በመምህር ጸጋ
አቢ ፒሬ የተባለው ፈረንሳዊ ቄስ በ1947 በፓሪስ በነበረው በጣም ቀዝቃዛ ብርድ መጠጊያ አጥተው መንገድ ላይ በብርድ ሊሞቱ ትንሽ የቀራቸውን ሰዎች ከህጻናት ልጆቻቸው ጋር ወደ ቤቱ ወሰዳቸው፡፡ ነገር ግን ቤቱ ጠባብ ነበረችና ሁሉንም መያዝ አልቻለችም፡፡ በዚህን ጊዜ ወደ ህንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ሄደና በመቅደሱ ያለውን ንዋየ ቅዱሳት ሁሉ አውጥቶ ቀዝቃዛው ኮርኒስ ውስጥ አደረገው፡፡ ከዚያም የቀሩትን ሰዎች አስገብቶ አስተኛቸው፡፡ ይህንን ያዩ ሌሎች ቀሳውስት እንዴ ቄስ አቢ ምን እያደረክ እንደሆነ ይገባሃል? የተቀደሰውን ቦታ እኮ እያረከስከው ነው፡፡ የተቀደሱትንም እቃዎች ብርድ ላይ ጣልካቸው አሉት፡፡ በዚህን ጊዜ መለስ አለና “በነዚህ ህጻናት አካል ውስጥ ያለው ክርስቶስ እንጂ በነዚህ ቅዱስ እቃዎች ያለው ክርስቶስ አይበርደውም” አላቸው፡፡
እንዴት የሚገርም ብርሃን ነው? ክርስቶስን አወቅነው አየነው ወደድነው ማለት የምንችለው በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ውስጥ ስናየው ስናውቀውና ስንወደው ብቻ ነው፡፡ ብዙ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያውቁት ከወንድሞቻቸውና ከእህቶቻቸው ውጭ ነው፡፡ ስለዚህ ሲርበው አይመግቡትም ሲታረዝ አያለብሱትም ሲጠማ አያጠጡትም ሲታሰር አይጎበኙትም፡፡ እነርሱ የሚያውቁት ክርስቶስ አሁን አይርበውማ አይጠማውማ አይታሰርማ አይራቆትማ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚራበው የሚጠማው የሚራቆተውና የሚታሰረበው በወንድሞችና በእህቶቻችን ውስጥ ሆኖ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ በወንድሞቻችን እና በእህቶቻችን ውስጥ ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ካላወቅነው ስለርሱ ያለን እውቀት የተሳሳተ ነው፡፡
“በነዚህ ህጻናት አካል ውስጥ ያለው ክርስቶስ እንጂ በነዚህ ቅዱስ እቃዎች ያለው ክርስቶስ አይበርደውም” ቄስ አቢ ፒሬ
“የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፥ በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል። ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፦ እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና። ጻድቃንም መልሰው ይሉታል፦ ጌታ ሆይ፥ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህስ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህስ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ አይተን መቼ ወደ አንተ መጣን? ንጉሡም መልሶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል።በዚያን ጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል፦ እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ። ተርቤ አላበላችሁኝምና፥ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፥ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፥ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፥ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና። እነርሱ ደግሞ ይመልሱና፦ ጌታ ሆይ፥ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን አላገለገልንህም? ይሉታል። ያን ጊዜ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም ብሎ ይመልስላቸዋል።” የማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 25፤31-45
ለካ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ቅርብ ነው፡፡ በኛና በርሱ መካከል ያለው ርቀት በኛና በወንድምና በእህቶቻችን መካከል ያለውን ርቀት ያክላል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን በወንድሞቻችን በኩል ልናበላው ልናጠጣው እንችላለን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም በቤተልሄም ከተማ በተወለደ ጊዜ ተቀባይ ያጣውና በበረት የተወለደው እኮ እንግዳ ሆኖ ስለመጣ ነው፡፡ እግዚአብሔርን እንደ እንግዳ የሚቀበል ህዝብ ቢሆን ኖሮ ይቀበለው ነበር፡፡ እነርሱ ግ ን እግዚኣብሔርን የሚያውቁትና የሚጠብቁት በወርቅ ባሸበረቀው መቅደስ እንጂ በቤተ ልሄም በረት አልነበረምና ሳያውቁት ሳይቀበሉት ቀሩ፡፡ ዛሬስ እግዚአብሔርን እንዴት ነው የምናውቀው? እንዴትስ ነው የምንቀበለው? ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተናገራቸው ምሳሌዎች አንዱ በሆነው በደጉ ሳምራዊ ታሪክ ላይ የምናየው ይህንን ነው፡፡ ታሪኩ እንዲህ ይላል፡
“ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፦ አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት ደበደቡትም በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ።ድንገትም አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ አይቶትም ገለል ብሎ አለፈ።እንዲሁም ደግሞ አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ።አንድ ሳምራዊ ግን ሲሄድ ወደ እርሱ መጣ አይቶትም አዘነለት፥ቀርቦም ዘይትና የወይን ጠጅ በቍስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው፥ በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደርያ ወሰደው ጠበቀውም።በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለባለቤቱ ሰጠና፦ ጠብቀው፥ ከዚህም በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ አለው።እንግዲህ ከነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሃል?እርሱም፦ ምሕረት ያደረገለት አለ። ኢየሱስም፦ ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ አለው።” የቅዱስ ሉቃስ ወንጌል 10፤30-37
ለመሆኑ ካህኑና ሌዋዊ ተደብድቦ የወደቀውን ሰው ትተው ወዴት ነበር የሚሄዱት? ወደ አገልግሎት ነዋ! ወደ መቅደሱ እግዚአብሔርን ወደሚያገለግሉበት ስፍራ ሲታጠዱ በመንገድ የወደቀውን በሞት አፋፍ ያለውን ሰው በደም ተለውሶ እያዩት ትተውት ሄዱ፡፡ እንዲህ ዓይነት ቄስ እንዲህ ዓይነት ጳጳስ እንዲህ ዓይነት ዲያቆን እንዲህ ዓይነት ምእመን ከመሆን እግዚአብሔር ያድነን፡፡ ለአገልግሎት ብሎ የወደቁትን አልፎ ከመሄድ ይጠብቀን፡፡ እግዚአብሔር ምን እንደሚፈልግ ምንስ ዓይነት አገልግሎት እንደሚያስደስተው በዚህ ምሳሌ አሳይቶናል፡፡ ይኸውም የወደቁትን በሞት አፋፍ ያሉትን ማዳን ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚራበው በሚራቡት ውስጥ ሆኖ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚራቆተው በሚራቆቱት ውስጥ ሆኖ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚጠማው በሚጠሙት ውስጥ ሆኖ ነው፡፡ እውነተኛ ክርስትና ይህ ነው፡፡ እግዚአብሔር በመልኩ የፈጠረውንና አንድ ልጁን በመስቀል ላይ አሳልፎ የሰጠለትን ሰውን ማዕከል ያላደረገ አገልግሎት ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ዓይኖች በሰው ላይ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር የወደደውና አንድ ልጁን አሳልፎ የሰጠው ለሰው ነው፡፡ ወንድሞቼና እህቶቼ እናንተስ ልባችሁ በሰው ላይ ነው ወይስ ከሰው የሚበልጥባችሁ አገልግሎት አለ? ዓይኖቻችሁ በሰው ላይ ናቸው ወይስ በነጣው ሰማይ ላይ? እውነተኛውን ወንጌል እንድናውቅና የኢየሱስ ክርስቶስን ፍለጋ እንድንከተል እግዚአብሔር የሁላችንንም ልቡና ይክፈትልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡
እባክዎትን ለሌሎችም ሼር ያድርጉት፡፡
በሥላሴ ማኅበር የሚሰጠውን የእግዚአብሔር ቃል ትምህርት መማር ከፈለጉ ይህንን ፎርም በመሙላት ቢልኩልን እንዴት መማር እንደሚችሉ እናሳውቅዎታለን፡፡ እግዚአብሔር ይባርክዎ፡፡