ለጌታችንና ለአምላካችን ለመድኃኒታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ የሚሆን ሥፍራ አላችሁ?

የእግዚአብሔር ፍቅር

ለጌታችንና ለአምላካችን ለመድኃኒታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ የሚሆን ሥፍራ አላችሁ?

በመምህር ጸጋ

“በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፥ የበኵር ልጅዋንም ወለደች፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው።” የቅዱስ ሉቃስ ወንጌል 2:6-7

ጌታችንና አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት የጠፋውን የሰውን ልጅ፤ እኔን፤ አንቺን፤ አንተን፤ እኛን፤ ሊያድን ወደዚህች ዓለም ተወለደ፡፡ ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛ ብርሃን ተወለደ፡፡ ህይወት ተገለጠ፡፡ የሚታዩትንና የማይታዩትን ሁሉ የፈጠረ ሁሉን ቻይ ኃያል አምላክ ወደዚህች ምድር ሲወለድ ራሱ የፈጠራት ምድር፤ ራሱ የፈጠራቸው የሰው ልጆች በአጀብ በሰልፍ አልተቀበሉትም፡፡ ሌላው ቀርቶ የሚወለድበትን ስፍራም አልሰጡትም፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ሊወለድ በተቃረበበት ጊዜ በዘመኑ ገናና ከነበረው ንጉሥ ከአውግስጦስ ቄሳር ሰው ሁሉ እንዲመዘገብ አስቸኳይ አዋጅ ታወጀ፡፡ ቅዱስ ዮሴፍም የጌታችንንና እና የመድኃኒታችንን እናት ቅድስት ድንግል ማርያምን ይዞ ወደ ቤተልሄም ተጓዘ፡፡ በመንገድ ላይ ሳሉም መውለጃዋ ደረሰ፡፡ ነገር ግን ማደሪያውን ማረፊያውን ቤት ሁሉ ሰዎች ቀድመው ይዘውት ነበርና የምትወልድበትን ስፍራ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ ሁሉንም ቦታ ሰዎች ተሽቀዳድመው ይዘውታል፡፡ መውለጃዋ ለደረሰ እናትም የሚራራ ልብ አልነበራቸውም፡፡ ስለዚህ የሰውን ሰፈር ትተው ወደ እንስሶች ማደሪያ ወደ በረት ሄዱ፡፡ የሰው ልጅ ያልተቀበላቸውን እንስሳት አስተናገዷቸው፡፡ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ይህንን የሰማይ ስጦታ ይህንን የሰው ሁሉ መድኃኒት ብርድ እንዳይመታው በያዘችው ጨርቅ ጠቀለለችው፡፡ የእናት አንጀትዋ እየተንሰፈሰፈ ተጠነቀቀችለት፡፡ እርስዋ ራስዋ አራስ ስለሆነች ሰውነትዋ እንክብካቤ ቢያስፈልገውም እናት ናትና ራስዋን ረስታ እርሱን ትንከባከብ ነበር፡፡

የሰው ልጅ ያልተቀበላቸውን እንስሳት አስተናገዷቸው፡፡ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ይህንን የሰማይ ስጦታ ይህንን የሰው ሁሉ መድኃኒት ብርድ እንዳይመታው በያዘችው ጨርቅ ጠቀለለችው፡፡ የእናት አንጀትዋ እየተንሰፈሰፈ ተጠነቀቀችለት፡፡ እርስዋ ራስዋ አራስ ስለሆነች ሰውነትዋ እንክብካቤ ቢያስፈልገውም እናት ናትና ራስዋን ረስታ እርሱን ትንከባከብ ነበር፡፡

ወንድሞቼና እህቶቼ ዛሬስ? የሚል ጥያቄ ራሳችንን እንጠይቅ፡፡ ምናልባት ብዙዎቻችን በቁጭት ያን ጊዜ እኔ ብኖር ኖሮ ቤቴን እለቅለት ነበር እንል ይሆናል፡፡ በዚያን ጊዜ በነበሩትና ስፍራውን ሁሉ ቀድመው ይዘው ልትወልድ ላላት ድንግል አለመራራታቸውን እያየን እንፈርድባቸው ይሆናል፡፡ ነገር ግን እኛ የምንጠየቀው ስለራሳችን ዘመንና ድርጊት ነው፡፡ በነርሱ ላይ መፍረዳችን እኛን ንጹህ አያደርገንም፡፡ ስለዚህ ዛሬስ ለዚህ ድንቅ ንጉሥ በህይወታችን ስፍራን ሰጥተነዋል ወይ? ብለን ራሳችንን እንጠይቅ፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን በኛ ዘንድ ስፍራን የፈለገው ያን ጊዜ ብቻ አይደለም፡፡ እርሱ ሁልጊዜ በህይወታችን ማደር ይፈልጋል፡፡ ሰው የተፈጠረው የአምላኩ ማደሪያ ለመሆን ነው፡፡ ስለዚህ ዛሬም በእያንዳንዳችን ህይወት ስፍራ ማግኘትና ማደር መክበር ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን አሁንም የብዙዎቻችን ህይወት በሌሎች እንግዶች ቀድሞ ተይዞአል፡፡ ገንዘብ ምኞት ሥጋዊነት፤ዓለማዊነት፤ዘረኝነት፤ብሄራዊስሜት፤አገራዊነት፤አሜሪካዊነት፤ኢትዮጵያዊነት፤ ኤርትራዊነት ወዘተ ስፍራውን ቀድመው ይዘውታል፡፡ ሰው ሁሉ ተሞልቶ የሚታየው በነዚህ ነው፡፡

የአባት ፍቅር

ከዚህ በታች ያለውን የወንጌል ድምጽ እንዲሰሙ በታላቅ ፍቅር እንጋብዝዎታለን፡፡

Play Video

ወገኖቼ ሆይ ሁሉን የፈጠረ፤ እኛንም ሁላችንን የፈጠረ፤ ይህችንም ውብ ምድር ፈጥሮ የሰጠን፤ የፕላኔትዋና የኛ ባለቤትና ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ ከአገራችንም ከብሄራችንም ከራሳችንም ከዚህች ዓለም ሁሉ ቀድሞ ህይወታችንን ሊወርሰው ይገባል፡፡ እስኪ እያንዳንዳችን ራሳችንን ጓዳችንን ልባችንን ህይወታችንን እንፈትሽ፡፡ ሌሎች እንግዶች ቀድመው አልያዙትም ይሆን? በእውነት ይህ ድንቅና አፍቃሪ ጌታ በህይወታችን ቀዳሚውን ስፍራ ይዞ ይሆን? ካልሆነ ከነዚያ ተሽቀዳድመው ስፍራውን ሁሉ ከያዙትና በበረት እንዲወለድ ከጨከኑበት በምን እንሻላለን? ስለዚህ ይህንን ቅዱስ መልእክት የምታነቡ ሁላችሁ ዛሬ ቀድመው ህይወታችሁን የያዙትንና የተቆጣጠሩትን እንግዶች ሁሉ አስወጥታችሁ የክብርን ጌታ በህይወታችሁ ለማኖር ወስኑ፡፡ ቤቱን በንስሐ ጥረጉለት፡፡ ህይወታችሁ እፍ ብሎ እስትንፋሱን በመስጠት የፈጠራችሁ የእግዚአብሔር ነው፡፡ ዘረኝነት ሥጋዊነት ገዳይነት ክፋት ዓለማዊነት በህይወታችሁ ሊኖር አልተፈጠራችሁም፡፡ ሁላችንም ወደ አምላካችን እንመለስ፡፡ እኛን ለማዳን ከሰማየ ሰማያት የወረደውን በበረት ተቀብለን በመስቀል የሸኘነውን የዋህና አፍቃሪ ጌታ ወደ ህይወታችን እናስገባው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሁላችንንም ይርዳን፡ አሜን፡፡

ወንድማችሁ መምህር ጸጋ ፡፡

1 thought on “ለጌታችንና ለአምላካችን ለመድኃኒታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ የሚሆን ሥፍራ አላችሁ?”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *