ማንም የማይወስድብን ዕድል

ማንም የማይወስድብን ዕድል

“ኢየሱስም መልሶ፦ ማርታ፥ ማርታ፥ በብዙ ነገር ትጨነቂአለሽ ትታወኪማለሽ፥42 የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፤ ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም አላት። ሉቃ.10:41-42.”

ብዙ ጊዜ ዘመናችንን ሁሉ ስናሳድድ የምንኖረው የሚጠፋውን ነገር ዛሬ አግኝተን ነገ የምናጣውን ነገር ነው። በተለይ የሰው ልጆች በእጅጉ ሲፈልጉት ቀንና ሌሊት ሲመኙትና ሲፈልጉት የሚኖሩት ዓለም አቀፍ ምኞት በመጽሐፍ ቅዱስ ስሙ ማሞን {የገንዘብ አምላክ} የተባለውን ገንዘብን ነው። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሁለት ጌቶች መገዛት አይቻላችሁም ብሎ ሲያስተምር ገንዘብ የእግዚአብሔርን ጌትነት የሚገዳደር ከባድ ፈተና እንደሆነ ነግሮናል። ነገር ግን ገንዘብን ብናገኘውም እንኳ ይወሰዳል ይጠፋል። ዘላቂና እውነተኛ እርካታና ዋስትና ሊሰጠን አይችልም። እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ እንደነፋስ በኖ የሚጠፋውንና ህይወት የሌለውን ነገር ለማግኘትና በገንዘብ ደስታንና እርካታን ለማግኘት የሚደረገው ሩጫ እጅግ ያስገርማል። እንደዚሁም የሰው ልጆች ክብርን ስምን ዝናን ሀብትን ውበትን  ስልጣንን ለማግኘት ይኳትናሉ። ይህ ሁሉ ግን ገና ጨበጥነው ብለን ሳንጨርስ በኖ የሚጠፋ ጊዜአዊ ነገር ነው። ሌላው ሁሉ ይቅርና ይህን ሁሉ በማግኘት ደስታን አገኛለሁ ብሎ ቀንና ሌሊት የሚኳትነው ህይወታችንም እንኳ ጠዋት ታይቶ ጸሐይ ስትወጣ እንደሚጠፋው ጤዛ ጊዜአዊ ነው። ምድራዊው ህይወታችን የሚያልፍና ጊዜአዊ  ነው። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ያገኘውን ሀብትና ክብር ስምና ዝና የሰራውን ቤተ መንግስትና ያሉትን ባሮች ሁሉ ከዘረዘረ በኋላ ሁሉ ከፀሐይ በታች የተሠራውን ሥራ ሁሉ አየሁ፤ እነሆም፥ ሁሉ ከንቱ ነው፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነው ነበር ያለው። ማንኛውም ነገር የሚወሰድና ጊዜአዊ እስከሆነ ድረስ መልካም ዕድል አይደለም። ጌታችንንና መድኃኒታችን ስለዚያ እርሻው ፍሬአማ ስለሆነችለት ባለጸጋ እንዲህ ብሎ ተናገረ

የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፥ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ አላቸው። ምሳሌም ነገራቸው እንዲህ ሲል፦ አንድ ባለ ጠጋ ሰው እርሻ እጅግ ፍሬያም ሆነችለት። እርሱም፦ ፍሬዬን የማከማችበት ስፍራ አጥቻለሁና ምን ላድርግ? ብሎ በልቡ አሰበ። እንዲህ አደርጋለሁ፤ ጐተራዬን አፍርሼ ሌላ የሚበልጥ እሠራለሁ፥ በዚያም ፍሬዬንና በረከቴን ሁሉ አከማቻለሁ፤ ነፍሴንም፦ አንቺ ነፍሴ፥ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ፥ ብዪ፥ ጠጪ፥ ደስ ይበልሽ እላታለሁ አለ። እግዚአብሔር ግን፦ አንተ ሰነፍ፥ በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል፤ ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል? አለው። ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፥ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው። ሉቃ.12፤15-22

ይህ ሰው የምትወሰድ ነፍስ ይዞ ይህችን ነፍሱን ለማስደሰት ጎተራውን ያሰፋ ነበር። ጎተራውን ሲሞላም አንቺ ነፍሴ፥ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ፥ ብዪ፥ ጠጪ፥ ደስ ይበልሽ እላታለሁ አለ። ነገር ግን አንድ ድምጽ ከሰማይ ተሰማ ይህችን ለብዙ ዘመን የሚበቃ በረከት አከማችቸልሻለሁና ደስ ይበልሽ የተባለችው ነፍስ በዚህች ሌሊት ልትወሰድ ነው ተባለች። ለራስዋ ብዙ ዘመን አትኖርም ነገር ግን ለብዙ ዘመን የሚኖር ሀብት አከማችታለች። ስንት ነገር ነው ለማንኖርበት ዘመን የምናከማቸው? ለብዙ ዘመን ለማትኖር ነፍስ ለብዙ ዘመን የሚቀር ሀብት ተከማቸላት። ይህች ነፍስ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ባለጠጋ ያልሆነች ነበረች።

ስለዚህ በምድር ላይ ተወዳጅነትን ክብርን ሀብትን ብልጽግናን ብናገኝም እንኳ በኖ የሚጠፋና ከኛ የሚወሰድ ነው። ማርያም ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ባለጠጋ የሚያደርጋትን ማንም የማይወስድባትን ዕድል መረጠች። ኦ ማንም የማይወስደውን በዚህች ሌሊት ካንተ ይወሰዳል የማይባልን ብልጽግና መያዝ እንዴት መታደል ነው። ወንድሞቼ እህቶቼ በውበታችሁ ትመካላችሁን? ይወሰዳል፡ በጉልበታችሁ በጤናችሁ ትመካላችሁን? ይወሰዳል። በገንዘባችሁ በሀብታችሁ ትመካላችሁን? ይወሰዳል። አንድ ግን ማንም የማይወስደው መልካም ዕድል አለ  ማንም የማይወስደው ከእግዚአብሔር የተሰጠን የማይወሰድብን ዕድልና ሀብት የክብር ጌታ ጌታችንንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ የዘላለም ዕድላችን የዘላለም ሀብታችን የዘላለም ክብራችን የዘላለም ህይወታችን የዘላለም ቤታችን ነው።

ጉም መጨበጥን ትታችሁ እንደ ማርያም ከእናንተ የማይወሰደውን ዕድል ምረጡ። ይህን መልካም ዕድል ትመርጡ ዘንድ መልካሙ ዕድል ክርስቶስ ኢየሱስ ያግዛችሁ።

በክርስቶስ ወንድማችሁ መምህር ጸጋ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *