጸም እያየነው ነው፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነ እያየን ግን አሁንም ብዙዎቻችን በሃይማኖታችን፤ በሥርኣታችን እንመካለን፡፡ እየተጋደልን እየተጠላላን ነገር ግን ባማሩ መቅደሶቻችን ሃያማኖታዊ ስርዐት እናደርሳለን፡፡ የገነባነው ነገር ሁሉ በኛ ላይ ሊናድ እየተደረመሰም ሃይማኖታዊ ወጋችንን ይዘን ቀጥለናል፡፡ ብዙ ህዝብ ክርስቲያን ነኝ ሃይማኖት አለኝ ይላል ነገር ግን የህይወት ለውጥ የለም፡፡ ፍቅር የሌለበት  የመቅደስ ውበት፤ ህይወት የሌለበት የውጭ ማማር፤ አንድነት የሌለበት የሃይማኖት ወግ  ገዝፎና በዝቶ የሚታይበት ዘመን ላይ ነን፡፡

ፈርሶ ከሚቀብራችሁ ውበቱ ከማያድናችሁ፤ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ ከማይቀረው እናንነት ለክብራችሁ ከገነባችሁት ማንኛውም የሃይማኖት ወግና ሥርአት ወጥታችሁ ኢየሱስ ክርስቶስን በህይወታችሁ እንዲነግሥ ፍቀዱ፡፡ የትኛውም ሰው ሰራሽ ሃይማኖታዊ ወግና ስርዓት፤ የትኛውም ውጫዊ ካባና ውበት፤ የትኛውም ሃብትና ባለጸግነት ከፍርድ አያድነንም፡፡ እየሆነ ካለውና ከሚመጣው ፍርድ የሚያድነን ራሱን በመስቀል ላይ ስለሁላችንም አሳልፎ የሰጠው መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ነው፡፡

እግዚአብሔር እርሱ የሚይሳየንን እንድናይ ዓይኖቻችንን ይክፈትልን፡፡ 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *